Saturday, 13 February 2016 10:48

በክልሎች መንጃ ፈቃድ ማውጣት ሊከለከል ነው

Written by 
Rate this item
(38 votes)

ደንብ በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ከባድ ቅጣት ሊጣል ነው
       የደንብ ጥሰት በፈፀሙ አሽከርካሪዎች ላይ ከባድ ቅጣት የሚጥል አዲስ ህግ ሊተገበር ሲሆን በአሽከርካሪው ላይ ቅጣት ከመጣል በዘለለ በእያንዳንዱ ጥፋት ላይ በሚያዝ ነጥብ መሰረት፣ የመንጃ ፈቃድን ለስድስት ወራትና ለአንድ ዓመት ከማገድ አንስቶ ከእነአካቴው እስከ መሰረዝ የሚደርስ ነው፡፡
በክልሎች መንጃ ፈቃድ የማውጣት አሰራርም እንደሚቀርና ከአንድ ማዕከላዊ ሥፍራ ወጥ በሆነ መልኩ ብቃትን መሰረት አድርጐ መንጃ ፈቃድ የመስጠት አሰራር እንደሚጀመር ታውቋል፡፡የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፤ አዲሱ ህግ ተግባራዊ ስለሚደረግበት ሁኔታ ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ለመወያየት ሰሞኑን አዘጋጅቶት በነበረው መድረክ ላይ የትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት፣ የግንዛቤ ትምህርት ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ ድል አርጋቸው ለማ እንደተናገሩት፤ ህጉ በ2003 ዓ.ም በአዋጅ ደረጃ ቢወጣም በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው ይኸው ህግ፤ ለአደጋ መንስኤ የሚሆኑ ተደጋጋሚ አጥፊዎችን ከመንገድ ለማስወጣት፣ በጥቂት ሥነ ምግባር የጐደላቸው አሽከርካሪዎች ምክንያት የሚጠፋውን ህይወት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለመከላከል፣ የአጥፊ አሽከርካሪዎችን ቁጥር ለመቀነስና ለህግና ደንብ የሚገዛ አሽከርካሪን ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል አቶ ድልአርጋቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፎርጅድ መንጃ ፍቃዶች መሰራጨታቸው የተገለፀ ሲሆን ለዚህም ደግሞ ምክንያቱ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጡ ወጥነት የጐደለው መሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድም ባለስልጣን መ/ቤቱ በአሻራ የተደገፈና በማዕከላዊነት ከአንድ ሥፍራ ላይ ብቻ የሚሰጥ አዲስ የመንጃ ፍቃድ አወጣጥ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም ታውቋል፡፡ ይህ አሠራር የመንጃ ፍቃዶች በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች የሚሰጡበትን ሁኔታ የሚያስቀር ሲሆን ወጥ የሆነ በአሽከርካሪው ብቃት ላይ ብቻ ተመስርቶ መንጃ ፍቃድን ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
በአገሪቱ ባለፈው ዓመት ብቻ ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ የ3847 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከ11ሺህ በላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋዎች እንደደረሱ የኤጀንሲው መረጃ ይጠቁማል፡፡

Read 13043 times