Saturday, 30 January 2016 12:52

እንደ ቀላል የምናየው ራስ ምታት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(34 votes)

 ራስ ምታት ሞትን የሚያስከትሉ ከባድ የጤና ችግሮች ምልክት ሊሆን ይችላል
              ማይግሪን ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን በሦስት እጥፍ ያህል ያጠቃል
                                        
    በአንጐላችን ውስጥ የሚገኙ የደምስሮች በተለያዩ ምክንያቶች ቀድሞ ከነበራቸው መጠን ሲጨምሩና ሲቀንሱ፣ ሲያብጡና ሲለጠጡ ለራስ ምታት ህመም ይዳርጋሉ፡፡  
ራሱን ችሎ ህመም የሆነው የራስምታት 3 ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡ እነዚህም፡-
Migrian Headache (ማይግሪን ሄዴክ)
Tension Headache (ቴንሽን ሄዴክ)
Claster Headache (ክላስተር ሄዴክ) ተብለው ይጠራሉ፡፡
Migrian Headache (ማይግሪን ሄዴክ)
ይህ የራስ ምታት አይነት ከሌሎች ህመሞች የበለጠ ከባድና አደገኛ ነው፡፡ ህመሙ በሴቶች ላይ ከወንዶች በሶስት እጥፍ የበለጠ ይከሰታል። በብዛት በወጣትነት ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎችን ያጠቃል፡፡ ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ በማይግሪን የመጠቃት ዕድል እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ዕይታን ማዛባት፣ ከጭንቅላታችንም ሆነ መላው የሰውነት አካላችን ወደ አንድ በኩል ማጋደል፣ ማቅለሽለሽ፣ የምግብ ፍላጐት በእጅጉ መቀነስ፣ ብርሃንን ለማየት አለመድፈር የዚህ በሽታ መገለጫዎች ሲሆኑ በሽታውና የህመሙ ስሜት እጅግ ከባድና የአካል ጉዳተኝነትንም ሊያስከትል የሚችል አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ማይግሪን በዘር የመተላለፍ ዕድል አለው፡፡
ይህ ራስ ምታት በአንደኛው የጭንቅላታችን ክፍል ላይ ይበረታል፡፡ ህመሙ ከጀመረ እስኪጠፋ ድረስ ከ4-72 ሰዓታትን ሊወስድ ይችላል፡፡ 60% ያህሉ የማይግሪን ህመሞች ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ አላቸው፡፡ ምልክቶቻቸውም፡- እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት፣ መደበት፣ መዛል፣ አብዝቶ ማዛጋትና መቁነጥነጥ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ማይግሪን የራስ ምታት የሰውነትን የነርቭ ሲስተም ያውካል፡፡  
Tension Headach (ቴንሽን ሄዴክ)
ይህ ዓይነቱ የራስ ምታት በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ በእኩል ደረጃ የሚከሰት ሲሆን በጭንቅላትና በአንገት አካባቢ የመደደርና የመጫጫን ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በሽታው በአብዛኛው በአዋቂነት ዕድሜ ክልል (ከ30-55) ድረስ ያሉትን የሚያጠቃና ሄደት መጣ የማለት ባህርይ ያሉት ህመም ነው፡፡
3. Claster Headache (ክላስተር ሄዴክ)
የዚህ ዓይነቱ የራስምታት ህመም በይበልጥ የሚያጠቃው ወንዶችን ነው፡፡ ህመሙ በተለይም በዓይን አካባቢ በስፋት ይገለፃል፡፡ ዓይን ቀይ ይሆናል (ደም ይለብሳል)፣ ዕንባ በብዛት ያመጣል፣ አፍንጫ አካባቢ የማቃጠል ስሜት ይኖራል፡፡ ህመሙ አብዛኛውን ጊዜ በፈረቃ በሚሰሩና የእንቅልፍ ሰዓታቸውን በአግባቡ በማይጠቀሙ ሰዎች ላይ ይከሰታል፡፡ አልኮል መጠጣትና ሲጋራ ማጨስም ለዚህ ህመም መከሰት ምክንያቶች ይሆናሉ፡፡
እነዚህ ሶስት ዓይነት የራስ ምታት ህመሞች በተለያዩ ጊዜ የሚያጋጥሙና ሄደት መለስ እያሉ የሚታዩ ቢሆንም ለሌላ ለከፋና ህይወትን ሊያሳጣ የሚችል የጤና እክል ምልክቶችም ሊሆኑ ይችላሉ። በራስ ምታት ህመም ከሚገለጡ ከባድ የጤና ችግሮች መካከል፣ ድንገተኛና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የደም ግፊት፣ ማጅራት ገትር፣ ዐይናችን ውስጥ የሚፈጠር ድንገተኛ የፈሳሽ ግፊት መጨመር (ግላኮማ)፣ በአንጎላችን ውስጥ የሚፈጠር ብግነት፣ በአንጎል ደምስሮች ላይ የመለጠጥ የመሳሳትና የመፈንዳት አደጋ መከሰት፣ የልብ ህመም፣ የአንጎል ውስጥ እጢ፣ የፓርኪንሰንስ በሽታና ስትሮክ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ለእነዚህ እጅግ ከባድና አደገኛ የጤና ችግሮች ምልክት የሆነው ራስ ምታትና ራሱን ችሎ ህመም የሆነው ራስ ምታትን መለየቱ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ህመሙ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመን ከሆነ፣ ምርመራ ማድረጉ የከፋ ችግር ላይ ከመውደቃችን በፊት መፍትሄ ልናገኝለት የምንችልበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ይረዳናል፡፡ በተለያዩ መንገዶች (በደም ምርመራ፣ MRI እና CTSCAN) በሚደረጉ ምርመራዎች የችግሩን መነሻነት ማወቅና አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይቻላል፡፡
ራስ ምታት እንደ ህመሙ መነሻነትና የህመም ደረጃ ህክምና ሊያገኝ የሚችል ችግር ሲሆን በራሱ እንደ በሽታ የተከሰተው የራስ ምታት ህመም በተለያዩ መድኃኒቶችና ህክምናዎች ሊፈወስ ይችላል፡፡ የሌላ ህመም ምልክት የሆነውን የራስ ምታት ለማከም ህመሙን ያመጣውን ችግር ምንነት በቅድሚያ መለየትና ለችግሩ መፍትሔ መፈለግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡
ለራስ ምታት ህመም እየተባሉ የሚወሰዱ እንደ ፓራሲታሞል፣ ዳይክሎፌናክ፣ አድቪልና አስፕሪን የመሳሰሉ መድኃኒቶች ህመሙን ሊያስታግሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህን መድኃኒቶች እንዳሻ እየደጋገሙ መውሰዱ ግን ለሌላ የጤና ችግሮች ይዳርገናል፡፡  
በተለይ ህፃናት፣ ከ12 ዓመት በታች ያሉ ልጆች፣ እርጉዝ ሴቶች፣ የጨጓራ፣ የጉበትና የኩላሊት ህመም ያለባቸው ሰዎች እነዚህን መድኀኒቶች ያለ ሃኪም ትዕዛዝ ፈፅሞ መጠቀም የለባቸውም፡፡

Read 32446 times