Saturday, 06 February 2016 11:05

ከጅብ ጅማት የተሠራ ክራር ቅኝቱ ልብላው ልብላው ነው

Written by 
Rate this item
(16 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ወደጎረቤት አካባቢ ያለችን አንዲትን ለአቅመ - ሔዋን የደረሰች ኮረዳ ለወንድ ልጃቸው ፈለጓትና ሽማግሌዎች ወደልጅቷ ቤተሰቦች ተላኩ።
ሽማግሌዎቹ የልጅቱ ቤተሰቦች ዘንድ ሲደርሱ፣ ቤት ገብተው ቆሙ፡፡ የልጅቱ ቤተሰቦችና ዘመድ - አዝማድ ሁሉ በአንድ ተርታ ተሰድረዋል፡፡
አባት፤
“እህስ፤ ምን አግር ጣላችሁ ጎበዝ?”
ከሽማግሌዎቹ አንዱ፤
“ምን የመሰለ ለአቅመ - አዳም የደረሰ ጎበዝ ወንድ ልጅ አለን፡፡ ልጃችሁን ለልጃችን ትሰጡን ዘንድ ይኸው ከወዲያኛው አምባ መጥተናል” ሲሉ መለሱ፡፡
አባት፤
እንደዚህ ከሆነማ፣ እኛ እምቢ የምንልበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ግን አንድ ቅድመ - ሁኔታ ማሟላት አለባችሁ”
“ምን?”
የልጅቷ ወላጆችም፤ “እንግዲያው በጥሞና አዳምጡን፡፡ ልጃችንን የምንሰጣችሁ ሃምሳ ሰው ይዛችሁ መጥታችሁ 1ኛ/ ሃምሳ በግ ቀርቦላችሁ የምትበሉ ከሆነ
         2ኛ/ ሃምሳ ጋን ጠላ የምትጠጡ ከሆነ
     3ኛ/ መላ የሚያውቅ ሰው፣ ግን መላጣ ያልሆነ ሰው ይዛችሁ ከመጣችሁ  ነው፤” አሉ
 የወንዱ ልጅ ወገኖች፤
“ሀሳቡን እንቀበላለን፡፡ ያላችሁትን 50 ሰው ይዘን እንመጣለን” ሲሉ ሀሳቡን መቀበላቸውን አረጋገጡ።
“እንግዲህ ከቆረጣችሁ የዛሬ 15 ቀን ኑ” አሉና ቀጠሯቸው፡፡
በቀጠሮው ቀን ሽማግሌዎቹ 50 ሆነው መጡ፡፡ 50 በጎች ቀረቡላቸው፡፡ እንዳጋጣሚ ይዘውት የመጡት መላ አዋቂ ሰው መላጣ ነው፡፡ “እንዴት እናድርግ መላጣ አይግባብን ብለዋል?” ብለው ጠየቁት፡፡
“ጥምጥም አምጡ፡፡ ቄስ ሆኜ እገባለሁ፡፡ ቄስ አይግባ አላሉ!” አለ፡፡
“የቀረቡትን በጎች እንዴት እንብላቸው?” አሉት፡፡
“አንድ በአንድ እየተረከባችሁ ለ50 ሰው ጥሬውን መቀራመት ነው” አላቸው፡፡
መላ አዋቂው እንዳለው አንድ አንድ በግ እየተቀበሉ ከጋኖቹ ጠላ እየቀዱ እያማጉ ጥብስቅ አድርገው በሉና ጠላውን ግጥም አድርገው ጠጡ፡፡
የሙሽሪት ቤተሰቦች አይሆንም ያሉት ነገር ሆነና ተሸነፉ፡፡ የግዳቸውን ልጃቸውን ለማስረከብ ተስማሙ፡፡ የወንድ ወገን “ሃይ ሎጋ!” አለ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሴት ወገን በኩል ለወንድ ወገን አካባቢ ሰዎች ስም ወጣላቸው፡፡ ለምን ቢሉ፣ ልብ ብሎ ላያቸው ጥሬውን ሲበሉ ነው የታዩት፡፡ ቢጠብሱት ኖሮ ቅባቱ ይዘጋቸው ነበር፡፡ ይሄን ተመርኩዞ፤
“አይጠብሴ” የሚል የቅፅል ስም ወጣላቸው፡፡
*          *         *
ሌሎችን አሸንፍበታለሁ ያልነው ዘዴ አንዳንዴ መሸነፊያችን ሊሆን ይችላል፡፡ በርካታ ህዝብ ዘክሮ መክሮ የሚያመጣው ብልሃት አይታወቅም፡፡ ዋናው ነገር የሚዘክር የሚመክረውን ህዝብ መሰባሰብ፣ መምረጥና ማደራጀት መቻል ነው፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የተበታተነ የህዝብ ሐተታ እንጂ የሰከነ ዕምነት ማፍራት አንችልም፡፡ የአስተሳሰብ አንድነት የዛሬ የሀገር ጥሪ ነው!
በጋራ አስቦ፣ በጋራ ተስማምቶ የጋራ ዓላማ መያዝ እጅግ ከባድ ተልዕኮ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ጠጣት ሰናይ ተግባር ስም የሚያስጠራ ምግባር ያስፈልጋል፡፡ ፀሐፍት፤ “ያለጥርጥር መልካም ሥራህ ካንተ ቀድሞ ይታወቃል፡፡ ክብርን ያመለካተ ከሆነ አንተ ወደ መድረኩ ትርዒት ሳትደርስ በፊት ብዙው ሥራህ ተከናውኖ ጠበቀህ ማለት ነው፡፡ አንዲት ቃል ሳትተነፍስ ጉዳይህ አለቀ” ይላሉ፡፡
ስለመልካምም ሆነ እኩይ ምግባር የማሳወቅ ታላቅ ኃላፊነት ያለባቸው ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ምንም ዋጋ ያስከፍላቸው የፈጠጠውን እውነት መራቅ የለባቸውም፡፡ በእርግጥ መንግሥትም ይህን ሀቅ ተገንዝቦ ሊያግዛቸው እንጂ ሊያስፈራራቸው አይገባም፡፡ እንደ ሙስና ያሉት መያዣ መጨበጫ ያጡ ድርጊቶች በሁሎች ርብርብ የሚጋለጡ መሆናቸውን አለመርሳት ነው፡፡
በሀገራችን የሚታየውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስናይ ኃምሌት ይከሰታል፡-
“…ኋላ ምን ሊታየኝ ኖሯል፣ ጊዜ ከፈተነው ሌላ
ምድር ዕፅዋት ብቻ አታበቅል፣ ያለሾህ ያላሜከላ
ወይንም የተፈጥሮ መልክ፣ ሲካበት ሞልቶ ድርጅቶ ብቻውን አደለም ከቶ
ግን እንደዚሁ እንደ ህንፃ፣ ላዩ በሰም አንፀባርቆ
አካባቢው በጌጥ ደምቆ
መሰረቱ ግን በግድፈት፣ በአገም ጠቀም ተደባብቆ
በመሀንዲስ ጥበብ ጉድለት፣ ወይ ባጉል መራቀቅ ዘፍቆ
ከስህተቱም፣ ከጥራቱም፣ ተቻችሎ፣ አለ ተጣብቆ”
ህንፃው ብቻውን ባዶ ነው፡፡ መሰረቱ የተዛባ ነው፡፡ መሀንዲሱ ስራውን በአገም - ጠቀም ሰርቶ አሳቡን ከወሰደ ቆይቷል፡፡ አካባቢያችን ጌጥ ብቻ ነው! እሾህና አሜከላ ዙሪያችንን ከቦናል፡፡ ይሄ የሀገራችን ሀቅ ነው፡፡ ማማር ያለበት መንገድ፣ ህንፃው፣ ሪል ኢስቴቱ ብቻ አይደለም፡፡ ዋናውና ዋነኛው የህዝባችን ኑሮ ነው፡፡ ተመችቶኛል፣ ደልቶኛል ማለት ያበት ነዋሪው ህዝብ ነው! በግፍ ተበልቻለሁ፣ ተመዝብሬአለሁ ማለትም ያለበት ነዋሪው ህዝብ ነው፡፡ በሹመት ስም፣ በሀገር ሰላም ስም፣ በትራንስፎርሜሽን ስም፣ በኢንቬስተሮች ማበረታታት ስም፣ ዘራፊዎችን በማሳደድ ስም፣ … የሚካሄዱ ምዝበራዎችን አውቆ፣ ነቅቶ፣ ከሥር መሰረቱ አብጠልጥሎ ተረድቶ፣ ማጋለጥና ዕውነቱን ይፋ ማድረግም የነዋሪው ህዝብ ደንታ ነው፡፡ በፋይናንስ፣ በገቢ አሰባሰብና የመሬት ቁጥጥር ጉዳይ ላይ ህዝብ የመናገር መብት ሊኖረው ይገባል!! የመክሰስ መብቱን ሊጠቀም ይገባል!
በሥልጣን ብልግናም ይገለጥ፣ በመሬት ዘረፋም ይገለጥ፣ በታክስ ማጭበርበርም ይገለጥ፣ በኮንስትራክሽን ግዢም ይገለጥ፣ በሚዲያ ኢንዱስትሪ ሀሳዊ - ስብከትም ይገለጥ፣ የቦርድ አባልነትን ተገን በማድረግም ይገለጥ፣ በሙልሙል ቢሮክራት መልክም ይገለጥ … “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው ልብላው ነው” በሚለው ተረት በሚገባ የሚንፀባረቅ ነው፡፡ ይህንን ልብ ለማለት ልብ ይስጠን!!

Read 7875 times