Saturday, 30 January 2016 11:37

ኢቢሲ ለበጎ አድራጎት 640 ሺህ ብር መመደቡን ገለፀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

ለመቄዶንያና ለክብረ አረጋዊያን 450 ሺ ብር ለግሷል

   የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በበጎ አድራጎት ስራ ለማክበር 640ሺ ብር የመደበ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ 250 ሺ ብር ሲለግስ፣ ለክብረ አረጋዊያን ደግሞ 200 ሺ ብር አበርክቷል፡፡  የፊታችን ሰኞም ለውዴ አረጋውያን መርጃ ማዕከልና ሰባተኛ አካባቢ ለሚገኝ የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ለእያንዳንዳቸው 93 ሺህ ብር እንደሚለግስ የኮርፖሬሽኑ የለጋሽ ቡድኑ አስተባባሪ አባል አቶ መንግስተአብ ገ/መድህን ተናግረዋል፡፡
ትላንት ረፋድ ላይ የኢቢሲ የይዘት ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብረሀም ገ/መድህንና የኮርፖሬት ዘርፍ ም/ስራ አስፈፃሚውን አቶ ኤሊያስ አዋቶን ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎችና የሰራተኛ ተወካዮች በመቄዶንያ ተገኝተው አራቱንም ማዕከላት የጐበኙ ሲሆን አቶ አብርሀም ገ/መድህን ባደረጉት ንግግር፤ በጉብኝቱ ብዙ መደነቃቸውን ገልፀው ኢቢሲ ወደፊትም ከማዕከሉ ጎን  እንደሚቆም ቃል በመግባት የ250 ሺ ብር ቼክ ለመቄዶንያ የቦርድ ሰብሳቢ ለዶ/ር ፀጋዬ በርሄ አስረክበዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው ቼኩን ከተቀበሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ኢቢሲ በሚዲያ ሽፋን በኩል እያደረገላቸው ስላለው አስተዋፅኦና በአዲስ ቲቪ ላይ ስለተሰጣቸው የአየር ሰዓት አመስግነው፣ ህዝቡ ስለ መቄዶኒያና ስለ መረዳዳት ባህል በደንብ እንዲገነዘብ በዋናው ጣቢያ (ኢቢሲ) የአየር ሰዓት እንዲፈቀድላቸው ተማፅነዋል፡፡
የኢቢሲ የለጋሽ ቡድለ ከመቄዶኒያ ከወጣ በኋላ ወደ “ክብረ አረጋዊያን” በመሄድ የ200 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የፊታችን ሰኞ ለ “ውዴ አረጋዊያን” እና 7ኛ ለሚገኘው የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ተመሳሳይ ልገሳ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
ኢቢሲ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ካከናወናቸው የበጎ አድራጎች ስራዎች መካከል ገንዘብ መለገስን ጨምሮ ደም መለገስና አልባሳትን ሰብስቦ ማከፋፈል ይገኙባቸዋል፡፡

Read 1133 times