Saturday, 18 February 2012 10:55

ጐበዝ! በ1ለ5 እንደራጅ! (የተደራጀ ተጠቀመ)

Written by  ኤሊያሰ
Rate this item
(1 Vote)

“የሀገሬ ሰው ቅቤው ባቄላ ነው፤ ሁሉ ሥጋ አያገኝም” ጃንሆይ

እኔ የምላችሁ … ከዚህች ከምንወዳት ጦቢያችን የዘመቻና የወረት አባዜ አልነቀል አለ አይደል? (እንደሙስና!) በነገራችን ላይ ወረት ስል ፋሺን ማለቴ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡  (“ዘመቻ” በጐጂ ልማዶች ውስጥ ይካተትልን) እስቲ የ100ሺ ብር ሽልማት የሚያስገኝ አንድ ቀላል ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ “የአውራ ፓርቲያችን የወቅቱ ፋሺን ምንድነው?” እናንተ ጥያቄውን መልሳችሁ 100ሺ ብሯን ብትወስዷት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ሆኖም የሽልማት ገንዘቡን ስፖንሰር የሚያደርግ “ልማታዊም” ሆነ “ኪራይ ሰብሳቢ” ባለሃብት ተፈልጐ በመጥፋቱ ጥያቄውን እኔው ልመልስላችሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ የሚከተለው ፋሺን ምን መሰላችሁ? “1 ለ 5” የተሰኘ የአደረጃጀት ስታይል ነው፡፡ ምናልባት እኔን ከተጠራጠራችሁኝ “አውራውን የመገናኛ ብዙሃን” ተከታተሉ! (ኢቴቪን ማለቴ ነው)

አርሶአደሩ ግንባር ቀደም የፋሺኑ ተከታይ ሆኗል - 1ለ5 ተደራጅቶ ልማቱን እያጧጧፈ ይገኛል፡፡ ፋሺኑ ት/ቤት ገብቷልም እየተባለ ነው፡፡ ተማሪዎች ጥናት የሚያጠኑት በ1 ለ5 ስትራቴጂ ሆኗል፡፡ በሜጀር ጄኔራል ኃየሎም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ተማሪዎች በ1 ለ 5 አደረጃጀት የጥናት ቡድን መስርተው “ቀለሜዋ” እንደሆኑ ሰምቻለሁ (እድሜ ለኢቴቪ!) የት/ቤቱ መምህራን እንዳሉት፤ ቀድሞ ደካማ የነበሩ ተማሪዎች በዚህ አደረጃጀት  ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ነው፡፡ (ከምኔው?)

እኔ የምለው … 1 ለ 5 የሚመለከተው የመንግስት መ/ቤት የትኛው ነው? ለሌላ እኮ አይደለም - ጥያቄ ለማቅረብ ነው፡፡ ለምሳሌ “እኔ ለብቻዬ ነው ማጥናት የሚመቸኝ” ያለ ተማሪ “መብትህ ነው” ይባላል ወይስ ካልተደራጀህ መማርም ማጥናትም አትችልም ተብሎ ከትምህርት ውጭ ይሆናል?

ልብ አድርጉ! ስጋቴን መግለፄ እንጂ ትምህርትና ጥናት አደናቃፊ ለመሆን ፈልጌ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ የሚከበሩትን ከተማዊና ፓርቲያዊ የልደት በዓላት በ1 ለ5 ስትራቴጂ ለማክበር አቅጃለሁ፡፡ የአዲስ አበባ 125ኛ ዓመት የልደት በዓልና የህወሀት 37ኛ ዓመት በዓልን ማለቴ ነው፡፡ መቼም ከኮሚቴ ይልቅ በ1ለ5 መደራጀት ይሻላል አይደል? (የባሰ ከሆነም እንደ ፍጥርጥሩ!)

እንግዲህ ኢህአዴግ አንድ የልማት ስትራቴጂ ሲቀዳ ወይም ሲኮርጅ ማንንም ለመጉዳት አስቦ አይደለም (ጠ/ሚኒስትሩ የሊዝ አዋጁ የወጣው ማንንም ለመጉዳት ታስቦ አይደለም ማለታቸውን ልብ ይሏል) ሆኖም ግን ወደታች ሲወርድ እንደተለመደው በአግባቡ ላይተገበር ይችላል የሚል “ቅዱስ ስጋት” አለኝ፡፡ እስቲ አስቡት … ደራሲና ቴያትረኛ  በ1ለ 5 ካልተደራጀ የፈጠራ ሥራ ውጤታማ አይሆንም ቢባልስ? (ሰውረና ከመአቱ!)  ፊልምም ለመስራት እንዲሁ … የሚል መመሪያ ቢወጣስ? (አይወጣምን ትተሽ…)

እኔና እናንተ እንዲህ ቁጭ ብለን የምናብጠለጥለውን የ”1ለ5” አደረጃጀት ኢህአዴግ ከየት እንደቀዳው ቢነግረን ደስ ይለናል፡፡ (ብቻ ከቻይና እንዳይሆን?)

ከልቤ ነው የምላችሁ … እኔ 1ለ5 የሚለውን ልማታዊ አደረጃጀት የማደናቀፍ አንዳችም ዓላማ የለኝም፡፡ (ምን ልጠቀም?) ግን ደግሞ ህገመንግስታዊ መብቴን በአግባቡ የመጠቀም ባህልን የማዳበር ግዴታ እንዳለብኝ ይሰማኛል - ሃሳቤን በነፃነት በመግለፅ፡፡ በነገራችሁ ላይ 1ለ5 የጓደኝነት ቡድን ለማደራጀት አቅጃለሁ (አጋርነቴን ለማሳየት!) እናም የቡድኑ አባል ለመሆን የምትፈልጉ ልታነጋግሩኝ ትችላላችሁ፡፡ (ያለምንም ክፍያ!)

ለኢህአዴግ ወይም ለሚመለከተው አካል አንድ ጥያቄ ጣል ላድርግና የ1ለ5 አጀንዳዬን በዚሁ ልቋጭ፡፡ ይሄ 1ለ5 የአደረጃጀት ስትራቴጂ በምርጫ ወቅትም ሥራ ላይ ይውላል እንዴ? (ለጠቅላላ ዕውቀት ብዬ ነው!) አንድ ዋና ጉዳይ ረሳሁ… ያ ዝነኛው BPR ድምፁ የጠፋው ፋሽኑ አልፎበት ነው ወይስ በሎው ፕሮፋይል (ድምፁን አጥፍቶ ማለቴ ነው) ሥራውን እየሰራ ነው? (ቢሰራ ይሻለዋል)

እናንተ… ሰሞኑን የሙስና ዜና ሰምታችኋል? የሰበታን መሬት ሸንሽነው የቸበቸቡት የቀድሞ የኢህአዴግ ሹማምንት “ሸቤ” ገቡ ተባለ እኮ! ከ2 ዓመት እስከ 10 ዓመት እስር እኮ ነው የተበየነባቸው፡፡ የገንዘብ ቅጣቱ ሳይጨመር፡፡ ለነገሩ እስሩ ነው እንጂ ገንዘቡ ብዙም አይጐዳቸውም (የመሬት ከበርቴ ነበሩ እኮ!) ጠ/ሚኒስትሩ ባለፈው የፓርላማ ንግግራቸው “የመንግስት ሌቦች” ያሏቸው እነዚህን “የመሬት ሱሰኞች” ነው አይደል?

አሁን አሁን በደንብ አስተዋላችሁ ከሆነ ብዙዎቹ ነገሮች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ለምሳሌ ገዢ ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ኪራይ ሰብሳቢና ልማታዊ ባለሃብት፣ የግልና የመንግስት ሌቦች ወዘተ… እኔ የምላችሁ ግን … ኪራይ ሰብሳቢነትና ልማታዊነት በደም ምርመራ አይታወቅም እንዴ? (እስቲ ቻይና ትጠየቅ!)

ሰሞኑን መድረክ ፓርቲ በአዲሱ የሊዝ አዋጅ ዙሪያ ያካሄደውን ህዝባዊ ስብሰባ ተከታትላችኋል? በአካል ማለቴ አይደለም - በኢቴቪ የዜና እወጃ፡፡ እውነቱን ለመናገር የተሰጠው የዜና ሽፋን ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ወይም በኢቴቪ እንዲያብብ ለሚመኝ ቅን ዜጋ ሁሉ ጥሩ ተስፋ የሚያሳድር ይመስለኛል፡፡ እኔማ የዜናውን ሚዛናዊነትና የተሰጠውን የሽፋን ጊዜ ስመለከት ቢቢሲ በኢቴቪ የአየር ሰዓት ተሰጠው እንዴ ብዬ ነበር፡፡ በኋላ ግን የጥንት የጠዋቱ ኢቴቪ መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ ከዛ ምን አልኩኝ መሰላችሁ - ለራሴ፡፡ “ኢቴቪ ለካ አውቆ ነው የሚያጠፋው!” እናም ኢቴቪን “ባንዳፍ” ብየዋለሁ - ለመድረክ በሰጠው ዓይነት ሚዛናዊ የዜና ሽፋን እንዲቀጥል! (በሌላ አነጋገር Keep it up ማለቴ ነው!)

በነገራችን ላይ ይሄ የሊዝ አዋጅ ተቃዋሚዎችን እያነቃቃ እኮ ነው፡፡ እናም አዋጁ

ሌላ ፋይዳ የለውም ቢባል እንኳ ተቃዋሚዎችን ማነቃቃቱ እንደ ቀላል መታየት የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ መድረክ ባለፈው ሳምንት በሊዝ አዋጁ ላይ ባካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ አንዳንድ ተሳታፊዎች “ኢህአዴግ በሊዝ አዋጁ ሰበብ ሚስቶቻችንን ሊነጥቀን ነው” የሚል ስጋት አስተጋብተዋል፡፡ (በሊዝ ነው?)

ባለፈው ሰሞን በአረብ ሳት የሚሰራጩት የኢቴቪ ሦስት ቻናሎች ያለማስጠንቀቂያ ድርግም ማለታቸውን ተከትሎ አንዳንድ “የዲሽ ሱሰኞች” ሲንጫጩ እንደነበር ሰምታችኋል? (እኔ ግን ኢቴቪን እንደወረደ ነው  የማየው - ከምንጩ!)፡፡ አቤት ያኔ ታዲያ… ምን ያልተወራ ነገር አለ መሰላችሁ! እናላችሁ… የኢቴቪ የሳተላይት ዲሽ ሥርጭት ሲቋረጥ የኤርትራ ቲቪም ተቋርጦ ነበር አሉ፡፡ የሁለት ጐረቤት አገሮች ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በአንድ ጊዜ ድርግም ሲል የሚፈጠረውን የመረጃ ክፍተት እስቲ አስቡት፡፡ ይህችን ሰበብ በማድረግ ታዲያ የሃሜት ሱሰኞች ሃሜታቸውን ሲነዙት ሰነበቱላችሁ - ያውም ያለ ቡና፡፡ (እኔ የምለው ግን ሃሜቱንም እንደቡናው Export ማድረግ አንችልም እንዴ?)

ባገኘሁት የሃሜት መረጃ መሰረት፣ መጀመሪያ የኢትዮጵያ መንግስት የቻይና የ“ጃሚንግ” ባለሙያዎችን ቀጠረና የኤርትራ ቲቪን ጃም አስደረገ (አፈነ) ተባለ፡፡ ከዛ ደግሞ … የኤርትራ መንግስት በተራው ሊበቀለን አሰበና ሌሎች የቻይና የጃሚንግ ባለሙያዎችን በመቅጠር ሦስቱን የኢቴቪ ቻናሎች ጃም አስደረጋቸው፡፡ (አፈናቸው) በጃሚንግ ግጥሚያውም ኤርትራ 3ለ1 ረታችን እያሉ ሲያሙን ሰምቼ ዝም አልኩኝ (በ1ለ5 አለመደራጀቴ ቆጨኝ!) እናም በውጤቱ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሳተላይት ሥርጭቶች ብላንክ (ባዶ) ሆኑ! ኢትዮጵያማ ፈርዶባት ከዚህ ቀደምም ቪኦኤን ጃም አስደርጋለች ተብላ ብዙ ታምታለች፡፡ ግን ግዴለም “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል”

በነገራችሁ ላይ ተቋርጦ የነበረው የአረብ ሳት የኢቴቪ ስርጭት ዳግም መቀጠሉን ኢቴቪ ሰሞኑን አብስሮናል (እልልልል…)

ወደ ሌላ አጀንዳ እንለፍ፡፡ ባለፈው ሳምንት የወጣው “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ላይ አንድ አስደማሚ ኢንተርቪው አንብቤ በእጅጉ ተደመምኩላችሁ፡፡ ጠያቂው ጋዜጠኛና ፀሃፌ … ተውኔቱ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ሲሆን ተጠያቂው ወይም እንግዳው ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ እስከ 90 ዓ.ም ድረስ በቤተ መንግስት በሰንጋ ጣይነት (በሬ አራጅነት) ያገለገሉት የማታው ወርቁ የተባሉ የ74 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ በተለይ ቀልቤን የሳበው በኑሮ ውድነቱ ዙሪያ “እንደወረደ” በሆነ አማርኛቸው የተናገሩት ቁም ነገር ነው፡፡ ከኢህአዴግ በፊት የቤተመንግስት የምግብ አቅርቦትን በተመለከተ ከጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “ምግብ? ደርግ እስተወደቀ ድረስ ምግብ እንደልብ ነው፡፡ ተዚያ በኋላ ቆሟል፡፡ በደንብ በክብር ነው የያዘን መንግስቱ ኃ/ማርያም” ይሉና ኋላ ላይ ነው ጉዱ የመጣው ይላሉ፡፡ “ይሄ ሁላ ወግ ማዕረግ ቀርቶ ሰሀን ተቤታችን እየቋጠርን ስንሄድ ጉድ አይደለም ይሄ?  ብቻ ተወው ያለፈው ጊዜ አለፈ፡፡ አሁን ሌላ ሌላውን እንጫወት” ያሉት አዛውንቱ የሠንጋን ዋጋ ድሮና ዘንድሮ እያነፃፀሩ የኑሮ ውድነቱን ያብራራሉ፡፡

“ፊትማ 200 ብር ነበር… የሐረር ሰንጋ… ኋላ ላይ ደርግ ሲመጣ 300 ብር ገባ፡፡” የሚሉት የማታው ወርቁ፤ ከደርግ በኋላ የሰንጋ ዋጋ ስንት እንደገባ ሲናገሩ፤

“እስተ 3000 ብር ደርሷል፡፡ ያኔም ደህና ነው፡፡ አሁን 15ሺ ደርሷል፡፡ 20ሺ ተሸጠ  ይባላል፡፡ 15ሺ ግን እያየሁ ነው፡፡ ተዚያ ምን አርገው እዚህ እንዳደረሱት አላውቅም” ብለዋል የመገረም ቅላፄ ባነገበ አነጋገር፡፡ የሰንጋው ዋጋ ከ200 ብር ተነስቶ 15ሺ ብር ላይ ጉብ ማለቱን በተመለከተ ምንድነው የሚሰማዎት ተባሉ - አዛውንቱ ሠንጋ ጣይ፡፡ “የሚሰማኝ ነገር አለ፡፡ ድሮ በሃይለስላሴ ጊዜ አንድ ቅንጣት ሥጋ አይወጣም፡፡ አንድም እህል አይወጣም፡፡ እንደውም ሚኒስትሮቻቸው ባቄላ ተወደደ እንሽጥ ቢሉ “የሀገሬ ሰው ቅቤው ባቄላ ነው፤ ሁሉ ሥጋ አያገኝም” ብለው ከልክለዋል፡፡ በደርግ መሸጥ ተጀምሮ ነበር፡፡ አሁን ሁሉም ነጋዴ ሆነ፡፡ ይሄ በጣም ያሳዝነኛል እንጂ … እኔ ጊዜዬ አልቋል፤ ነገ ብሞት ግድ የለኝም፡፡ … ለወደፊቱ ምን ሊቀምስ ነው ይሄ ትውልድ ብዬ አዝናለሁ፤ አዝናለሁ እንጂ ካንጀቴ” አሉ፡፡

የቀለም ትምህርት ባለማግኘታቸው የሚቆጩት እኚህ የዕድሜ ባለፀጋ፤ ለኑሮው ውድነት፣ ለእህሉና ለሰንጋው ዋጋ መናር ሰበቡ ምርቱ ሁሉ ለውጭ ገበያ መቅረቡ ነው የሚል ጥርጣሬ አዘል ግምት እንዳላቸው ከተናገሩት መገንዘብ ይቻላል፡፡

እኔ በበኩሌ ከዩኒቨርስቲ ግቢዎች መውጣትን እርም ካሉትና አፋቸው ከተለጐመው የኢኮኖሚ ምሁራኖቻችን ይልቅ እኚህ አዛውንት ተሽለውኛል፡፡ ቢያንስ የመሰላቸውን ነግረውናላ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ስለቀጣዩ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ጭንቅ ጥበብ ማለታቸው ልብ ይነካል፡፡

ይሄ ጭንቅ ጥበብ ግን ከየዋህነት የመነጨ የሚመስለን የዋሆች ሞልተናል (እኔን ጨምሮ) የእሳቸውን ቃለ ምልልስ አንብቤ ገና በቅጡ ሳላጣጥም ጆሮዬ የደረሰውን ዜና ብነግራችሁ በግርምት ትሞላላችሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ … የዜናው ይዘት እሳቸው እንዳሉት እውነት ትውልዱ ምን ሊቀምስ ነው … የሚል ስጋት ውስጥ የሚዶል በመሆኑ ነው፡፡ እናላችሁ “ሴቭ ዘ ቺልድረን” የተባለው ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት በዓለም ላይ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ህፃናት ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት በመላው ዓለም በየዓመቱ 7ሚ. ህፃናት ይሞታሉ ያለው ሪፖርቱ፤ የዚህ ሁሉ ሰበቡም የዓለም የምግብ ዋጋ እያሻቀበ መምጣቱ ነው ብሏል፡፡ (ልብ አድርጉ! አዛውንቱ ይሄን መረጃ ሳያገኙ ነው ስጋታቸውን የገለፁት)

ሰሞኑን ኢቴቪ በአንድ የአገራችን ክልል የተካሄደ የም/ቤት ስብሰባን ዘግቦ ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ የተናገሩ አንድ የም/ቤት አባል የክልሉ የውሃ ሽፋን 80 በመቶ ደርሷል በሚል የቀረበውን ሪፖርት በመቃወም የውሃ ሽፋኑ ከ50 በመቶ እንደማይበልጥ በመጠቆም የሚመለከተው አካል በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ጠየቁ፡፡ ይሄኔ ነው ግርምት የፈጠረብኝን ምላሽ የሰማሁት፡፡ የክልሉ ቱባ ባለሥልጣን እንዲህ አሉ:- “80 በመቶ የውሃ ሽፋን ሲባል አንፃራዊ ነው፡፡ ስሌቶቹ ግምታዊ ናቸው … ነገ ቁጥራቸው ሊቀንስ ይችላል”

እንዴት ነው ነገሩ? ዛሬ የተገለፀ ቁጥር በምን ተዓምር ነገ ጠዋት ሊቀየር ይችላል? (አንፃራዊ የሚለው ቃል ፍቺ ይነገረን!)

እኚሁ ቱባ ባለስልጣን አንድ ውል የተፈራረሙበትን ጉዳይ ጠቀስ ካደረጉ በኋላ “እሷ ሚስቴክ ናት!” ብለው እንደዘበት ሲያልፉዋት ሰምቼ በትዝብት ቆዘምኩ፡፡ “ሚስቴክ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ስህተት” የሚለውን የአማርኛ አቻውን የሚተካ ከሆነ ስህተት ያሏትን አስረግጠው ሊነግሩን በተገባ ነበር … ስል ከራሴ ጋር ተሟገትኩ፡፡ ሲሆንማ እንደዘበት ለታለፈችው “ሚስቴክ” ይቅርታ ብንጠየቅ አይጠላብንም፡፡ (ቅንጦተኛ እንዳይሉኝ ብቻ!)

የይቅርታ ነገር ሲነሳ የድሮው ቴሌ የአሁኑ ኢትዮ ቴሌኮም ትዝ አለኝ፡፡ ቴሌ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ የካርድ ሂሳብ ሞባይል ውስጥ ግባ አትግባ እያሉ መታገል አከተመ ብሎናል፡፡ (እኛም እልል ብለናል!) ሆኖም ለእስካሁኑ እንግልታችን ካሳው ቢቀር እንኳ ይቅርታ አንባልም እንዴ? (በአማርኛ ከከበደው እኮ በእንግሊዝኛ Sorry ሊለን ይችል ነበር)

አንድ ወዳጄ የነገረኝን ቀልድ ላጋራችሁና የዛሬውን የፖለቲካ ወጌን ልቋጭ፡፡ አንድ የ7 ዓመት ታዳጊ ነው አሉ፡፡ አስር ሳንቲም ይዞ ሲጫወት ድንገት ወደ አፉ ይሰደውና ይውጠዋል፡፡ በአካባቢው አሉ የተባሉ ባህላዊም ዘመናዊም የህክምና ባለሙያዎች የችሎታቸውን ያህል ጣሩ - 10 ሳንቲሟን ለማውጣት፡፡ በስተመጨረሻ የደረሰ አንድ ግለሰብ ግን ልጁን ነቅነቅ፣ ዘቅዘቅ፣ ወዝወዝ ሲያደርግ ቆየና ሳንቲሟን እንደምንም አወጣት፡፡ ከዚያም ከሌላው የተለየውን የህክምና ችሎታውን ለተሰበሰበው የአካባቢው ነዋሪ እንዲያብራራ ጥያቄ ቀረበለት፡፡ ግለሰቡም ጉሮሮውን ከጠራረገ በኋላ፡- “እኔ እኮ የህክምና ባለሙያ አይደለሁም፤ የአገር ውስጥ ገቢ ሠራተኛ ነኝ!” አለና ነዋሪውን አስደመመው፡፡ (አስገረመው!) መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ!!

 

 

Read 4302 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 11:03