Saturday, 13 February 2016 10:53

መንግስት በነዳጅ ዋጋ ላይ ተገቢውን ቅናሽ አላደረገም ተባለ

Written by 
Rate this item
(24 votes)

    በአዲስ አበባ ከተማ በታክሲ ሹፌርነት ላለፉት 18 ዓመታት የሰሩት አቶ ጥላሁን ቢሆነኝ፤ በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ትርፋማ ሆነው በሥራቸው ለመቀጠል ወሳኙ ነዳጅ የሚገዙበት ዋጋ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የነዳጅ ዋጋ እርካሽ ሲሆን ብቻ ነው ትርፋማ የሚሆኑት ይላሉ፡፡ ከአንድ አመት በላይ በአለም ገበያ ነዳጅ በከፍተኛ መጠን ዋጋው እያሽቆለቆለ ቢሄድም መንግስት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ባለማድረጉ፣ በየጊዜው ከሚንረው የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ ጋር ተደምሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፉን ክፉኛ ጐድቶታል ይላሉ አቶ ጥላሁን፡፡
ሰሞኑን በቤንዚን ችርቻሮ መሸጫ ላይ መንግስት ያደረገው የ82 ሳንቲም ቅናሽ እጅግ ከጠበቁት በታች እንደሆነባቸው የጠቆሙት የታክሲ  ሹፌሩ፤ ቢያንስ በሊትር እስከ 3 እና 4 ድረስ ብር ቅናሽ ይደረጋል የሚል ግምት እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡
ሌላው የታክሲ አሽከርካሪም የአቶ ጥላሁንን ሃሳብ ይጋራል፡፡ መንግስት የነዳጅ ዋጋን በደንብ ቀንሶ የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ መጠነኛ ቅናሽ ቢያደርግ ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆን ነበር ይላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አብዛኛው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ በኪሳራ ነው የሚንቀሳቀሰው የሚለው ሹፌሩ፤ መንግስት  የታክሲ ታሪፍን ማስተካከል ከፈለገ፣ ነዳጅ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ፣ ህብረተሰቡም ሣይጐዳ ተጠቃሚ ሊያደርገን ይችላል ባይ ነው፡፡
መቀመጫውን በአዲስ አበባ ባደረገ አንድ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ውስጥ በኢኮኖሚ አማካሪነት የሚያገለግሉት ዶ/ር በላይ ተስፋ ኪሮስ እንደሚሉት፤ ነዳጅን ከውጭ የሚያስገቡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ከዓለም አቀፉ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ሲያደርጉ ግን በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ “መንግስት አሁን ካለው የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ ጋር የተመጣጠነ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ በማድረግ፣ ኢኮኖሚው የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል መትጋት አለበት፤ ከፍተኛ የነዳጅ ቅናሽ ካደረገ እየተረጋጋ የመጣውን  የግብይት ስርዓት ሊያናጋው ይችላል” ብለዋል - ባለሙያው፡፡ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም፡፡ መንግስት አለማቀፉን የነዳጅ ዋጋ መነሻ አድርጐ ከፍተኛ ቅናሽ ቢያደርግም በምንም መመዘኛ የኢኮኖሚ መናጋት እንደማይፈጥር ይገልፃሉ፡፡ “ነዳጅ በአለም ገበያ በከፍተኛ መጠን ሲቀንስ በዚያው ልክ በሀገር ውስጥም መቀነስ ይገባዋል” የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ ምናልባት መንግስት ቀደም ሲል ነዳጅ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ድጐማ ለማካካስ ወይም ምናልባት ዋጋው እንደገና ቢጨምር ሰው እንዳይማረር በሚል በለመደው ይሂድ ብሎም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይሄ አግባብ አይደለም፤ ዋጋ ሲጨምር እንደሚጨምረው ሁሉ ሲቀንስም በተገቢው መንገድ መቀነስ አለበት፤ ይላሉ፡፡ የዛሬ ዓመት አካባቢ ነዳጅ በአለም ገበያ ከ140 ወደ 100 ዶላር ሲቀንስ፣ በሀገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ከ20 ብር ወደ 9 እና 10 ብር መቀነስ ነበረበት ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ አሁን በዓለም አቀፍ ገበያ ከ30 ዶላር በታች ሲሸጥም በሃገር ውስጥ 7 እና 8 ብር በሊትር መሸጥ እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡ መንግስት የዚህን ያህል የዋጋ ቅናሽ ቢያደርግ ራሱንም ሆነ አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚውን የሚጐዳው ነገር የለም ይላሉ - ባለሙያው፡፡
“እንደውም ነዳጅ በ7 ብር እና በ8 ብር እንዲሸጥ ሲያደርግ የትራንስፖርት ዋጋ ይቀንሳል፤ ዋጋው ሲቀንስ ከውጭ የሚመጡ እቃዎች፣ ከገበሬው ለከተሜው የሚቀርቡ ምርቶች፣ ለገበሬው የሚሄዱ እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያሉ ግብአቶች … ዋጋቸው ይቀንሳል” የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ በዚህም በተለይ ቋሚ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሠራተኞችና ጡረተኞች የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ሠራተኞችና ጡረተኞች በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን አውስተው፤ የትራንስፖርትና መሠል ወጪዎች ሲቀንስላቸው በኪሣቸው የሚቀመጠው ገንዘብ እየበረከተ ስለሚሄድ፣ ኑሮን መቋቋም ያስችላቸዋል ብለዋል፤ ባለሙያው፡፡ አሁን በአለማቀፍ ደረጃ ነዳጅ በከፍተኛ መጠን በመቀነሱ የውጭ ምንዛሬን ከመቆጠብ አንፃር ዋነኛ ተጠቃሚው መንግስት ቢሆንም በአገር ውስጥ ተገቢውን፤ የዋጋ ቅናሽ የማያደርገው ብቸኛ ነዳጅ አቅራቢ በመሆኑና የሚወዳደረው ባለመኖሩ ነው ያሉት ባለሙያው፤ ይሄም በነዳጅ ግብይት ላይ የገበያ መር ኢኮኖሚው እየሠራ አለመሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡የአገሪቱን የነዳጅ ዋጋ በየ 6 ወሩ እንደሚከልስ የጠቆመው መንግስት በበኩሉ፤ የነዳጅ ዋጋችን ከአፍሪካ የመጨረሻው ዝቅተኛው ነው ብሏል፡፡  በአለም አቀፉ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከዚህ በኋላ ይጨምራል ተብሎ እንደማይገመትና እንዲያውም ከ20 ዶላር በታች ሊወርድ እንደሚችል መተንበዩንም ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ጠቁመዋል፡፡ በቅርቡ የንግድ ማዕቀብ የተነሣላት ኢራን በቀን 2 ቢሊዮን በርሜል ነዳጅ ለአለም ገበያ ለማቅረብ መወሰኗን ያስታወቀች ሲሆን ተፎካካሪዋ ሳኡዲ አረቢያ በበኩሏ፤ በቀን 10 ቢሊዮን በርሜል ነዳጅ ለገበያ እያቀረበች መሆኗ የነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ ይሄዳል የሚለውን ትንበያ ያጠናክረዋል፡፡
ይህን መነሻ አድርጐ መንግስት የነዳጅ ዋጋን በከፍተኛ መጠን በመቀነስ፣ በተለይ ቋሚ ገቢ ያላቸውን ዜጐች ተጠቃሚ የሚያደርግበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ይመክራሉ፡፡ በኢትዮጵያውያን ሚሊኒየም (2000 ዓ.ም) መግቢያ ላይ አለምአቀፍ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ65 - 100 ዶላር የነበረ ሲሆን በወቅቱ የአገር ውስጥ የቤንዚን ዋጋ በሊትር 7 ብር ከ77 ሣንቲም ነበር፡፡ በሀገር ውስጥ ገበያ ነዳጅ በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠው ከግንቦት 1 ቀን 2003 እስከ መስከረም 26 ቀን 2004 በነበረው ጊዜ ውስጥ ሲሆን በወቅቱ 1 ሊትር ቤንዚን በ20 ብር ከ94 ሣንቲም ተሸጧል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት በአለማቀፍ ገበያ የ1 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ደግሞ ከ85 እስከ 118 ዶላር ነበር፡፡
በጥር 2007 የመጀመሪያ ሁለት ሣምንታት የነዳጅ ዓለም አቀፍ ዋጋ በበርሜል ከ95 ዶላር ወደ 50 ዶላር የወረደ ሲሆን የሀገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ደግሞ በሊትር የ2 ብር ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ይህም የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ከጀመረበት ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ከፍተኛው ቅናሽ ነበር፡፡  በወቅቱ መንግስት ቢያንስ የነዳጅ ዋጋን በሊትር እስከ 9 ብር ማውረድ እንደነበረበት አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጠቁመው መንግስት በእነዚህ ጊዜያት ከነዳጅ ሽያጭ ከፍተኛ ትርፍ መሰብሰቡን ያስታውሳሉ፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው ቢለዋወጥም የአገር ውስጥ ታሪፍ ግን እስካለፈው ሣምንት ድረስ ሳይለውጥ ነው የቆየው፡፡
 ከ13 አመት በፊት የሀገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በሊትር ከ5 ብር በታች እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማል፡፡ ለአንድ አመት ያህል ከጥር 23 ቀን 2007 እስከ ጥር 17 ቀን 2008 ዓ.ም የቆየው የነዳጅ ታሪፍ፤ በሚያዚያ ወር 2003 ዓ.ም ከነበረው ጋር ተቀራራቢ ሲሆን በወቅቱ በሰሜን አፍሪካና በአረብ ሀገራት የተነሳውን ተቃውሞና የመንግስት ግልበጣ ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየበት ነበር፡፡ በሚያዚያ 2003 ዓ.ም የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 100 ዶላር የነበረ ሲሆን በአገር ውስጥ አንድ ሊትር ቤንዚን በ17 ብር ከ88 ሣንቲም ይሸጥ ነበር፡፡ በጥር 2008 ዓ.ም ነዳጅ በአለማቀፍ ገበያ ከ30 እስከ 35 ዶላር ሆኖ፣ በአገር ውስጥ በሊትር 17 ብር 43 ሣንቲም ተሸጧል፡፡ ሰሞኑን የተደረገው ቅናሽም የ80 ሣንቲም ሲሆን በአሁኑ ሰዓት አንድ ሊትር ነዳጅ በ16 ብር 61 ሣንቲም እየተሸጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከሠሞኑ መንግስት በነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ያደረገው የዋጋ ማስተካከያ የሸቀጦች ዋጋን እንደሚያረጋጋ የጠቆሙት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋም በአፍሪካ ዝቅተኛ የሚባል ነው ብለዋል፡፡  

Read 10116 times Last modified on Saturday, 13 February 2016 12:21