Saturday, 06 February 2016 10:51

ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱን ወቅታዊ ፈተናዎች የሚዳስስ ዐውደ ርእይ ያዘጋጃል

Written by 
Rate this item
(9 votes)

• ከመቶ ሺሕ በላይ ተመልካቾች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል
• ኦርቶዶክሳዊ ክውን ጥበባት ልዩ ገጽታዎቹ ይኾናሉ ተብሏል
• ለአጠቃላይ ዝግጅቱ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፋዊነት፣ ነባራዊ ሁኔታና ተግዳሮቶች ተረድተው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ያስችላል የተባለ ልዩ ዐውደ ርእይ በመጪው መጋቢት ወር አጋማሽ እንደሚያካሒድ ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ፣ ከመጋቢት 15 - 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚያካሒደው ዐውደ ርእይ፣ ለአምስተኛ ጊዜ የሚያዘጋጀው ሲሆን፣ “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን፡ አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ” የሚል መርሕ እንዳለው የዝግጅቱ ዐቢይ ኮሚቴ ገልጧል፡፡
በዘንድሮው ዐውደ ርእይ፥ ቤተ ክርስቲያን በአደረጃጀቷ የካህናትና የምእመናን ኅብረት መሆኗን በማስገንዘብ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ድርሻቸውን ዐውቀው ሓላፊነታቸውን የሚወጡበትን መንገድ የሚያስገነዝቡ፤ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነትና አንድነት የሚያስረዱ፣ በአራት ሰፋፊ አርእስተ ጉዳዮች የተከፈሉ ትዕይንቶች ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመታገዝ እንደሚቀርቡ ተጠቅሷል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ማንነት፤ በዓለም፣ በአፍሪቃ እና በኢትዮጵያ ያላትን ሐዋርያዊ ተልእኮ፤ ወቅታዊ ተግዳሮቶቿንና መፍትሔውን በመለየት ምን መደረግ እንዳለበትና ከምእመናን ምን እንደሚጠበቅ በስፋትና በዝርዝር ከተካተቱበት ዐውደ ርእይ ጎን ለጎን፣ ጭብጦቹ በጥናታዊ ጽሑፍ የሚዳሰሱበት ዐውደ ጉባኤ እንደሚካሔድም ታውቋል፡፡
ዐውደ ርእዩ ለእይታ ክፍት ኾኖ በሚቆይባቸው ሰባት ቀናት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የጥንታዊ ሥርዐተ ትምህርት የመማር ማስተማር ሒደት በደቀ መዛሙርቱና በመምህራኑ እንቅስቃሴ በተግባር የሚታይበት “የአብነት ት/ቤቶች መንደር” የሚገነባ ሲሆን በየዕለቱ ከ10 ሰዓት በኋላም ያሬዳዊ ዜማና ቅኔ ከትውፊታዊ ዕሴቶቻቸው ጋር የሚቀርቡበት መሰናዶ እንደሚኖር ተገልጧል፡፡ ኮሚቴው፣ “ኦርቶዶክሳዊ ክውን ጥበባት”/performance arts/ ሲል የገለጻቸው መሰናዶዎቹ፥ የጥበባቱን ሕያውነት፣ ገቢራዊነትና አሳታፊነት በማስገንዘብ ተመልካቾችን ለዕውቀት በማነሣሣት ረገድ ጉልሕ ድርሻ| ይኖራቸዋል፤ ብሏል፡፡
ለዐውደ ርእዩና ተጓዳኝ መሰናዶዎች አስፈላጊው ፈቃድና የድጋፍ ደብዳቤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት ተገኝቶ ከኤግዚቢሽን ማእከሉ ጋር ስምምነት መፈጸሙን ዐቢይ ኮሚቴው ገልጦ፤ ከአንድ ሺሕ አባላቱ በዝግጅትና በቴክኒክ ምድቦች ተከፋፍለው ቅድመ ዝግጅታቸውን በማከናወን ላይ እንዳሉና በሒደትም የሰንበት ት/ቤቶችንና ሌሎች መንፈሳውያን ማኅበራትን በአጋርነት በመያዝ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል፡፡
ለአጠቃላይ ዝግጅቱ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ  ወጪ የተያዘለት ሲሆን፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ተቋማት ጨምሮ የተለያዩ አጋር አካላት ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለግብይት በማቅረብ እንደሚያስተዋውቁበት ተመልክቷል፡፡
ከመክፈቻው ዕለት ጀምሮ ከጠዋቱ 2፡00 እስከ ምሽቱ 12፡00 ለእይታ ክፍት የሚሆነው ዐውደ ርእዩ፣ ከመቶ ሺሕ በላይ ተመልካቾች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተገለጸ ሲሆን የመግቢያ ቲኬት ሽያጭም ካለፈው ታኅሣሥ ጀምሮ በመካሔድ ላይ ነው፡፡ ዓላማውን የሚደግፉ አካላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ የጠየቀው ዐቢይ ኮሚቴው፣ ሕዝበ ክርስቲያኑም ወዳጅ ዘመዶችን ወደ ዐውደ ርእዩ በመጋበዝ ስለ ቤተ ክርስቲያን እንዲያውቅና እንዲያሳውቀው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱና በምእመኑ መካከል ያለውን መስተጋብር ለማዳበር፣ ማኅበሩ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ ከዘረጋቸውና በስፋት ከተገበራቸው ሰፊ የማስተማሪያና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች መካከል ዐውደ ርእይ አንዱ መሆኑን ያስረዳው ዐቢይ ኮሚቴው፤ ያለፉት አራት ዙር ዝግጅቶች፥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ፣ ታሪክ፣ የቅርስ ባለቤትነትና ባለአደራነት፤ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ለሀገሪቱ ዕድገት ላበረከተችው አስተዋፅኦ ሰፊ ሽፋን የሰጡ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡

Read 6691 times