Saturday, 06 February 2016 11:29

የበዕውቀቱ መፅሐፍ በግማሽ ቀን ተሸጦ አለቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የታዋቂው ገጣሚና ደራሲ በእውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” የተሰኘ አዲስ መፅሃፍ የመጀመሪያው 20ሺ ቅጂ በግማሽ ቀን ውስጥ ተሸጦ ማለቁን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ባለፈው ሰኞ ጠዋት ገበያ ላይ የዋለው መፅሀፉ፤ ከሰዓት በኋላ ተሸጦ እንዳለቀ ታውቋል፡፡ ሁለተኛው ህትመት ከአስር ቀናት በኋላ በድጋሚ በገበያ ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
የአንድ መፅሃፍ መደብር ባለቤት ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው፤ “እስከዛሬ ከሸጥኳቸው መፃህፍት በአንድ ቀን ያለቀ አልገጠመኝም፡፡ ይሄ የመጀመሪያው ነው፡፡” ብሏል፡፡
ሌላው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የመፅሃፍ አከፋፋይ በበኩሉ፤ “ብዙ የመፃህፍት ሽያጭ እንቅስቃሴ በሌለበት በዚህ ወቅት በአጭር ጊዜ ተሸጦ ያለቀው “ከአሜን ባሻገር” የመፃህፍትን ገበያ አነቃቅቷል፡፡ እስካሁን ታትሞ በወጣ በግማሽ ቀን ውስጥ ተሸጦ ያለቀ መፅሃፍ አላየሁም፡፡ በህዝቡ ውስጥ የተለየ ስሜት የፈጠረና ሁሉም ነጋዴ የያዘው መፅሃፍ ነው፡፡” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ሌሎች መፃህፍት የራሳቸው አንባቢ አላቸው፤ ይሄኛው ግን ወጣት አዛውንት ሳይል በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የጠየቁትና የገዙት መፅሃፍ ነው፡፡” ሲልም አክሏል አከፋፋዩ፡፡
“ይህች መጽሐፍ ጉዞ ቀመስ፣ ፖለቲካ ቀመስና ታሪክ ቀመስ መጣጥፎችን ይዛለች” በሚል ደራሲው በመግቢያው የገለፀው ይኸው መጽሐፍ፤ በ70 ብር ነው ለገበያ የቀረበው፡፡
የመፅሃፉ ደራሲ በዕውቀቱ ስዩም በአሜሪካ ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡   

Read 3033 times