Saturday, 06 February 2016 10:55

በኦሮሚያና በጐንደር ግጭቶች ላይ የምርመራ ሪፖርቶች ሊቀርቡ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

በ “ማስተር ፕላን” መነሻነት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን፤ እንዲሁም በጐንደር “የአማራ ተወላጅ፣ የቅማንት ተወላጅ” በሚል የተከሰተውን ሁከት እንደመረመሩ የገለፁ የመንግስት እና ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ የምርመራ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ገለፁ፡፡
መንግስታዊ ተቋሞቹ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የህዝብ እንባ ጠባቂ፤ በጋራ ያካሄዱትን ምርመራ አጠናቅቆው ከሳምንት በኋላ ሪፖርታቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡ መንግስታዊ ያልሆነው ተቋም የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሠመጉ) በበኩሉ፤ በሦስት ሳምንት ውስጥ ለህዝብ ሪፖርት አደርጋለሁ ብሏል፡፡
የመርማሪ ቡድኖችን በመላክ ጥልቅ ምርመራ ተካሂዷል ያሉት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካይ አቶ ብርሃኑ አባዲ፤ በግጭቶቹ የጠፋውን የሰው ህይወትና የደረሰውን የንብረት ጉዳት እስከ ወረዳ ድረስ ተጣርቷል ብለዋል፡፡  
በኦሮሚያ አካባቢዎች የተፈጠረውን ተቃውሞና ግጭት ዙሪያ የምናካሂደውን ምርመራ እያጠናቀቅን ነው ያሉት የሠመጉ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ ወንድሙ፤ እያንዳንዱን ወረዳና የገጠር ቀበሌ ያካተተ ምርመራ በጥንቃቄ አከናውነናል ብለዋል፡፡
የሠመጉ መርማሪዎች የተጐጂ ቤተሰቦችን በማነጋገር፣ ከአይን ምስክሮች ቃል በመቀበል፣ የህክምና ማስረጃዎችን፣ የተለያዩ የፎቶግራፍና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ መርምረዋል ብለዋል - ሃላፊው፡፡
በጐንደር፣ “የአማራ ተወላጅ እና የቅማንት ተወላጅ” በሚል፤ እንዲሁም በወልቃይት አካባቢ፣ “የአማራ ተወላጅ እና የትግራይ ተወላጅ” በሚል በሚቀርቡ ጥያቄዎች  ላይ ምርመራ እንደተጀመረ የገለፁት  አቶ ቡዛየሁ፤ በጋምቤላ የተከሰተውን ግጭት ለማጣራትም መረጃ እየሰበሰብን ነው ብለዋል፡፡ 

Read 11289 times