Saturday, 06 February 2016 11:15

‹ሞቷን የምትጠብቅ ከተማ›› እናት መሬት ብዙ አትታወቅም

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

    ከመሬት ጋር ስሽከረከር ሰነበትኩ፡፡ ተሽከርክሬ - ተሽከርክሬ ብዙ ያወቅኩት ነገር የለም፡፡ ለጋዜጣ የሚሆን ወሬ ግን አላጣሁም፡፡ የዛሬ ሣምንት እንዳልኩት፤ ‹‹ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት፤ በዓለም ውስጥ እጅግ የረቀቀ ሳይንቲስት የሚባለው ሰው፤ ስለ ከርሰ ምድር የነበረው ዕውቀት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡››ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩት ሳይንቲስቶች፤ ዛሬ አንድ የከሰል ማዕድን ቆፋሪ ከሚያውቀው ነገር የተሻለ ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡
የዛሬውን ጨዋታ፤ እንደ ጆግራፊ መምህር፤ ‹‹መሬት ሦስት ክፍሎች አሏት›› ብዬ ልጀምር፡፡ ሦስት ክፍሎች፤ ‹‹ክረስት››፣ ‹‹ማንትል›› እና ‹‹ኮር›› ናቸው፡፡ ከ0 እስከ 45 ኪ.ሜ የሚገኘው የመሬት ክፍል ‹‹ክረስት›› ነው፡፡ ቀጣዩ ‹‹ማንትል›› ነው፡፡ ‹‹ማንትል›› ራሱ ሦስት ቀጣና አለው። ‹‹ላይኛው››፣ ‹‹መሸጋገሪያው›› እና ‹‹ታችኛው›› ማንትል ተብለው ይከፈላሉ፡፡ ስለዚህ ከ45 ኪ.ሜ እስከ 400 ኪ.ሜትር ያለው ላይኛው ‹‹ማንትል›› ነው፡፡ ከ400 እስከ 650 ኪ.ሜ ድረስ ያለው፤ መሸጋገሪያ የሚሉት ክፍል ነው። ከ650 እስከ 2ሺህ 700 ኪ.ሜ ያለው ታችኛው ‹‹ማንትል›› ነው፡፡ ከ2ሺህ 700 እስከ 2ሺህ 890 ኪ.ሜ ያለው ‹‹ዲ ሌየር›› (“D” Layer) የሚሉት ክፍል ነው፡፡
ቀጥሎ የሚመጣው ‹‹ኮር›› ነው፡፡ ‹‹ኮር›› በሁለት ይከፈላል፡፡ ‹‹ውጫዊው ኮር›› እና ‹‹ውስጣዊው ኮር›› በሚል ይከፍሉታል፡፡ ስለዚህ፤ ከ2ሺህ 890 እስከ 5ሺህ 150 ድረስ ያለው ‹‹ውጫዊው ኮር›› ሲሆን፤ 5ሺህ 150 እስከ 6ሺህ 378 ያለው ‹‹ውስጣዊው ኮር›› ነው፡፡
ከርሰ ምድርን ማየት ባለመቻላችን፤ የመሬትን ውስጣዊ ሁኔታ ለማወቅ ሌሎች ዘዴዎችን እንጠቀማለን። ይህም ሞገዶችን የማንበብ ዘዴ ነው። ሞገዶች በከርሰ ምድር ውስጥ ማለፍ ይችላሉ። ስለዚህ፤ አሁን ስለ ከርሰ ምድር ያለን ዕውቀት ሞገዶችን በማንበብ የተገኘ ዕውቀት ነው፡፡
አር. ዲ. ኦልድሃም (R. D. Oldham) የተባለ የአየርላንድ ዜጋ፤ እኤአ በ1906 ዓ.ም፤ በጓቲማላ የተከሰተን የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያሳይ ‹‹ሲስሞግራፍ›› (Seismograph) ሲያነብብ፤ አንዳንዶቹ የመሬት መንቀጥቀጥ ሞገዶች ወደ ጥልቁ የመሬት እምብርት ዘልቀው እንደሚገቡና፤ የሆነ አንጥሮ የሚመልስ ነገር እንደሚገጥማቸው ዓይነት፤ ሞገዶቹ በሆነ አንግል እንደ ኳስ ነጥረው የሚመለሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ግራፍ ተመለከተ።
ከዚህ በመነሳት መሬት ‹‹ኮር›› ያላት መሆኑን ደመደመ፡፡ ይህ በሆነ በሦስተኛው ዓመት አንድሪጃ ሞሆሮቪቺች (AndrijaMohorovičić) የተባለ አንድ የክሮሺያ‹‹ሴስሞሎጂስት››፤ በዛግሬብ አካባቢ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥን የሚያመልክት ግራፍ እየተመለከተ ሳለ፤ ተመሳሳይ የሆነ (ነገር ግን ቀደም ሲል ከታየው ጥልቀት ያለው) እንግዳ የሆነ የሞገድ መቀልበስ (Deflection) ሁኔታን ተመለከተ፡፡
በዚህም፤ ‹‹ክረስት›› (Crust) በመባል በሚታወቀው ንብብር የመሬት አካልና ቀጥሎ በሚመጣው ሌላ የመሬት ንብብር አካል መካከል ድንበር መኖሩን ተመለከተ፡፡ ይህም ድንበር ‹‹ማንትል›› (Mantle) በሚል የሚታወቀው የመሬት አካል ነው፡፡ ይህ የመሬት አካል፤ ‹‹የሞሆሮቪቺች ኢ-ተለጣጣቂነት›› (Mohorovičić Discontinuity) ወይም በአጭሩ የ‹‹ሞሆ ኢ-ተለጣጣቂነት›› በሚል የሚታወቅ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ዕውቀቱ ከጭላንጭል ከፍ ያለ ነገር ባይሆንም፤ ሳይንቲስቶች ስለ መሬት ውስጣዊ ንብብር አካል የተወሰኑ ዕውቀቶች መገኘት ቀጠሉ፡፡ ሆኖም፤የተለየ ነገር የተፈጠረው በ1936 ዓ.ም (እኤአ) ነበር፡፡
በ1936 ዓ.ም (እኤአ)፤ኢንጅ ሌህማን (Inge Lehmann) የተባለ አንድ የዴን ማርክ ሳይንቲስት፤ በኒውዝላንድ የተከሰተን የመሬት መንቀጥቀጥ ግራፍ ሲያጠና፤ መሬት ሁለት ኮር እንዳላት ተረዳ። ‹‹ውስጣዊ ኮር›› እና ‹‹ውጫዊ ኮር›› የሚባሉ የመሬት አካል ክፍሎች መኖራቸውን ለየ፡፡ ታዲያ ‹‹ውስጣዊው ኮር›› ጠጣር እንደመሆነ ይታመናል፡፡ ነገር ግን ‹‹ውጫዊው ኮር›› (ይህ ኦልድሃም ያገኘው ነው) ፈሳሽና የማግኔት ኃይል ማህደር እንደሆነ ይታሰባል፡፡
ታዲያ ኢንጅ ሌህማን (Inge Lehmann)፤በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ የሚከሰተውን ሞገድ (Seismic waves) በማጥናት ስለ መሬት እምብርት ያለንን ዕውቀት ለማጥራት ይታገል በነበረበት ወቅት፤ በካሊፎርንያ የሚገኙ ሁለት ሳይንቲስቶች ተከታትለው በሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት ለማነጻጸር የሚያስችል ዘዴ ለማግኘት ጥናት ያደርጉ ነበር፡፡
እነዚህ ሳይንቲስቶች ቻርልስ ሬክተር (Charles Richter) እና ቤኖ ጉተንበርግ (Beno Gutenberg) ናቸው፡፡ ሆኖም የፍትህን ዓይን በሚያጠፋ አኳኋን የመሬት መንቀጥቀጥ መጠን መለኪያ ምድቡ ‹‹የሬክትር ስኬል›› እየተባለ ሲጠራ ያሳዝናል። በእርግጥ፤ ይህን ያደረገው ሬክተር አይደለም። እንደውም ሬክተር ትሁት ሰው ነው፡፡ ስለዚህ፤ ስኬሉን ‹‹ሬክትር›› በሚል ጠቅሶት አያውቅም ይላሉ፡፡ ሰዎች ‹‹የሬከረተር ስኬል›› ይበሉት እንጂ፤ እርሱ ሁልጊዜም‹‹ማግኒቲዩድ ስኬል›› (Magnitude Scale) ነው የሚለው፡፡
ታዲያ በተለይ መጀመሪያ ግድም ‹‹የሬክትር ስኬል›› የሚለው አጠራር ሳይንቲስት ባልሆኑ ሰዎች የተዛባ አስተሳሰብ ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ችግር አሁን አሁን ሳይሻሻል አይቀርም እንጂ፤ ‹‹የሬክተር ስኬል›› የሚለውን መለኪያ ምድብ የሰሙና ወደ ቻርልስ ሬክተር ቢሮ ጎራ ይሉ የነበሩ ሰዎች ሁሉ፤ አንድ የመሬት መንቀጥቀጥን ለመለካት የሚያገለግል መኪና ለማየት እያሰቡ ነበር ወደ ሬክትር የሚሄዱት።
ነገር ግን፤ የመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ ሚዛን፤ ቁስ አይደለም፡፡ ይልቅስ ሐሳብ ነው፡፡ በመሬት ገጽ ላይ የሚፈጠርን እርግብግቢት ወይም ንዝረት በመለካት ላይ የተመሠረተ ልኬት ነው፡፡ እንዲያውም አለካኩ ‹‹ዘፈቀዳዊ›› ነገር የሚታይበት ነው፡፡ ለምሣሌ፤ ‹‹በሬክትር ስኬል›› ሲለካ 7 ነጥብ 3 ተለካ የተባለ የመሬት ርደት፤ 6 ነጥብ 3 ከተለካ ርደት በሐምሳ በመቶ የላቀ ኃይል ያለው ርዕደ መሬት ነው፡፡ ‹‹በሬክትር ስኬል›› 5 ነጥብ 3 ከተለካው ደግሞ 2ሺህ 500 ጊዜ ብልጫ ያለው ርደት ይሆናል። ይህ ነው ‹‹ዘፈቀዳዊ›› የመሰለ ነገር የሚፈጥረው። ‹‹ቲዮረቲካሊ›› ለርዕደ መሬት ከፍተኛ ጣሪያ ተብሎ ሊቀመጥ የሚችል ነገር የለም ይላሉ ሳይንቲስቶች። በተመሳሳይ  ዝቅተኛ የሚባል ድንበርም የለም፡፡
የ‹‹ሬክተር ስኬል›› የሚለካው ወይም የሚያመለክተው የርዕደቱን ኃይል እንጂ የጉዳቱን መጠን አይደለም፡፡ ለምሣሌ፤ ከመሬት ገጽ 644 ኪ.ሜ ወደ ከርስ ገብተን በምናገኘውና ‹‹ማንትል›› በሚል በምንጠራው የመሬት ቀጣና የሚፈጠር፤ ርደቱ 7 ሬክተር የሚለካ የመሬት ርደት፤ የንዝረቱ መጠን ከፍተኛ ሊባል የሚችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በመሬት ገጽ ላይ የሚታይ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም፡፡
በተቃራኒው፤ ከመሬት ገጽ ስድስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ የተከሰተና በሬክተር ስኬል ሲለካ በጣም ዝቅተኛ ሊባል የሚችል የመሬት ርዕደት፤ መጠነ ሰፊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ‹‹ከስኬሉ›› ይልቅ፤ የጉዳቱ መጠን ይበልጥ የሚወሰነው፤ የአፈሩ ይዞታ፣ የርዕደቱ ቆይታ፣ የድግግሞሹ መጠን፤ እንዲሁም ዋናውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትለው የሚመጡት ርዕደቶች (Aftershocks) እና ርዕደቱ የተከሰተበት አካባቢ መልክዐ ምድራዊ ገጽታ ነው። እርግጥ፤ ኃይል ትርጉም የሌለው ነገር አይደለም። ነገር ግን፤ በጣም አደገኛው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በሬክተር ስኬል በጣም ኃይለኛ ሊባል የሚችለው ርዕደት አይደለም፡፡
በዓለም ላይ የተለያዩ የሬክተር ስኬል መዝጋቢ ማዕከላት አሉ፡፡ በአላስካ የሚገኘውና በቺሊ የሰላማዊ ውቂያኖስ ዳርቻ የሚገኙት ማዕከላት ተጠቃሽ ናቸው። ሆኖም፤ የመሬት ርደት ልኬት ወይም ምዝገባ ሳይንስ እንከን የለሽ ትክክለኝነት የሚታበት አይደለም፡፡ በተለይ ሩቅ ሥፍራ ባለ ማዕከል የተመዘገበ ልኬትን በማንበብ ላይ የተመሰረተ ንባብ ሲሆን ችግር አያጣውም፡፡
ታዲያ ‹‹የሬክተር ስኬል›› ልኬት ከተፈጠረ ወዲህ፤ በአላስካው ማዕከል የተመዘገበው ከፍተኛው ርዕደት 9 ነጥብ 2 (በማርች 1964) ሲሆን፤ በቺሊው ማዕከል የተመዘገበው (በ1960 ዓ.ም) 9 ነጥብ 5 ነው፡፡ በተለያየ ዘመን የተመዘገቡት እነዚህ ሁለት ርዕደቶች እጅግ ከፍተኛ ሊባሉ የሚችሉ ርደቶች ናቸው፡፡
ክፍ ብሎ የተጠቀሰው የ1960 የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በደቡብ አሜሪካ ሰፊ ውድመት ያስከተለ ርደት ብቻ ሳይሆን፤ በሰላማዊ ውቂያኖስ ላይ 9ሺህ 654 ኪ.ሜ ተምዘግዝጎ፤ እንደ ሃዋይ ያሉ ከተሞችን በጥፊ መትቶ፤ አምስት መቶ ህንጻዎችን ያፈራረሰና 60 ሰዎችን የገደለ ሱናሚን ያስነሳ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ሞገዱ ጃፓንና ፊሊፒንስ ድረስ ተስፈንጥሮ ጉዳት ለማድረስ የቻለ ሱናሚን የቀሰቀሰ ርዕደት ነበር፡፡
ከጉዳት አንፃር፤ በታሪክ ተመዝግቦ ያለው እጅግ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 1፣ 1775 ዓ.ም በፖርቹጋል ዋና ከተማ በሊዝቦን የተከሰተው ነው። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊዝቦን ወደ ቁርጥራጭ ወረቀትነት የቀየረ ክስተት ነበር፡፡ በ1775 ዓ.ም ከጧቱ አራት ሰዓት በሊዝቦን ከተማ የተከሰተው ርደት ከተማይቱን እንደ ሰፌድ አነፈሳት። ‹‹በሬክተር ስኬል›› 9 ነጥብ 0 የተገመተውና ሊዝቦን ለሰባት ደቂቃ በጭካኔ የናጣት ርደት፤ በሰፌድ እንደተነፈሰ እህል ከተማይቱ ወደብ ያነሳውን የባህር ውሃ ሐምሳ ጫማ 15 ያህል (5ሜትር ገደማ) ሽቅብ በማጎን በከተማይቱ ላይ ከነበለው፡፡ ይህም በወቅቱ የደረሰውን አደጋ አክፍቶት ነበር፡፡
ለሰባት ሰዓታት የቆየው ‹‹አቦሉ›› የመሬት ርዕደት አልፎ፤ ለሦስት ደቂቃ ዕድሜ ብቻ ፋታ ያገኙት የሊዝቦን ከተማዋ ነዋሪዎች፤ በ‹‹ቶናው›› ርዕደት እንደገና አንቀረቀባቸው። ከዚያም ከሁለት ሰዓታት በኋላ ‹‹በረካው›› ወይም በመጨረሻው ርዕደት መሬትን ቁና አደረገባቸው፡፡ በዚህ ክፉ ርዕደት 60 ሺህ ሰዎች አለቁ፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ህንፃዎች ሁሉ ወደ ፍርስራሽ ተቀየሩ። ከዚህ ሌላ፤ በ1906 ዓ.ም የተከሰተውና የፍራንሲስኮ ከተማን የመታው ርዕደት በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 የተለካ ሲሆን፤ ከሰላሣ ሰከንድ ላነሰ ጊዜ የቆየ ከፍተኛው ርዕደት ነበር፡፡
በነገራችን ላይ የመሬት ርደት ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነገር ነው፡፡ ሳንቲስቶቹ እንደሚሉት፤ በዓለም ውስጥ በአማካይ በየዕለቱ አንድ ቦታ ላይ በሬክተር ስኬል 2 ነጥብ 0 ወይም ከዚያ ትንሽ ከፍ ያለ ርዕደት ይከሰታል፡፡ ይህ የርደት መጠን ርዕደቱ በተከሰተበት ሥፍራ በአቅራቢያ የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ በመጠኑ ለማንገራገጭ የሚችል ኃይል ያለው ነው፡፡
የመሬት ርደት በተወሰኑ አካባቢዎች፣በአብዛኛው የሰላማዊ ውቂያኖስ ከንፈርን ይዞ- የመከማቸት ዝንባሌ ያለው ቢሆንም፤ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሊከሰት ይችላል፡፡ ለምሣሌ፤ በአሜሪካ የመሬት መንቀጥቀጥ ጨርሶ አይነካቸውም ተብለው የሚታሰቡት አካባቢዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ በመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ የሚጠቁ ቦታዎች አሉ፡፡ ፍሎሪዳ፣ ምሥራቃዊ ቴክሳስና የአፐርሚድ ዌስት ግዛቶች በርዕደት የማይጠቁ የሚባሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በተቃራኒው፤ ኒው ኢግላንድ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 0 በተለኩ ሁለት ርደቶች ተመትቷል፡፡ ይህ አካባቢ (በኒው ዮርክ እና ቬርሞንት የጋራ ድንበር አካባቢ በቻምፕሌን ሐይቅ ግድም) በ2002 ዓ.ም ስዕልን ከግድግዳ፣ ልጆችን ከአልጋ ማውረድ የቻለ፤ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 1 በተለካ ርዕደት ተመትቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ነበር፡፡
የመሬት ርዕደት በተደጋጋሚ የሚከሰተው ሁለት ተገፋፊ የመሬት ሻኛዎች (ፕሌቶች) ሲገናኙ ነው፡፡ ሁለቱ ሻኛዎች እርስ በእርስ እየተገፋፉ፤ በመጨረሻ አንደኛው ‹‹ሻኛ›› አሸናፊ እስኪሆን ድረስ ኃይሉ እየጨመረ ይሄድና ከፍተኛ ግፊት ይፈጠራል፡፡ ከዚያም ርዕደቱ ይከተላል፡፡
ታዲያ፤ በሁለት የርዕደት ክስተቶች መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት ሰፊ በሆነ መጠን፤ የግፊቱ ኃይል ከፍተኛ ይሆናል። በዚያው ልክ ከፍተኛ መንገራገጭ የመፈጠር ዕድሉ ሰፊ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለ የመሬት ርደት ከሚያሰጋቸው የዓለማችን ከተሞች መካከል ግንባር ቀደሟ የጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ ነች፡፡ ‹‹የሎንዶን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ›› የአደጋ ስፔሻሊስቱ፤ ቢል ማክጊዮሪ (Bill MacGuire)፤ ‹‹ሞቷን የምትጠብቅ ከተማ›› ሲል የሚገልጻት ቶኪዮ ነች፡፡ ቶኪዮ ሦስት ‹‹ቴክቶኒካዊ›› የርዕደት ጋሻዎች ከሚደናበሩበት አካባቢ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡
የቶክዮ አካባቢ የአደጋ ቀጣና ነው፡፡ ለምሣሌ፤ በ1995 ዓ.ም (እኤአ) ከቶኪዮ ከተማ በስተምዕራብ በ482 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ኮቤ (Kobe) የተባለች ከተማ፤በሬክትር ስኬል 7 ነጥብ 2 በተለካ የመሬት ርዕደት ተመትታ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ አደጋ 6ሺህ 394 ሰዎች ለሞት ተዳርገው ነበር፡፡ ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ 99 ቢሊየን ዶላር የተገመተ የንብረት ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ ቶኪዮን ከሚጠብቃት አደጋ ጋር ሲነፃፀር ይህ አደጋ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
አዎ፤ ቶኪዮን የሚጠብቃት አደጋ የከፋ ነው። ሆኖም፤ በሃያኛው ክፍለ ዘመን (ሴፕቴምበር 1፣ 1923 ዓ.ም እኤአ)፤ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ ርዕደት አስተናግዳለች፡፡ በተጠቀሰው ዕለት ተሲያቱ ግድም በተከሰተና የ‹‹ታላቁ ካንቶ ርደት›› በሚል በሚታወቅ ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመትታ ነበር፡፡ የ‹‹ታላቁ ካንቶ የመሬት ርደት››፤ ኮቤን ከመታት ርዕደት አስር እጅ የበለጠ ሲሆን፤ 200 ሺህ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ርዕደት ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ቶኪዮ ውስጥ ውስጡን እየነፈረች በፀጥታ መኖር ቀጥላለች። ሆኖም ውጥረቱ ለ80 ዓመታት እየበሰለ ነው፡፡ ይህ ውጥረት አንድ ቀን መፈንዳቱ አይቀርም፡፡
በ1923 ዓ.ም ቶኪዮ የ3 ሚሊየን ገደማ ነዋሪዎች ከተማ ነበረች፡፡ አሁን 30 ሚሊየን የደረሰ ህዝብ መኖሪያ ከተማ ነች፡፡ ቶኪዮን ሊመታት በሚችለው ርዕደት ምን ያህል ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ ለመገመት ከባድ ቢሆንም፤ ርዕደቱ ሊያስከትል የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ግን 7 ትሪሊየን፤ (ይህን ቁጥር ዛሬ ገና ፃፍኩት)፤ ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ባለሙያዎች በ‹‹ፕሌቶች›› (በመሬት ጋሻዎች) መገፋፋት ይፈጠራል ከሚሉት ርዕደት የተለየ እና አልፎ አልፎ የሚከሰት ሌላ የርዕደት አይነት አለ፡፡ ‹‹በመሬት ሻኛዎች ርግጫ›› ከሚነሳው ርዕደት በተለየ፤ ባለሙያዎች ‹‹Intra-plate Quakes›› የሚሉት የመሬት መንቀጥቀጥ አለ። ይህ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ዓይነት አይደለም። ‹‹Intra-plate Quakes››፤ የመሬት ሻኛዎች ርግጫ ከሚካሄድበት ድንበር ራቅ ባለ ሥፍራ የሚከሰት ርዕደት ነው፡፡ አስቀድሞ ለመተንበይ የማይቻል ዓይነት ርዕደት ነው፡፡
ይህ ርዕደት የሚነሳው ከጥልቅ የመሬት ከርስ በመሆኑ፤ በጣም ሰፊ አካባቢን የሚሸፍን የመሬት መንቀጥቀጥን የሚያስከትል ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ርዕደት በጣም የከፋ የሚባለው፤ በ1811 እና 1812 ዓ.ም (እኤአ) የተከሰቱትና ሚሲዮሪና ኒውማድሪድ የተሰኙ የአሜሪካ ግዛቶችን የመቱ ሦስት ርዕደቶች ናቸው፡፡ ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው በዲሴምበር 16፣ 1811 ዓም እኩለ ሌሊት አለፍ እንዳለ ነበር፡፡ ሰዎች አገር አማን ብለው ተኝተው ነበር። ሆኖም ሌሊቱ እንደተጋመሰ በበረት የነበሩት እንስሳት እየጮሁ መተራመስ ጀመሩ፡፡ ከዚያም ከመሬት ጥልቅ ከርስ በተቀሰቀሰ እጅግ ኃይለኛ ፍንዳታና በእንስሳቱ ጩኸት ወይም ትርምስ የተነሳ፤ እንቅልፍ የወሰዳቸው ሰዎች በድንጋጤ ከመኝታቸው ነቁ፡፡
በነገራችን ላይ፤ ‹‹የመሬት መንቀጥቀጥ ሊመጣ ሲል እንስሳት ይተራመሳሉ›› የሚል አባባል የአሮጊት ወሬ አይደለም፡፡ የተረጋገጠ ሐቅ ነው፡፡ ‹‹ለምን እንዲያ ሆነ›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ባይኖርም ሐቁ የታወቀ ነው፡፡ እናም እንስሳቱ ሲታወኩ ከእንቅልፋቸው የነቁት ሚሲዮሪና የኒው ማድሪድ ነዋሪዎች፤ መሬት እየተናጠች ከመኝታቸው ተነሱ፡፡ መሬት እንደሚራገፍ ጋቢ ሆናለች። በየቦታው ጥልቅ ጉድጓድ እየሰራች፤ አፏን ትከፍታለች፡፡ እንደ ጉድ የሚሰነፍጥ ድኝ አየሩን ሞልቶታል፡፡ ታዲያ ያ ርዕደት ለአራት ደቂቃ የቆየና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ያስከተለ ነበር፡፡
በ1960ዎቹ አካባቢ ሳይንቲስቶች የምድርን እምብርት ብዙ ባለማወቃቸው (በዕውቀታቸው አናሳነት) ይጨነቁ የነበረበት ዘመን ነበር፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ፡፡ የውቂያኖስን ወለል በመቆፈር፤ ‹‹ከሞሆ የኢ-ተለጣጣቂነት›› ቀጣና ድረስ በመዝለቅ፤ ከመሬት ‹‹ማንትል›› ለጥናት የሚያገለግል የዓለት ናሙና ለማውጣት አቀዱ። ሐሳባቸው፤ ‹‹ከማንትል›› የተወሰዱትን የዓለት ናሙና ባሕርይ በማጥናት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተትን በደንብ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ነበር፡፡ስለዚህ፤ ‹‹የሞሆ ጉድጓድ›› በተሰኘ ፕሮጀክት፤ በሜክሲኮ ዳርቻ በሚገኘውና 4ሺህ 267 ሜትር ጥልቀት ካለው የሰላማዊ ውቂያኖስ ወለል ድረስ መቆፈሪያ ማሽን በማውረድ፤ 5ሺህ 181 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር ናሙና ዓለት ለማውጣት አሰቡ፡፡ ቁፋሮ የተጀመረው በአንጻራዊ ሚዛን ዓለቱ ጠንካራ ባልሆነበት አካባቢ ነበር፡፡ ሆኖም፤ በውሃ ላይ ከሚንሳፈፍ መርከብ ላይ ሆኖ መሬትን ለመቆፈር ማሰብ፤ ‹‹ኒው ዮርክ ከሚገኝ አንድ ህንፃ ላይ ወጥቶ በፓስታ ዘንግ ጎዳናውን ለመቆፈር ከመሞከር የተለየ ነገር አይደለም›› የሚል ትችትን የጋበዘ ፕሮጀክት ነበር፡፡ እንደተባለውም፤ ሁሉም ሙከራዎች ከሸፉ። ‹‹የሞሆ ጉድጓድ›› በተሰኘው ፕሮጀክት፤ ለመቆፈር የቻሉት 183 ሜትር ያህል ጉድጓድ ነበር፡፡ ስለዚህ አንዳንዶች ‹‹ሞ ሆል›› የተሰኘውን ፕሮጀክት፤‹‹ኖ ሆል›› በሚል ይጠሩታል፡፡ በመጨረሻም፤ በየጊዜው እየጨመረ በመጣው የቁፋሮ ዋጋና ውጤት አልባ በሆነው ጥረት፣ ተስፋ የቆረጠው የአሜሪካ ኮንግረስ በፕሮጀክቱ ላይ ሞት ፈረደበት፡፡
ከአራት አመታት በኋላ ሩሲያ ሌላ ሙከራ ለማድረግ ወሰነች፡፡ የእርሷ ሙከራ በውቂያኖስ ላይ አልነበረም።  ሩሲያ ለመቆፈር የወሰነችው፤ ወደ ፊንላንድ ድንበር ጠጋ ብሎ በሚገኘው ‹‹የኮላ ሰላጤ›› አካባቢ ካለ አንድ ሥፍራ ነው፡፡ ሩሲያ 15 ኪሎ ሜትር ለመቆፈር አስባ ተነሳች። ግን ሥራው ከታሰበው በላይ ከባድ ሆኖ ተገኘ፡፡ ይሁንና ሶቬቶች በቀላሉ እጅ አልሰጡም፡፡ ለአስራ ዘጠኝ ዓመታት ሙከራው ቀጠለ። ከዚያ በኋላ ታከታቸውና ተዉት፡፡ ታዲያ ይህ የሩሲያ ፕሮጀክት በተቋረጠ ጊዜ፤ 12 ሺህ 262 ሜትር ያህል መቆፈር ተችሎ ነበር፡፡
‹‹ክረስት›› የሚሉት የመሬት ክፍል፤ ከጠቅላላ የመሬት አካል ድርሻው 0ነጥብ3 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ሩሲያ ‹‹በኮላ ፕሮጀክት›› 12 ኪሎ ሜትር ግድም ስትቆፍር፤ ‹‹ክረስት›› ከሚባለው የመሬት ክፍል አንድ-ሦስተኛውን ያህል እንኳ መቆፈር እንዳልቻለች ግልፅ ነው፡፡
ታዲያ የሩሲያ ጉድጓድ ብዙም ጥልቅ ባይሆንም፤ የ‹‹ሴሲሚክ ሞገድ››ን በማጥናት በርካታ ነገሮችን ለመገመት የሚያስችል ዕድልን ፈጥሯል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ አስተሳሰቦችን የቀየሩ መላ ምቶችን ለመደንገግ አስችሏል፡፡ ከመሬት ጋር ይህን ያህል ተሽከርክረን የምናርፈው ‹‹ስለ ከርሰ ምደር ያለን ዕውቀት አሁንም ትንሽ ነው›› ከሚል ወደብ ነው። ቸር ሳምንት!

Read 5784 times