Saturday, 30 January 2016 11:51

“ግዴለም፣ እኔ አለሁ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቀደም ነው፣ በአንድ ሚኒባስ ታክሲ ወደ አራት ኪሎ እየመጣን ነበር፡፡ እናላችሁ… ቤተ መንግሥቱን እያለፍን ሳለ ከተሳፋሪዎቹ አንዱ… “ሥላሴ መግቢያ ላይ አውርደኝ…” ይላል፡፡ ረዳቱ ሆዬ ሳቅ ብሎ ዝም ይላል፡፡ ሰውየው እንደገና… “ሥላሴ በር ላይ ጣለኝ…” ይላል፡፡ ይሄን ጊዜ ረዳቱ…
“እዛ’ጋ መቆም ክልክል ነው…” ይለዋል፡፡
ተሳፋሪ ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ግዴለም፣ እኔ አለሁ፡፡”
ግዴለም እኔ አለሁ!
እንዴት፣ እንዴት ነው ነገሩ! እንዲህ ብሎ ነገር አለ እንዴ? እንክት ነዋ! ሁሉም ቦታ ቃል በቃል “ግዴለም፣ እኔ አለሁ…” አይባል እንጂ… ነገርዬው መአት ነው፡፡
ታዲያላችሁ…እነኚህ “የእከሌ ልጅ ነው…”   “እነ እትና የአገሩ ሰዎች ናቸው…” ምናምን እየተባለ… “የኬኩን ሦስት አራተኛ ይገባኛል…” የሚሉት ያው “ግዴለም፣ እኔ አለሁ…” አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ አለ አይደል…“ማነው ዝንቤን እሽ የሚለው…” አይነት ነው፡፡
እናላችሁ…ታክሲ ውስጥ የነበረው ሰውዬ “ግዴለም፣ እኔ አለሁ…” በሚልበት ጊዜ “እንደፈለግሁ የትስ ብወርድ…” “የትስ ምን ባደርግ ማነው ዝንቤን እሽ የሚለው…” ባይ ነው…እንደ አቅሚቲ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ሰውየው አራት ኪሎ ሲወርድ ረዳቱን የጠየቀው ጥያቄ ምን መሰላችሁ… “የመርካቶ ታክሲ የት ነው የሚቆመው!” የመርካቶ ታክሲ ‘የት እንደሚቆም እንኳን ሳያውቁ “ግዴለም፣ እኔ አለሁ…”  ብሎ ‘ፉከራ’ አለ እንዴ! መኪና ‘ይሰጠዋ’! ማመልከቻ በመጻፉ ለመተባበር ፈቃደኞች ነን፡፡
የምር ግን እኔ የምለው…አለ አይደል…እነኚህ ‘ልዩ እንክብካቤ’ የሚፈልጉ ሰዎች አይገርሟችሁም? ማለት አንዳንድ ጊዜ እኮ ‘ይሉኝታ’ የምትባል ነገር አለች። የሆነ አገልግሎት መስጫ ቦታ ላይ እናንተ ሁለት ሰዓት ሙሉ ተሰልፋችሁ ተራችሁን እየጠበቃችሁ ነው። እናማ…የሆነ “ግዴለም፣ እኔ አለሁ…” አይነት ሰው እንደመጣ ዘው ብሎ አገልግሎት መስጫው ቢሮ ሊገባ ይሞክራል፡፡ ታዲያላችሁ…“ተራህን ያዝ…” ምናምን ሲባል ግልምጫው… አለ አይደል… “ማነሽ ልብ ያለሽ ዝንቤን እሽ የምትይ…” አይነት ነው፡፡
የምር ግን…እንደዚሀ አይነት ሰዎች መብዛታቸው ግርም አይላችሁም! ወይ ለዚህ አይነት ‘አገልግሎት’ መስፈርቱ ይነገረንና እኛም ማመልከቻ እናስገባ፡፡
ደግሞላችሁ…የሆነ ቦታ እናንተ ስትገቡ ምንጥር ተደርጋችሁ ትፈተሻላችሁ፡፡ እናማ…የሆነ “ግዴለም፣ እኔ አለሁ…” አይነት ሰው ይመጣና፣ አይደለም ‘ተመንጥሮ’ መፈተሽ፣ ዳበስ እንኳን ሳይደረግ በቀይ ምንጣፍ አይነት ማለፍ ይፈልጋል፡፡ የሚገርመው… አንዳንድ ቦታ ፈታሾቹም እጃቸውን አጣምረው ትንፍሽ ሳይሉ ያሳልፏችቸዋል፡፡ ለፍተሻ እንኳን እጃቸውን ከፍ ሲያደርጉ ልክ በሁለቱም እጆቻቸው ሠላሳ፣ ሠላሳ ኪሎ የተሸከሙ ነው የሚመስለው፡፡
እናማ…እንደ ሚኒባሱ ተሳፋሪ… “ግዴለም፣ እኔ አለሁ…” አይነት ነገር የሚያደርገን መአት ነን፡፡
እኔ የምለው…ያን ጊዜ ‘ኔትወርክ’ ምናምን ሲባል የነበረው ነገር ምን ደረሰ? ‘ሲወጣ ሁሉም ወደየኔትወርኩ’ ሄዶ ቀረ ወይስ… ነገርዬው እንዴት ነው? ‘አፕዴት’ አድርጉና! አለበለዛ መጀመሪያ ‘አለመነካካት’ ነበር፡፡
ስሙኝማ...የሚኒባስ ታክሲ ነገር ካነሳን አይቀር…ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ በነበርኩበት ታክሲ ውስጥ የሆነ ‘ሪቮሊሲዮን’ ምናምን ሊነሳ ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ ምን ሆነ መሰላችሁ…ሾፌር ሆዬ የሆነ ኃይማኖታዊ መልእክት ያለው ነገር በቴፑ ለቋል። የሆነ ተሳፋሪ…
“እሱን ነገር አጥፋው…” ይለዋል፡፡
“ለምን አጠፋዋለሁ?”
ተሳፋሪም “እሱን አጥፋውና ወይ አንዱን ኤፍ ኤም ክፈት...” ይለዋል፡፡ ይሄኔ ‘ሲምቢሮ’ ክንዱ ላይ ምኑ ከምኑ የማይለይ ንቅሳት የተነቀሰው ሾፌር…
“እንግዲህ ካልተመቸህ ታክሲ መቀየር ነው…” ይለዋል፡፡ ሰውየው ይሄን ጊዜ በስጨት ይላል፡፡
“ለምንድነው ታክሲ የምቀይረው! ይሄ እኮ የህዝብ ትራንስፖርት ነው፣ የፈለግኸውን ማስጮህ አትችልም…” ይላል፡፡
እናላችሁ… “አይ የእኛ ነገር…” የምትሉት አይነት ነገር የተፈጠረው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ አንዳንዱ ተሳፋሪ…
“ቢያጫውት ምን አለበት፣ እኛ መስማት እንፈልጋለን…” ምናምን አይነት ነገር ይላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ…
“የማንፈልገውን ለመስማት መገደድ አለብን እንዴ!…” ይላል፡፡
ከዚህ በኋላ…ምን አለፋችሁ ታክሲው በሁካታ ተሞላ፡፡ የሚገርመው ምን መሰላችሁ… አብዛኞቹ አስተያየት ሲሰጡ ወይም ‘ሲከራከሩ’ የተሳፋሪ መብት ጉዳይ አሳስቧቸው ሳይሆን፣ ‘ዋናው ነጥብ’ የየራሳቸው እምነት ነበር፡፡
እናማ… በህዝብ ትራንስፖርት ላይ ይህኛውን ወይም ያኛውን እምነት የሚያጎላ፣ አንዳንዴም (በተዘዋዋሪም ቢሆን) ሌላውን የሚያሳንስ አይነት ነገር መልቀቅ ለምን መቆም እንዳልተቻለ አይገባኝም።
የምር ግን…የምር ‘ወዴት እየሄድን ነው’ የሚያሰኛችሁ እንዲህ አይነት ነገሮች ስታዩና ስትሰሙ ነው፡፡ የእውነትም ሁሉ ነገራችን በቋፍ ላይ ያለ ነው የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ተንታኝ በበዛበት፡ ይሄ ሁሉ ‘የፖለቲካ ተንታኝ’ ባለበት፣ ይሄ ሁሉ ‘የስነ ጥበብ ተንታኝ› ባለበት፣ ይሄ ሁሉ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ’ ባለበት…ምነዋ ለምን ቶሎ ‘ሆድ እንደሚብሰን’ ለምን ቶሎ “አጉራህ ጠናኝ…” እንደሚያሰኘን የሚተነትንልን ጠፋሳ! ነው…ወይስ ምንም ትንታኔ አያስፈልገውም!
የምር ግን…በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሾፌሩ የራሱ እምነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ግን ህዝብ ትራንስፖርት ላይ፣ የተለያዩ እምነቶች የሚከተለውም፣ ጭራሽ እምነት የሌለውም አንድ ላይ በሚገለገልበት ታክሲ ውስጥ ለአንዱ ወገን ብቻ የሚስማማ ነገር መልቀቅ ትክክል አይደለም፡፡ ኤፍ.ኤም. ከሆነ፣ ምንም እንኳን ሁሉም የየራሱ ምርጫ ቢኖረውም፣ የሌላውን ያህል ላያጣላ ይችላል፡፡
ሌላ ደግሞ አለላችሁ… አንዳንዱ ሾፌር የአገሩን ዘፈን ያስገባና ተጀምሮ እስኪያልቅ እሱን ብቻ ያሰማል። አንዳንዱ ሾፌር ደግሞ ለእሱ ብቻ በሚመቸው ቋንቋ የተሠራ ካሴት ይከትና ይለቀዋል።
ታክሲ ላይ የተለጠፈች ነገር ምን ትላለች መሰላችሁ… “ታክሲ የሚቆመው ፌርማታ ላይ ነው እንጂ በቤት ቁጥር አይደለም፡፡” ሌላ እንዲጨመርልን የምንፈልገው ‘ጥቅስ’ አለ… “ታክሲ የተዘጋጀው ሰዎችን ከስፍራ፣ ስፍራ ለማመላለስ እንጂ ለሰበካ አይደለም፡፡”
እኔ የምለው…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…‘ቦተሊከኛ’ ሆኖ አንዳንዴ ምናምን ሊበራል፣ አንዳንዴ ምናምን ዲሞክራሲ… ‘ሪሊጂየስ’ የሚሆነው እኮ… አለ አይደል…ሸቤ ገብቶ ሲወጣ ብቻ ነው! ቂ…ቂ…ቂ… ግራ ስለገባኝ ነው፡ በቃ ‘ሪሊጂየስ’ መሆን የሚፈልግ ሰው ለመንደርደሪያ ‘ቦተሊከኛ’ ይሁን…አራት ነጥብ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 8032 times