Saturday, 30 January 2016 11:45

ሃዋሳ አሁንም በሥጋት ተወጥራለች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(42 votes)

• ዩኒቨርሲቲው ለ15 ቀን ተዘግቶ ተማሪዎች ተሰናብተዋል
• የመሬት መንቀጥቀጡ ትናንት ለ5 ተከታታይ ጊዜያት ተከስቷል
• የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ከቤት ወጥተው በድንኳን ውስጥ ናቸው
• የርዕደ መሬቱን መጠን የሚለካ መሳሪያ ነገ ይተከላል
• መንቀጥቀጡ ለቀጣዮቹ ዘጠኝ ቀናት ይቀጥላል

     በሃዋሣ ከተማና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች ባለፈው እሁድ ጥር 5 የጀመረው የመሬት መንቀጥቀጥ ትላንት ለ5 ጊዜ መከሰቱን ተከትሎ ነዋሪዎችን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ጥሏል፡፡
በሬክተር ስኬል 4.3 ይደርሳል የተባለው ይኸው ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት፤ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ መደናገጥና ፍርሃትን የፈጠረ ሲሆን በተለይ የአዋሣ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ማስከተሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ርዕደ መሬቱ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ በተደጋጋሚ መከሰቱን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲው ለ15 ቀናት እንዲዘጋና ተማሪዎቹ ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ተደርጓል። የተማሪዎች የማጠቃለያ ፈተና ጥር 16 የነበረ ቢሆንም በአደጋው የተነሳ ተማሪዎቹ ተረጋግተው መዘጋጀትና መፈተን የማይችሉ በመሆኑ  ፈተናው ለየካቲት 7 እንዲተላለፍ መወሰኑን ዩኒቨርሲቲው ከትላንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ህንፃዎች ላይ የመሰነጣጠቅ ጉዳትን ያስከተለ ሲሆን በትናንትናውም ዕለትም ለ5 ጊዜያት ያህል ሲንቀጠቀጥ መዋሉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ጉዳቱ በተለይ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የከፋ ሲሆን ተማሪዎች በቤተመፃሕፍት ውስጥ ለማጠቃለያ ፈተና እያጠኑ በነበረበት ወቅት የተከሰተው ርዕደ መሬት በተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥን በመፍጠሩ እርስበርስ በመገፋፋትና በመስኮት በመዝለል ለተለያዩ የአካል ጉዳቶች መዳረጋቸው ታውቋል፡፡
ርዕደ መሬቱ በትናንትናው ዕለት በተደጋጋሚ በመከሰቱ ነዋሪዎች ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ የገቡ ሲሆን በስላሴ ኮንደሚኒየም ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ እንደተናገሩት፤ ቀንም ሆነ ሌሊት በቤታቸው ውስጥ ማሳለፍ አልቻሉም፡፡ አደጋው በድንገት የሚከሰት በመሆኑ ህፃናት ልጆችን ይዞ በቤት ውስጥ መቀመጡ ፈጽሞ የማይታሰብ ጉዳይ ያሉት ነዋሪዋ፤ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ከነልጆቼ ውሎዬም ሆነ አዳሬ በድንኳን ውስጥ ነው ብለዋል፡፡ አደጋው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች፡- ደቡብ ዕዝ፣ ሥላሴና አዲስ ከተማ ክፍለከተማ ውስጥ በሚገኙ ኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚኖሩ ነዋሪዎች ሜዳ ላይ ድንኳን በመትከል ቀንና ሌቱን ከቤት ውጭ እንዳያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡
የፒያሣ አካባቢ ነዋሪው አቶ ተመስገን ታዬ እንደሚናገሩት፤ በከተማዋ የተከሰተውና በተደጋጋሚ በተከታታይ የቀጠለው ርዕደ መሬት፤ የከተማዋን ነዋሪ ህዝብ ሥነልቦና በእጅጉ የጐዳው ሲሆን ቀጥሎ ምን ይፈጠር ይሆን? የሚል ሥጋት ውስጥም ከቶታል ብለዋል፡፡  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተማዋ የበርካታ ፎቆች ግንባታ እየተካሄደባት መሆኗን የጠቆሙት ነዋሪው፤ አብዛኛዎቹ ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ተጠጋግተው የተሰሩ እንደሆኑ ገልፀው፡፡ ርዕደመሬቱ በፎቆቹ ላይ አደጋ ቢያስከትል በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ጉዳት መጋለጣቸው አይቀርም፤ ይህም በእጅጉ ሥጋት ላይ ጥሎናል ብለዋል፡፡
በከተማ ውስጥ በተለያዩ ህንፃዎች ላይ የሚገኙ ቢሮዎች ሙሉ በሙሉ ተከፍተው አገልግሎት ለመስጠት ስጋት ስላደረባቸው አብዛኛዎቹ ተዘግተው ነው የሰነበቱት ተብሏል፡፡ ርዕደ መሬቱ ባስከተለው ጉዳትም በርከት ያሉ ህንፃዎች፣ ታዋቂ ሆቴሎችና የመዝናኛ ሥፍራዎች የመሰነጣጠቅና የመፈራረስ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
የርዕደ መሬቱን መጠን የሚለካ መሣሪያ በነገው ዕለት ሊተከል መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ የመሬት መንቀጥቀጡ ለቀጣይ ዘጠኝ ቀናት ይቀጥላል ተብሎ እንደሚገመት ጠቁመዋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው የሚሉ ነዋሪዎች፤ አደጋው በድንገት ቢከሰት ህብረተሰቡ ማድረግ ስለሚገባው ጉዳይ በበቂ ሁኔታ አልተነገረም ይላሉ፡፡ አደጋውን ለመከላከልም ቅድመ ዝግጅት መደረግ ይገባዋል ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡን በስልክ የጠየቅናቸው የከተማዋ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገዲባ፤ “መረጃውን አሁን ለመስጠት አንችልም፤ በአካል መጥታችሁ አነጋግሩን” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የከተማዋ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ ሲሆን ነዋሪዎችም ርዕደ መሬቱ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል በሚል ሥጋት ውስጥ ናቸው ተብሏል፡፡

Read 7235 times