Saturday, 06 February 2016 10:58

የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ነገ ወደ ቦታው ይመለሣል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

የሐውልቱ ሥፍራ 6.5 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል
- ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት`በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይተውናል
   ከሦስት ዓመት በፊት ከባቡር ፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ተተክሎ ከነበረበት ሥፍራ መነሳቱን ተከትሎ ውዝግብ ያስነሳው የታላቁ አርበኛ የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት፤ ነገ ረፋድ ላይ ከብሄራዊ ሙዚየም ወጥቶ በቀድሞ ሥፍራው ላይ ይተከላል፡፡
የሃውልቱ ጉዳይ አብይ ኮሚቴ አባላት፡- የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢ/ር ጌታቸው በትሩ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዳይሬክተር ኢ/ር ፍቃደ ሃይሉና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻ፤ ትናንት ለጋዜጠኞች በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ሃውልቱ በነገው ዕለት በታላቅ ክብር በፖሊስ ማርሽ ቡድን ታጅቦ ወደ ቦታው ይመለሳል ብለዋል፡፡
ጠዋት ከ3 ሰዓት ጀምሮ ሃውልቱን ከብሔራዊ ሙዚየም ወደ ጊዮርጊስ አደባባይ የማጓጓዝ ሥነ ስርዓት የሚከናወን ሲሆን ሃውልቱ በተዘጋጀለት ቦታ የሚቀመጠው አቡኑ መስዋዕትነትን በተቀበሉበት ከረፋዱ 5 ሰዓት ከሩብ ላይ ነው ተብሏል፡፡
ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ሃውልቱ ለህዝብ እይታ የሚገለጥ ሲሆን “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” የተሰኘው የባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ተውኔት ለዚሁ በተዘጋጀው መድረክ ላይ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡
በሥነ - ሥርአቱ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ አባት አርበኞች፣ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች የሚታይ ሲሆን ሥነ ስርዓቱን የፖሊስ ማርሽ ቡድንና የብሄራዊ ቲያትር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በተለያዩ ጥበባዊ ትዕይንቶች ያደምቁታል ተብሏል፡፡
ሃውልቱን ለማፅዳትና ለማደስ እንዲሁም የሚያርፍበትን አደባባይና ተያያዥ መንገዶች ለመስራት 6.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ እንደተደረገበትም ተገልጿል፡፡ ሃውልቱ የሚያርፍበት አደባባይ በሶስት ዙር የተገነባ ሲሆን ዓላማውም ሃውልቱን ከተሽከርካሪ አደጋ ለመከላከል እንደሆነ ታውቋል፡፡
በ1875 ዓ.ም በፊቼ የተወለዱት አቡነ ጴጥሮስ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከተሾሙ 5 ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት አንዱ ሲሆኑ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የነፍስ አባት እንደነበሩና ለ7 ዓመታትም በጵጵስና እንዳገለገሉ ታሪካቸው ይጠቁማል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ለመታሰቢያነት ከቆሙ 14 ታላላቅ ሃውልቶች መካከል በመንገድ ግንባታ ምክንያት ከቆመበት ተነስቶ የነበረው የፑሽኪን ሃውልትም ወደ ቀድሞ ቦታው በሚመለስበት ሁኔታ ላይ ምክክር እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡   

Read 7145 times