Saturday, 30 January 2016 11:37

የጥጥ አምራቾች ማህበር ምርታችንን የሚገዛን አጣን አለ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(3 votes)

“የጥጥ ግብይት ቆሟል፤ አምራቹ ከጥጥ ስራ ሊወጣ ነው”

  የኢትዮጵያ ጥጥ አምራቾች ማህበር፤ ያመረትነውን ጥጥ የሚገዛን አጥተናል ሲል ያማረረ ሲሆን መንግስት አምራቾቹን ለመርዳት በኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት በኩል ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ተብሏል።
የጥጥ አምራቾች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሐዱሽ ግርማይ፤ የመንግስት ጥረት ያልተሳካው ድርጅቱ ለግዥ ያቀረበው ዋጋ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት፤ የራሱን ትርፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለአምራቹ እንደየጥጡ ደረጃ በኪሎ ከ30-33 ብር የግዥ ዋጋ መተመኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልፀው፣ ይሄን የዋጋ ተመን ግን አምራቹ አያዋጣኝም ብሎ አልተቀበለውም፡፡
የሌሎች አገራት አምራቾች መንግስታቸው ይደግፋቸዋል፤ በእኛ ሀገር የጥጥ ሴክተሩ በተገቢው ሁኔታ እየተደገፈ አይደለም የሚሉት አቶ ሐዱሽ፤ “አለም በሄክታር ከ50 እስከ 60 ኩንታል ሲያመርት፤ እኛ ግን በሄክታር እያመረትን ያለነው ከ10 እስከ 15 ኩንታል ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
አምራቹ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ፡፡ “ኬሚካልና የተለያዩ ማሽኖችን ከውጪ እያመጣ ነው የሚሰራው፤ በዚያ ላይ የምርጥ ዘር ችግሮች አሉበት፤ የምርምር ስራው በጣም የተዳከመ በመሆኑም የምንጠቀመው ዝርያ ከዛሬ 25 አመት በፊት እንጠቀምበት የነበረውን ነው” - ብለዋል፤ አቶ ሃዱሽ። ይህም የዘርፉን ጥራትና ምርታማነት እንደጐዳው ይገልፃሉ፡፡ “በአሁኑ ወቅት የጥጥ ግብይት ቆሟል፤ አምራቹ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ እንሄዳለን፤ ሰላማዊ ሰልፍም እንወጣለን፣ መንግስት መልስ መስጠት ይኖርበታል” እስከማለት ደርሰዋል ያሉት አቶ ሃዱሽ፤ ይህ ሁሉ ችግር ቢያልፍ እንኳን በሚቀጥለው ዓመት አምራቹ ከጥጥ ምርት ለመውጣት ወስኗል ብለዋል። እኛም እንደ ማህበር ድልድይ ሆነን ከመንግስት ጋር ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ሞክረን ነበር፤ ግን አልቻልንም ይላሉ - ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡
የኢንዱስትሪ ግብአት አቅርቦት ድርጅት (የቀድሞው ጅንአድ) በበኩሉ፤ የጥጥ ዋጋው የወጣው በገለልተኛ አካል መሆኑንና አምራቹን ለማበረታታት በኪሎ 2 ብር ድረስ ጭማሪ መደረጉን ገልጿል፡፡ የድርጅቱ የግዥና አቅርቦት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ከበደ ስለሁኔታው ሲያስረዱ፤ “እኛ ገዝተን የምንሸጠው ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ነው፤ ኢንዱስትሪው ምርቱን አምርቶ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ገበያም ተወዳዳሪ መሆን አለበት። ዋጋው የተሰላውም የዓለም አቀፍ ገበያውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ዋጋው ቢጨምር ገዥ አይኖርም፡፡ ድርጅታችን የተቋቋመው በዋናነት አምራቹንና ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ እንጂ ለትርፍ አይደለም” ብለዋል፡፡   
አምራቹ በተባለው ዋጋ አያዋጣኝም ካለ፣ እናንተም በዚህ ዋጋ ካልሆነ አንገዛም ካላችሁ የመጨረሻ መፍትሔው ምንድነው ያልናቸው አቶ አባይ፤ “አልሸጥም ያለ አካል የራሱን አማራጭ ይወስዳል” ሲሉ መልሰዋል፡፡

Read 2082 times