Saturday, 30 January 2016 12:27

የዘገሊላ ለት

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)


      እንደ አበባ ከአውዳመት ጋር በፍቅር የወደቀ ሰው ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በርግጥ በልጅነታችን ገና ዓመትባሉ ወራት ሲቀሩት ስለሚታረደው ዶሮ፣ ስለሚጣለው የቅርጫ ሥጋ የሚያወራ ጓደኛ ነበረኝ። ግን እርሱ ትኩረቱ ሥጋው ላይ ነው፡፡ እርሷ ግን ከነዘፈኑ ነው፡፡ ጓደኞችዋም የርሷ ዓይነት ይኖርባቸዋል ብዬ አንድ ሁለቱን ሠልዬ ነበር። ሲያልፍም አይነካቸው፡፡ ይልቅስ “ሀበሻ በዐል ሲወድድ!...” እያለች ታጥላለች፡፡ ሌላኛዋም ብትሆን ከርሷ ጋር አትመጣጠንም፡፡ ምናልባት የርሷንም ያህል ባይሆን በጥቂቱ የምትመስላት አንድ የቡና ቤት ሴት ነበረች፡፡
ቄጠማ መጐዝጐዝ፣ አበባ መነስነስ ትወድድ ነበር። ከመጀመሪያ ፍቅረኛዬ ጋር የተጣላሁ ሰሞን አብሬያት ሽርጉድ ብዬ ነበር፡፡ ከዚያ ሌላ ትዝ የሚለኝም የለ፡፡ ግን የታደለ አባት ደግሞ ቀላል የሚባል የአውዳመት ፍቅር የላቸውም፤ በተለይ መስቀል ደመራ ሲሰበስቡ ወራት ይቆጥራሉ፡፡ የርሳቸው የችቦ በዓላት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የብርሃን ፍቅርና ናፍቆት ዓይነት ነው፡፡ ለጥምቀትና ፋሲካ ያን ያህል ናቸው፡፡
የአበባ እኮ  ዓውዳመት አይመረጥም፡፡ ሥጋ የማይበላበት ቡሄ እንኳ በርሷ ዘንድ ደማቅ ነው። እሺ ቡሄ ከጌታ በተራራ ላይ ከፍ ብሎ ከመታየት ጋር ተያይዞ ነው እንበል፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንኳ ትንሿን ባንዲራ ገዝታ ነው የምትገባው፡፡ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን አብዮታዊ በዓላትም ቢኖሩ አትመለስም፡፡
ለነገሩ የወደደችውን በዓል ብታከብር ግድ አልነበረኝም፤ ገና ዛሬ ሳንጋባ ባንዲራ ግዛ፣ ዳቦ አስደፋ፣ ቀሚስ ሸምት… ያለችኝ ሴት፣ ነገ ጨረቃን አውርድ ብትለኝ የታባቴ እገባለሁ፡፡ ገንዘብንስ ይበደሩታል፣ ሥልጣን አምጣ ብትለኝ ምን ይውጠኛል!
ዘንድሮም ገና ጥምቀት ሲደርስ ትከሻዋ ለእስክስታ መነቅነቁን ያወቅሁት ቀድሜ ነበር፡፡ ሩቅ እያለ “…የዘገሊላ ለት፣ የዘገሊላ ለት/ነዪልኝ በኔ ሞት” ማለት ስለጀመረች ነቄ ነበርኩ፡፡ ስለዚህ አንድ ጂንስ ሱሪና አሪፍ ሸሚዝ ገዛሁላት፡፡
ደስታዋ ነፍሴን ነው የኮረኮራት፡፡ ምስጋና ስታውቅበት!...ከሁሉ ነገሯ ቅንነትዋና ግልጽነትዋ ይማርከኛል፡፡ ለነገሩ ድሬዳዋን የረገጠ ሰው ከዚህ አያመልጥም፡፡ ድሬዳዋ መኖር የማይችለው ማሽንክ ሰው ነው፣ ድብቅ ሰው መከራውን ያያል፡፡ ቆንቋና ሰው ፈተና እሣት ላይ ይጣዳል፡፡ የኔዋ አበባም ከእናትዋ ጋር እዚያ ጥቂት ዓመታት ቆይታለች፡፡ አባትዋ ወታደር ስለነበሩ ብዙ ቦታ አይታለች፡፡
ቁመናና መልክ ተሟልቶላታል ባይባልም፣ ለኔ ግን ቆንጆ ናት፡፡ ስትስቅ ዓለምን ታሽከረክራለች። ቅርጽ የላትም የሚሉት ነገር አይገባኝም፡፡ ዳሌዋና ወገብዋ… የሚሉ ጓደኞች አሉኝ፡፡ “መልሴ ቀንታችሁ ነው” የሚል ነው፡፡ ብቻ ያም ተባለ ይህ አንድ ጐጆ ሥር የምንከትትበት ጊዜ እየደረሰ ነው፡፡ እኔም ብዙ ሀብት ያፈራሁ አልሁን እንጂ ሲቪል መሀንዲስ ነኝ፣ እርሷም በአካውንቲንግ ተመርቃለች፡፡
ስለዚህ ብዙ ጊዜ ተለያይቶ መኖር አስፈላጊ አይደለም፡፡ ጧት መነፋፈቅ፣ ማታ መሸኛኘት፤ ልብ ማንጠልጠልና መንጠልጠል ሲረዝም አይመክርም። ደስ የሚለው ደግሞ እርሷ ሠርግ የሚባል ነገር አትወድድም፡፡ እኔ ልውደድ አልውደድ አላውቅም። ስለ ሠርግ ሲነሳ ግን እደነግጣለሁ፡፡ የገንዘቡ ነገር ይሁን አይሁን እንጃ፡፡ እጅ ለእጅ ገጥሞ፣ እንደ ዔሊ እየተጐተቱ ሕዝብን ሥራ አስፈትቶ፣ እልል በሉልኝ…አጨብጭቡለኝ ማለት ራስ ወዳድነት ይመስለኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ ሠላሣዬን ከደፈንኩ በኋላ ማቅማማት የለብኝም፡፡ አባወራ መሆን አለብኝ፡፡
የከተራ ቀን ዋቢሸበሌ ጋርደን ውስጥ ተቀምጬ እየጠበኳት ሳለ እየዘፈነች ነበር የመጣችው። “የዘገሊላ ለት፣ የዘገሊላ ለት፣ ነይልኝ በኔ ሞት! ለአስተርዮ ማርያም…” እያለች፡፡
ወዲያው “ይሄ ደሞ የምን ጋዜጣ ነው… ይሄን ፖለቲካ አታንብብ አላልኩህም?” አለች፡፡ “…በዓውዳመት ቀን እንኳ በጥምቀት”
ሣቄ መጣና የሆነ ነገር ልላት ስል “አሽሟጣጭ” ብላ ቀደመችኝ፡፡
“ቀይ ሴት ነበር የምወድደው፤ እግዜር ጠይም ላይ ጣለኝ” አልኩ፡፡
“አግኝተህ ነው…የሀበሻ ጠይም አይገኝም፤…”
“ሎሚ ጣሉባት በደረቷ የተባልሽው አንቺ ነሻ!”
“ያማ ቀረ… ሞባይል መጣል ነው አሁን!”
ዛሬ ደሞ አምሮባታል፡፡ የገዛሁላትን ልብስ አልለበሰችም፡፡ የሀበሻ ቀሚስ ነበር የለበሰችው፡፡ እንዴት ዘንጣለች፡፡
“ጂንሱን ጠላሽው?”
“ኧረ በፍፁም! ምርጥ ነው የኔ ውድ…ግን የሀበሻ ሴት በጥምቀት ቀን የፈረንጅ ልብስ አትለብስም!”
ደስ የሚለኝ አንዱ ነገሯ ይህ ነው፡፡ በፈረንጅ ነገር የሰከረች አይደለችም፡፡ በዚያ ላይ ሀገሯን ትወድዳለች። ባህሏን ታከብራለች፡፡ ይህን ያስለመደችኝ አክስቷ ናት ብላኛለች፡፡ የተወሰኑ ዓመታት ወሎ ሰፈር ከአክስቷ ጋር ኖራለች። ከአክስቷ ልጅ ጋር እንደ ወንድምና እህት ነው ያደጉት፡፡ ጋብቻችን ላይ አንድዋ የቅርብ ሰው እርሷ እንደምትሆን ነግራኛለች፡፡ ቢሆንም አንዳች ደስ የማትሰኝበት ነገር ያለ ይመስላል፡፡ ምናልባት በድላት ይሆን የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ስለርሷ ሲነሳ ነገር ታሳጥራለች፡፡ እኔም ብዙ ገፍቼ አልሄድም፡፡
ዋቢሸበሌ ጥቂት ከቆየን በኋላ ወጣን፡፡ የከተራን በዓል እንደ ዘንድሮ አክብሬው አላውቅም። በልጅነቴ ማስቲካ ስናጠቅ፣ ሴት ልጆች ስላከፍ፣ ጭፈራ ስጨፍር ያሳለፍኩት… እርሱ ሌላ ጣዕም ስለሆነ ወዲህ አይመጣም፡፡ ነፍስ አውቄ ትልቅ ነኝ ካልኩበት ጊዜ በኋላ ግን እንደዚህ ደሺህ ገነት ሆኖልኝ አያውቅም። አበባ ናት፤ የምድረበዳ ገነት የሆነችኝ - መሰለኝ፡፡
በመጀመሪያ አውጉስታ የልብስ ስፌት ፋብሪካ አካባቢ ያለችውን ፅዮን ማርያምን አጅበን፣ ወደ ማደሪያዋ አደረስን፡፡ ይህ የኔ ሠፈር በዓል ነበር። በማግስቱ ደግሞ የእርሷን ሠፈር የኪዳነምህረት ታቦት፣ ከታቦት ማደሪያ ወደ ቤቷ አስገብተን ተመለስን፡፡
ከፊሉ በአማርኛ ሌላው በኦሮሚኛ፣ አንዳንዱም በወላይትኛ እየጨፈረ፣ ጉራጊኛውና ትግሪኛው ቀልጦ በዓሉ በድምቀት አለፈ፡፡ የኔና የርሷ በዓል ግን እንደቀጠለ ነበር፡፡ ምሣችንን ሆቴል ቤት እንክት አድርገን በልተን፤ ወደ መጠጡ ዞርን፡፡
አበባ አሥቸገረችኝ፡፡ ድራፍትና ቢራ ኮመኮመች። “አታብዢ” ብሏት መች ሠምታኝ! “ይልቅ ዛሬ እኔን የምትሠማበት ቀን ነው” ብላኝ አረፈችው፡፡
ሞቅ ሲላት፤ “የምንጋባባት ቀን ስለደረሰ ቤት እንከራይ! አታንቀላፋ!” አለችኝ፡፡
“እንከራያለን”
ከንፈሬን በከንፈሯ ስትነጥቀኝ ሰዎች ያሉ መስሎኝ ደነገጥኩ፡፡ እርሷ እንዲህ ላለው ነገር ግድ የላትም፡፡
“ሰሞኑን ባንክ ያለኝን ገንዘብ አውጥቼ ዕቃ እገዛበታለሁ፡፡”
“እሱ ያንቺ ሥልጣን ነው!”
“እሺ የኔ ጌታ!” አሁንም ጉንጬን ሳመችኝ። “ዛሬ ሱፍ ልበስ ያልኩህም ለእዚህ ነው፣ ዘንጠህ እንድትታይልኝ የኔ ቆንጆ!”
“እሺ - አንቺን ደስ ይበልሽ እንጂ እንኳን ሱፍ ሌላም እለብሳለሁ፡፡” አልኳት፡፡ ደግሞ ከልቤ ነው፡፡ አበባን ለመሰለች ቅን ሴት የማላደርገው ምን አለና? በዚህ ሞቅታ መሀል አንድ ሰው ወደ እኛ መጣና የሆነ ወረቀት ወርውሮ ሄደ፡፡
“ምንድነው ምንድነው?” አለች፤ አይኖችዋ ደፍርሰዋል፡፡
“እንጃ ምናባቱ አውቄ?”
“ታውቀዋለህ?”
“በፍፁም!”
ከፍቼ ሳነብበው እርሷ ዕብድ ሆነች፡፡
“አሁንም አይተወኝም! ደብዳቤ ፅፎ ይልካል!...ሕይወቴን ይረብሻል!” አረጋጋኋት፡፡ የአክስት ልጅ ተብዬ ነው፡፡ አለቀሰች፡፡ “…ታሜ” አለችኝና አንገቴ ላይ ተጠመጠመች፡፡
“ወንድሜ ነው ብዬ አቅፌው ሣድር የደፈረኝ’ኮ ነው፡፡ እርሱ! ኮ ነው አሁንም አልላቀቅ ያለኝ…” “እዚህ ሀገር ሆነሽ ያላንቺ መኖር አልችልም” ነው የሚለኝ… አረመኔ!”
“ተዪው! ካላረፈ በምንጠቀምበት መንገድ እንጠቀማለን፤ አይዞሽ” አልኳት፡፡ በሕግ ልናስቆመው እንደምንችል አውቃለሁ፡፡
“አንተ ባትሆን ግን ሌላ ጣጣ ውስጥ ከትቶኝ ነበር፡፡”
“አይዞሽ!” እኔም ሰው መኖሩን ረስቼ ሳምኳት፡፡
መጠጡን አላቆመችም፡፡ እኔም ደስ ይበላት ብዬ ተውኳት፡፡ የዓውዳመት ሱስ አለባት፡፡
ምሽት ላይ እንደሌላው ጊዜ በእግር አልሸኘኋትም። ላዳ ተከራይቼ ቤቷ ሣደርሳት ልብሴን ይዛ ተንጠለጠለችብኝ፡፡ “ዛሬ እንኳ ቤታችን ግባ” ብላ ተናነቀችኝ፡፡ ቤታቸው ዝግ ስለነበር ከቦርሣዋ ቁልፍ አውጥታ ከፈተችና ገባን። ሣሎናቸው ያምራል፤ ቀይ የለበሰ ሶፋ፣ የሚያምር ምንጣፍ፣ ቴሌቪዥን፣ ፍሪጅ… አለ፡፡
“በል ተቀመጥ” ብላ አስቀመጠችኝ፡፡
አባብያት ልወጣ ስል፤ “ነገ እኮ ቃና ዘገሊላ ነው፤ እንጋባለን..” ብላ ያዘችኝ፡፡
“እሺ” ብያት ልወጣ ስል፣ እናትዋ ከተፍ አለች፡፡ ሰውነቴ ሽምቅቅ አለ፡፡ ተያየን፡፡
“አስተዋውቅሻለሁ ያለችኝ አንተን ነው?” ወይ ዕድሌ… ወይ ዕድልሽ…” ብላ ወደ ኋላ ወደቀች፡፡
በዚያ የሽሽት ጊዜ፣ በዚያ ክፉ ቀን፣ አብሬያት የከረምኩት ለካ ከእናትዋ ጋር ነበር… ወጥቼ ሸመጠጥኩኝ፡፡
“ታ…ሜ…ታ..ም..ራ..ት”
ድምፅዋ ጠላልፎ የሚጥለኝ መሠለኝ፡፡
…የዘገሊላ ለት… የዘገሊላ ለት… የሚለው ትዝታዋ ተከተለኝ፡፡

Read 3878 times