Saturday, 13 February 2016 10:51

“ለግጭት ተጐጂዎች፣ ካሳ ለመክፈል ታስቧል”

Written by 
Rate this item
(25 votes)

በኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት ሙሉ ለሙሉ አልቆመም
“በተወሰኑ አካባቢዎች ግርግር አጋጥሟል፤ ግን እየተረጋጋ ነው”
ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚደረገው ድርድር የግድቡን ህልውና የሚነካ አይደለም” (ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ)
          በአወዛጋቢው “ማስተር ፕላን”  መነሻነት ከሁለት ወራት በፊት በኦሮሚያ አካባቢዎች በተከሰተው ተቃውሞና ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የክልሉ መስተዳድር ካሳ ለመክፈል እንዳሰበ ተገለፀ፡፡
ግጭቱ ሙሉ ለሙሉ አለመቆሙ በየጊዜው ሲዘገብ የቆየ ሲሆን፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “ችግር ተፈጥሮባቸው በነበሩ አካባቢዎች መረጋጋት እየተፈጠረ ነው፤ ትምህርት ቤቶችም መደበኛ ተግባራቸውን እየቀጠሉ ነው” ብለዋል፡፡ በቅርቡ በቦረና ጉጂ አካባቢና በተወሰኑ መንደሮች ግን ግርግሮች አጋጥመዋል ብለዋል - ሚኒስትሩ ትናንት በሰጡት መግለጫ፡፡
ግጭቱን አባብሰዋል ተብለው የታሰሩ ሰዎች በህግ ይዳኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሳያውቁ የተሳተፉ ሰዎች ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡ በጎንደር አካባቢና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ከቀረቡት የውሳኔ ሃሳቦች ላይም ሚኒስትሩ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ መንግስት ተቀብሎ ሊያጣራቸው የሚችሉ ሀሳቦች መኖራቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሱው፤ በአጠቃላይ ግን ለአውሮፓ ፓርላማ ቀረበ ለተባለው የውሳኔ ሀሳብ መንግስት እምብዛም ትኩረት አይሰጠውም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከግብፅና ከሱዳን ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር የግድቡን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመወሰን የሚደረግ ድርድር አይደለም ብለዋል፡፡
ከግድቡ የጋራ ተጠቃሚ ለመሆንና በሁለቱ ሃገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ በመወያየት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ብቻ ያለመ ድርድር ነው ብለዋል -ሚኒስትር አቶ ጌታቸው፡፡

Read 6073 times