Saturday, 13 February 2016 10:50

በሽብር የተከሰሱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከእስር እንዲለቀቁ ታዘዘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

    በሽብር ወንጀል የተከሰሱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹን አብርሃ ደስታ፣ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺና የሸምስ አሰፋን ጨምሮ አቶ አብርሃም ሰለሞን ከእስር እንዲለቀቁ ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ፃፈ፡፡ ተከሳሾቹ በከፍተኛው ፍ/ቤት ከቀረበባቸው ክስ በነፃ መሠናበታቸውን ተከትሎ በአቃቤ ህግ ይግባኝ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው በጠቅላይ ፍ/ቤት እየተከታተሉ ሲሆን ፍ/ቤቱ ከትናንት በስቲያ “ከእስር ነፃ ሆናችሁ በውጪ ጉዳያችሁን እንድትከታተሉ የመፍቻ ትዕዛዝ ይፃፍላችኋል ባለው መሠረት፤ በትናንትናው እለት ትዕዛዙ መፃፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በማረሚያ ቤት አስተዳደር በደል እየደረሰብን ነው በማለት ከ5ቱ ተከሳሾች ሶስቱ ማለትም አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ የሸዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ ለጠቅላይ ፍ/ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ማረሚያ ቤቱ ለየካቲት 3 ምላሽ ይዞ እንዲቀርብ ፍ/ቤት ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በቀጠሮው እለት ዳኞች ከማረሚያ ቤቱ መልስ ሳይሆን ነገ መፈቻችሁ ይፃፍላችኋል የሚል ምላሽ ከትናንት በስቲያ የሰጣቸው ሲሆን የመፈቻ ትዕዛዙም ከፍ/ቤቱ ተጽፎ መውጣቱን የተከሳሾች ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን ለአዲስ አድማስ አረጋግጠዋል፡፡
በመፈቻ ትዕዛዙ ላይ ተከሳሾች ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ከሃገር እንዳይወጡ ለኢምግሬሽን ትዕዛዝ እንዲደርስና ፍትህ ሚኒስቴር እንዲያውቀው የሚል መልዕክት መኖሩን የጠቀሱት አቶ አመሃ፤ እስከ ትናንት አመሻሹ ድረስ (ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰአት ድረስ) ተከሳሾቹ ከእስር አለመለቀቃቸውን ነግረውናል፡፡
የአቶ ሃብታሙ አያሌው ባለቤት አድማስ የመፈቻ ትዕዛዙ ለማረሚያ ቤቱ ተወካይ መድረሱን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የአቶ ሃብታሙ አያሌው ባለቤት፤ ትናንት አመሻሹ ድረስ ከእስር መፈታታቸውን እየተጣጠበቁ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ተከሳሾቹ ከተጠየቀባቸው ይግባኝ ጋር በተያያዘ ከነገ በስቲያ ሰኞ በጠቅላይ ፍ/ቤቱ ቀጠሮ ያላቸው ሲሆን ፍ/ቤቱ ሐሙስ እለት የመፈቻ ትዕዛዝ እንደሚፃፍላቸው ሲያሳውቋቸው “ሰኞ የሚኖራችሁን ቀጠሮ ከቤት መጥታችሁ ነው የምትከታተሉት” ብለዋቸው ነበር ተብሏል፡፡

Read 4004 times