Saturday, 13 February 2016 10:24

ዩኒቨርስቲዎቹ፤ በህክምና ትምህርት ጥራት ላይ ይመክራሉ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(1 Vote)

    ሰላሳ አንዱም ዩኒቨርስቲዎች በኢትዮጵያ የህክምና ትምህርት ጥራት፣ ተደራሽነትና አግባብነት እንዲሁም የጋራ ትብብር ዙሪያ ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል እንደሚመክሩ ተገለፀ፡፡ የምክክር ጉባኤውን የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ከ“ፒፕል ቱ ፒፕል” (P2P) እና ከኬንታኪ ዩኒቨርስቲ (ዩኬ) ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል ተብሏል፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አስተዋይ መለስ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በጉባኤው ላይ ከ31ዱም ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ 130 የጤና ምሁራን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ፣ የትምህርት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች፣ እንዲሁም የኬንታኪ ዩኒቨርስቲና የ“ፒፕል ቱ ፒፕል” ተወካዮች ይሳተፉበታል፡፡ ጉባኤው በዋነኛነት ትኩረት የሚያደርገው በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተቋቋሙ አዳዲስና ነባር የህክምና ትምህርት ቤቶችን በተማረ የሰው ሃይል አቅም ግንባታ፣ በክህሎት ማሻሻያና በቤተ-ሙከራ ግብአቶች አደረጃጀት ማጠናከር ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም የህክምና ትምህርት ቤቶቹን በውጪ ከሚገኙ አቻ የትምህርት ተቋማት ጋር በማገናኘት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንዲያገኙና አለቀም አቀፍ ደረጃ እንዲኖራቸው መንገድ ለመጥረግ ነው ተብሏል፡፡  ከምክክር ጉባኤው ባሻገር ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ፣ አሜሪካ ከሚገኘው “ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኬንታኪ” ጋር በህክምና ትምህርት ዘርፍ እንዲሁም ሁለቱ አቻ ተቋማት በጋራ ሊሰሩባቸው በሚያስችላቸው ሌሎች ዘርፎች ላይ የጋራ ስምምነት ፊርማ ይፈራረማሉ
ተብሏል፡፡

Read 1394 times