Saturday, 30 January 2016 11:42

ድርቁ አስጨናቂና አሳሳቢ ሆኗል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

• በድርቁ አካባቢዎች 350ሺ ተጨማሪ ህፃናት ይወለዳሉ
• የነፍሰ ጡር እናቶች ቁጥር እየጨመረ ነው
• የእርዳታ እህል በፍጥነት እንዲጓጓዝ ተጠየቀ
  በድርቅ በተጐዱ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚቀጥሉት 6 ወራት ውስጥ 350ሺህ ተጨማሪ ህፃናት እንደሚወለዱ የተባበሩት መንግስታት ያስታወቀ ሲሆን ለድርቁ የሚደረገው አለማቀፍ ድጋፍ የተቀዛቀዘ መሆኑ ችግሩን አስጨናቂና በእጅጉ አሳሳቢ አድርጐታል ተብሏል፡፡
አለማቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት በበኩሉ፤ በአሁኑ ወቅት ከሶሪያ ቀጥሎ አሠቃቂ የሰብአዊ ቀውስ ያንዣበበው በኢትዮጵያ መሆኑን ጠቁሞ፤ 4መቶ ሺህ ህፃናት የአልሚ ምግብ በእጅጉ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል፡፡
ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎቹን በመላክ ተዘዋውረው እንዲጎበኙ ማድረጉን የጠቆመው የህፃናት አድን ድርጅቱ፤ በርካታ እናቶች ነፍሰ ጡር መሆናቸው አሳሳቢ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ለእናቶች እንክብካቤ ማድረግ አስቸጋሪ በሆነበት እንዲሁም እናቶች አስፈላጊውን ንጥረ ምግብ ማግኘት ባልቻሉበት ሁኔታ የነፍሰ ጡር ሴቶች ቁጥር መጨመር ችግሩን አስጨናቂ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ የሚወለዱት ህፃናት እጣ ፈንታም አሳሳቢ የህፃናት አድን ድርጅቱና የተባበሩት መንግስታት ጠቁመዋል፡፡  
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ድርቁን ለመቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ከ10.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማውጣት እንደሚገደድ የአለም የምግብ ፕሮግራም ከትናንት በስቲያ ያስታወቀ ሲሆን የገንዘብ ድጋፉም እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ ተሰባስቦ ለተረጅዎች ድጋፍ መዋል እንዳለበት ገልጿል፡፡
በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የድርቁ ሁኔታ በ1977 ዓ.ም ከተከሰተውና የ1 ሚሊዮን ገደማ ዜጐችን ህይወት ከቀጠፈው የድርቅ ክስተት የባሰ መሆኑን የጠቆመው የአለም የምግብ ፕሮግራም፤ 10.5 ቢሊዮን ብሩን በመጪው ወር ከለጋሾች እንደሚያሰባስብም ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ለእርዳታው ያስፈልጋል ተብሎ ከተገመተው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ በአሁኑ ወቅት 37 በመቶ ያህሉ መገኘቱን የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ የአደጋና ስጋት ቅነሳ ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ፤ መንግስት ለተጐጂዎች በቂ እርዳታና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፆ እስካሁን ከተለያዩ አገራትና የረድኤት ተቋማት 431 ሚ. ዶላር ድጋፍ ቃል መገባቱን አስታውቋል።
የመንገድ ችግርና የመጋዘን እጥረት እርዳታ በማከፋፈል ሂደቱ የሚገጥሙ እንቅፋቶች እንደሆኑም ኮሚሽኑ ጨምሮ ገልጿል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በበኩሉ በእርዳታ አሰጣጡ ላይ ዘይት፣ ስንዴና የማባያ የምግብ ግብአቶች በአንድነት ለተረጂዎች እየቀረቡ አለመሆኑ እርዳታ ፈላጊዎች ለእንግልት እየዳረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ የምግብ ግብአቶች በአንድነት እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡
እስከ ሚያዚያ 2008 የሚበቃ እርዳታ መገኘቱን የጠቆመው ኤጀንሲው፤ እርዳታውን ከወደብ የማጓጓዝ ሥራ በፍጥነት መከናወን እንዳለበት አሳስቧል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአጭር የሞባይል የጽሑፍ መልዕክት ስኬታማ የሆነ እርዳታ እያሰባሰበ መሆኑን  አስታውቋል፡፡ የማህበሩ የኮሚኒኬሽንና የሃብት ማሰባሰብ መምሪያ ሃላፊ አቶ ደግሰው አማኑ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በአጭር ጽሑፍ መልዕክቱ እርዳታ የሚያዋጣው የህብረተሰብ ቁጥር በየእለቱ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀን እስከ 10ሺህ ሰው ከ5 ብር 50 ብር የሚደርስ የገንዘብ እርዳታ እየሰጠ እንደሆነ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

Read 5099 times