Saturday, 06 February 2016 10:52

የመኪና እጥበት ድርጅቱ፤ ወረዳው አላሰራ አለኝ ሲል አማረረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

“ጥፋታችንን ሳይነግረን የንግድ ፈቃድ አላድስም ብሎናል”

    በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ድልበር በሚባለው አካባቢ ከ11 ዓመት በፊት የተቋቋመው “ራስ አገዝ የመኪና እጥበት”፤ ወረዳው ምክንያቱን ሳይነግረን የንግድ ፈቃድ አላድስም በማለቱ፣ 131 ሰራተኞች ሊበተኑ ነው ሲል ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡
የድርጅተ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ አየለ እንደገለፁት፤ ከ11 ዓመት በፊት የመኪና እጥበትና ውሃን ሪሳይክል በማድረግ የማጠብ ስራ ላይ የተመሰረተ ጥናት አዘጋጅተው ለአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ባቀረቡት መሰረት፤ አሁን እየሰሩ ያሉበትን ቦታ ከባለሥልጣን መ/ቤቱ የተሰጣቸው ሲሆን ስራውን በሰባት ሰራተኞች ቢጀምሩትም አሁን 131 ሰራተኞችን የሚያስተዳድር ድርጅት ለመሆን እንደበቃ ተናግረዋል፡፡
መጀመሪያ ላይ ውሃውንም ሪሳይክል በማድረግ የሚጠቀሙት ለአራት ዙር ብቻ እንደነበር ጠቁመው በአሁን ሰዓት አንድ ጊዜ የቀዱትን ውሃ ከ38-40 ጊዜ ሪሳይክል እያደረጉ እንደሚጠቀሙበት የገለፁት ስራ አስኪያጁ፣ ባለፉት 11 ዓመታት ፕሮፖዛሉን በማሻሻል የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ብዙ ደክመናል ብለዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ከወረዳው ሃላፊዎች  “ሃብት በአቋራጭ አፍርተሃል፤ በአቋራጭ የቦታ ካርታ ጠይቀሃል” እና ሌሎች ውንጀላዎች ሲቀርቡብኝ ነበር ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በመጨረሻም የንግድ ፈቃድ እንዲታደስልን ስንጠይቅ ያለበቂ ምክንያት አይታደስም ተብለና ሲሉ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ ሰባት አስተዳደር፤ ችግሩ ይሄ ነው ሳይል የንግድ ፈቃድ አላድስም፤ በማለቱ፣  እየሰሩ የሚማሩ፣ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ፣ ቤተሰብ የሚረዱ በአጠቃላይ 131 ሰራተኞቼ ሊበተኑብኝ በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ይሰጠኝ ሲሉ ተማፅነዋል - የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፡፡
የወረዳው ሃላፊዎች እየደወሉና በአሳቻ ሰዓት እየመጡ፤ “ህገ - ወጥ ግንባታ ገንብታችኋል፤  በግሬደር እናፈርሰዋለን” በማለት በየጊዜው ያስፈራሩናል ያሉት አቶ ስንታየሁ፤ “የፕሮጀክቱ ባለቤት ሀብት ስላፈራ ለሌላ ልማት እንፈልገዋለን” እያሉ ሰራተኛው በአግባቡ እንዳይሰራ ፍርሃት እያሳደሩበት ነው” ሲሉ አማርረዋል፡፡
“ድርጅቱም ሆነ እኔ ህገ - ወጥ አይደለንም፤ በመኪና እጥበት ታሪክ ቫት ተመዝጋቢ ሆነን እየሰራን ነው፤ ወረዳው በአንድ ወር ብቻ ከሰራተኛ ጡረታ፣ ከስራ ግብርና ቫት 61 ሺህ ብር ይሰበስባል” ያሉት አቶ ስንታየሁ፤ በአሰራራችን ላይ ያየው ችግር ካለ ወረዳው በዝርዝር ፅፎ በደብዳቤ ሊሰጠን ይችላል፤ ወንጀል አለባቸው ካለም አሊያም ፍ/ቤት እንዲከሱን ጠይቀናል፤ ሆኖም፤ ወረዳው መልስ አልሰጠንም ብለዋል፡፡
“ከዚያ ይልቅ የንግድ ፈቃድ አላድስም” ማለትን መርጧል፤ ፈቃዱ ሳይታደስልን መስራት ደግሞ ህገ - ወጥነት ስለሚሆን ሰራተኞቼ ሊበተኑብኝ ነው” ሲሉ ጭንቀታቸውን ገልፀዋል፡፡
የጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ ሰባት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አማኑኤል አስመላሽ በበኩላቸው፤ “መጀመሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 786 ካ.ሜ ቦታ ወስዶ እየሰራ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 3000 ሺህ ካሬ አስፋፍቷል፣ ህገወጥ ግንባታዎችን ገንብቷል፤ ይህን አስመልክተን ብዙ ጊዜ እንዲያፈርስ ብንመክረውም አልተቀበለንም” ብለዋል፡፡
የመኪና እጥበት ድርጅቱ ስራ አስኪያጅ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ወረዳው ለክቶ ባልሰጠኝ ቦታ ላይ ወደ ሶስት ሺህ ካ.ሜ አስፋፍቷል ማለት አይችልም፣ ገነባ አስፋፋ የሚሉት የክፍለ ከተማው አካባቢ ጥበቃ ዛፍ ቆርጦ ለማጓጓዝ የተጠቀመበትና ያራቆተው ቦታ እንዳይሸረሸር የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ፤ “ቦታውን ካልገነባህ ውል አላድስም” በማለቱ ውል ገብቼ የገነባሁትን ቦታ ነው” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃንና የወረዳውን አስተዳደር ያማረሩት አቶ ስንታየሁ፤ ቦታውን የሰጠኝ አካል የ2008 ዓ.ም ውል ካደሰልኝ በኋላ “ ቦታውን አስፋፍቷል፤ ገንብቷል” በሚል ውሉ እንዲቋረጥ ህገወጥ ድርጊት እየፈፀሙብኝ ነው ብለዋል፡፡


Read 3889 times