Saturday, 23 January 2016 13:48

የሂችሀይኪንግ ጨዋታ

Written by  ደራሲ፡- ሚላን ኩንዴራ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

ሆቴሉ አይስብም፡፡ ‘አንድ ለእናቱ’ እንዲሉ፣ ‘አንድ ለከተማዋ’ ነው፡፡ ሌላ ሆቴል የለም፡፡ ወጣቱም ከዚህ በላይ

ማሽከርከር አልፈለገም፡፡ “እዚሁ ጠብቂኝ፡፡” ብሏት ከመኪናው ወረደ፡፡
ከመኪናው ሲወርድ መልሶ እራሱን ሆነ፡፡ ተናደደ ደሞ፡፡ ጨርሶ እሄድበታለሁ ብሎ ያላሰበው ከተማ ውስጥ ነው

ያለው፡፡ ለዚያውም በምሽት፡፡ እዚህ የመጣው ደግሞ በማንም ሰው ገፋፊነት ወይም አስገዳጅነት ሳይሆን በራሱ ውሳኔ

ነው፡፡ የበለጠ ተበሳጨ፡፡ ለዚህ ቂልነቱ እራሱን ወቀሰ፡፡ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ሁኔታውን ተቀበለ፡፡ ታትራስ

ያስያዙት ክፍል እስከ ነገ ይቆያቸዋል፡፡ የእረፍታቸውን የመጀመሪያ ቀን ባልጠበቁት ቦታ ማሳለፍም ብዙ አይከፋም፡፡

ተፅናና፡፡
ሆቴሉ ውስጥ ገባ፡፡ በጭስ የታፈነውን፣ በጩኸት የተሞላውን፣ ግር ግር የበዛበትን ምግብ ቤት አልፎ ሄደ፡፡ እንግዳ

መቀበያው የት እንዳለ ጠየቀ፡፡ መተላለፊያውን አልፎ፣ ደረጃዎቹ መዳረሻ ጋ ያለ ቦታ ጠቆሙት፡፡ ለጉድ የጃጀች፣ ፈዛዛ

ቢጫ ፀጉር ያላት ሴትዮ የመስታወት ሳጥን ውስጥ ቁጭ ብላለች፡፡ ከፊቷ ያለው ጠረጼዛ ላይ ብዙ ቁልፎች አሉ፡፡

ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ፣ ሳትያዝ የቆየችውን፣ ብቸኛ ክፍል ቁልፍ አቀበለችው፡፡
ልጅቷ መኪናው ውስጥ ብቻዋን ስትሆን ገፀ-ባህሪዋን ረሳቻት፡፡ እራሷን ያልጠበቀችው ከተማ ውስጥ ስላገኘች

የመሸወድ ስሜት አልተሰማትም፡፡ ወጣቱን ስለምትወደው የትም ቢወስዳት ቅር አይላትም፡፡ ታምነዋለች፡፡ ምንም

አንሆንም፣ እና ወደ ገሃነም እንሂድ ቢላት አብራው ትሄዳለች፡፡ ቆይ ግን አሁን እሷ እዚህ መኪና ውስጥ ብቻዋን ቁጭ

ብላ እየጠበቀችው እንዳለው ስንት ሴቶች ጠብቀውት ይሆን? እነዛ የማታውቃቸው ግን ሁሌም በቅናት የሚያሳብዷት

ሴቶች አሁንም ታወሷት፡፡ ሌሎቹን ብትተው በስራ ምክንያት ከብዙዎቹ ጋር ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዟል፡፡
በሚያስገርም ሁኔታ አሁን ስለእነዚህ ሴቶች ስታስብ አልተበሳጨችም፡፡ እኒያን በቅናት ጨርቋን የሚያስጥሏትን

ሀላፊነት የጎደላቸውና ስድ ሴቶች ቦታ ወስዳለች፡፡ እነሱ የሚቀመጡት ቦታ ነው የተቀመጠችው፡፡ ደስ ተሰኘች፡፡ አሁን

እነሱን ከፍቅረኛዋ ህይወት ውስጥ ቆርጣ ትጥላቸዋለች፡፡ እስካሁን እሷ ልትሰጠው ያልቻለችውን ከእነሱ ብቻ ያገኝ

የነበረውን ሁሉ ትሰጠዋለች፡፡ እሷ የማትችለው እነሱ በቀላሉ የሚሆኑት ምንድነው?
ግድ የለሽ፡፡
ሀፍረተ-ቢስ፡፡
ወራዳ፡፡
ረቀቅ፣ መጠቅ ያለ እርካታ ተሰማት፡፡ አሁን ሁሉን ሴቶች የመሆን እድል አግኝታለች፡፡ በአንዴ ሁሉን ሴቶች ልትሆንና

ሁሉን ነገር ልትሰጠው የምትችለው እሷ ብቻ ናት፡፡
እሷ ብቻ፡፡ አሁን የእሷ ምርኮ ነው፡፡
ወጣቱ የመኪናውን በር ከፍቶ ልጅቷን እየመራ ወደ ምግብ ቤቱ ገቡ፡፡ ሁካታው፣ አቧራውና ጭሱ ውስጥ፣ አንዲት

ያልተያዘች ጠረጴዛ ጥግ ላይ አገኙ፡፡
“አሁን እንዴት ነው የምትንከባከበኝ?” አጠያየቋ ትንኮሳ አለው፡፡
“አፕሬቲፍ ከምን ከምን ይሰራልሽ?”
አልኮል መጠጥ ላይ ብዙ አይደለችም፡፡ አልፎ አልፎ ወይን ትጠጣለች፡፡ ብዙ ጊዜ ምርጫዋ ቬርሙጥ ነው፡፡ አሁን

ግን ሆን ብላ፡-
“ቮድካ፡፡” አለች፡፡
“መልካም፡፡” አለ ወጣቱ፡- “መስከር ብሎ ነገር የለም ግን ፡፡”
“የሰከርኩ እንደሆነስ?”
ዝም አላት፡፡ አስተናጋጅ ጠራ፡፡ የሚጠጣ? ሁለት ቮድካ፡፡ የሚበላ? ሁለት ስቴክ፡፡ አስተናጋጁ መጠጡን ወዲያው

አመጣላቸው፡፡ ወጣቱ ብርጭቆውን ከፍ አድርጎ፡-
“እነሆ ላንቺ ጤና!”
“ሌላ የተሻለ ብርጭቆዎቻችንን የምናጋጭበት ነገር የለህም?”
የልጅቷ ጨዋታ የሆነ ነገሩ የምር እየደበረው ነው፡፡ ቃሎቹ ብቻ አይደሉም እንግዳ የሆኑበትና ያስጠሉት፡፡ ሁለንተናዋ

ተቀይሯል፡፡ የሰውነቷ እንቅስቃሴዎች የሌላ ናቸው፡፡ ፊቷ ላይ ያሉት ገለፃዎች የእሷ አይደሉም፡፡ ያለምንም መዛነፍ

እነዚያን የሚያውቃቸውን፣ ያንገሸገሹትንና የሚጠላቸውን ሴቶች ሆናለች፡፡ ቁጭ እነሱን፡፡
እናም (አሁንም ብርጭቆውን ከፍ አድርጎ ይዞ) ብርጭቆ የሚያጋጩበትን ምክንያት ቀየረው፡-
“እሺ ለአንቺ ሳይሆን የእንስሳትን ዋና፣ ዋና መለያ ባህርያትና የሰው ዝርያን አስጠሊታና አስከፊ ፀባዮች አዋህደው

ለያዙ መሰሎችሽ ሁሉ፡፡”
“ ‘መሰሎችሽ’ ስትል ሁሉንም ሴቶች ማለትህ ነው?”
“አይደለም፡፡ አንቺን የሚመስሉትን ብቻ ነው ያልኩት፡፡”
“ለማንኛውም የሰው ልጅን ከእንስሳት ጋር ማነፃፀር የሚመስጥ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡”
“እሺ፡፡” አሁንም ብርጭቆውን ከፍ አድርጎ እንደያዘ ነው፡- “እንዲያ ከሆነ ለመሰሎችሽ አልጠጣም፡፡ ለነፍስሽ ልጠጣ፡፡

ይስማማሻል? ከአናትሽ ወደ ከርስሽ ሲወርድ ለሚደምቀው፣ ከከርስሽ ወደ አናትሽ ሲወጣ ለሚጨልመው ነፍስሽ፡፡”
ልጅቷ ብርጭቆዋን አነሳች፡-
“እሺ፡፡ ወደ ከርሴ ለወረደው ነፍሴ፡፡”    
 
“አሁንም አንድ ጊዜ እራሴን አስተካክላለሁ፡፡” አለ ወጣቱ፡- “ለከርስሽ፤ ነፍስሽ ለሚዘቅጠበት ከርስሽ፡፡”
“ለከርሴ፡፡” አለች ልጅቷ፡፡ ከርሷ (ስሙ በቀጥታ ስለተጠራ) መኖሩን አስታወቀ፡፡ የከርሷ እያንዳንዱ ቅንጣት ተሰማት፡፡
አስተናጋጁ ስቴኮቹን አመጣ፡፡ ወጣቱ ተጨማሪ ቮድካና ሶዳ አዘዘ፡፡ (አሁን ብርጭቆዎቻቸውን ለጡቶቿ አጋጩ)

ጨዋታው በእንዲህ አይነት መጃጃል ቀጠለ፡፡ ልጅቷ ዝሙት መቀስቀስን እየተጠበበችበት መጣች፡፡ ወጣቱ ደግሞ

እየተናደደ መጣ፡፡ ዝሙት መቀስቀስን ይህን ያህል ከቻለችበት ፊቱንም ስሪቷ የሸርሙጣ ነው ማለት ነው፡፡ ባዕድ

ፍጡር ከህዋ መጥቶ ሰውነቷ ውስጥ አልገባ ነገር፡፡ እሷው እራሷ ናት በሚያስደምም ፍፅምና እየተወነች ያለችው፡፡

እንዲህ ቢሆንስ፡- እንበልና እውነተኛ ማንነቷ ሁኔታዎች ሳይፈቅዱለት ቀርቶ የሰውነቷ ዋሻ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፡፡

አሁን ሁኔታዎች ሲመቻቹ፣ በሂችሀይኪንግ ጨዋታው አሳቦ ምሽጉን ሰብሮ ወጣ፡፡ ልጅቷ ጨዋታው የፈጠረላትን እድል

ተጠቅማ፣ እውነተኛ ማንነቷን ለጊዜው ገሸሽ አድርጋ፣ ገፀ-ባህሪዋን ተላብሳ እየተጫወተች እንደሆነ ታስብ ይሆናል፡፡

የተገላቢጦሽ ቢሆንስ? ጨዋታውን ተጠቅማ፣ እስከዛሬ ስትተውን የነበረውን ማንነቷን ትታ፣ እውነተኛ ባህሪዋን

ተላብሳ ቢሆንስ? እየተወነች ሳይሆን፣ እራሷን እየሆነች ቢሆንስ? ከእሱ አንፃር የተቀመጠችው የፍቅረኛውን ገላ የለበሰች

ሌላ እንግዳ ሴት አይደለችም፡፡ ነገርየው እንዲያ አይደለም፡፡ ሌላ ገፀባህሪይ ምናምን አይደለችም፡፡ እራሷ ፍቅረኛው

ናት፡፡
አያት፡፡ ሸከከችው፡፡
ተራ ጥላቻ ነገር አይደለም፡፡ ትንሽ ተወሳስቧል፡፡ መንፈሷ የገፈተረውን ያህል፣ ገላዋ ይስበው ጀመር፡፡ መንፈሷ

ያስጠላውን ያህል ገላዋ ማረከው፡፡ መንፈሷ ባእድ ሲሆንበት በገላዋ ተወሰወሰ፡፡ ገላዋ ገላ ሆነ፡፡ እስከዛሬ አስተውሎት

አያውቅም ነበር፡፡ እስከዛሬ ገላዋ፡- ሀዘኔታ፣ ስሱነት፣ ደንታ፣ ፍቅር፣ ስሜት፣ በሚባሉ ደመናዎች ውስጥ ተከልሎ

ነበር፡፡ (አዎ፤ ገላዋ እስከዛሬ አልነበረም! ጠፍቶ ነበር፡፡) ገላዋን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያየው ሆነበት፡፡
ተነሳች፡፡ ሶስት ቮድካና ሶዳ ጨርሳለች፡፡ እየተሽኮረመመች፡-
“አንዴ ይቅርታ፡፡” አለች፡፡
“የእኔ እመቤት ወዴት እየሄድሽ እንደሆነ መጠየቅ ይቻላል?”
“የምትፈቅድልኝ ከሆነ ሽንቴን ልሸና ነው፡፡” ብላ ሄደች፡፡
በተናገረችው ነገር ወጣቱን ማስደንበሯ ተመችቷታል፡፡ ሽንቴን ልሸና ነው ማለት ምንም ክፋት የለውም፡፡ ግልጽና

የተለመደ ነው፡፡ ፍቅረኛዋ ግን እሷ እንዲያ ስትል ሰምቶ አያውቅም፡፡ ከተላበሰቻት ገፀ ባህሪ ነገረ ስራ ሁሉ አሁን

አጽንኦት አድርጋ እንደተጠቀመቻቸው ቃላት ብርቅና ድንቅ የሆነባት የለም፡፡ ሽንቴን ልሸና ነው፡፡ ደስ ብሏታል፡፡

ማራኪ ጨዋታ ነው፡፡ መቼም ተሰምቷት የማያውቅ አቦ-እስኪ-ወላ-በሉ የሚያሰኝ ምንግዴነት የሚያመጣው ደስታ

አጥለቀለቃት፡፡
የምታደርጋቸው እያንዳንዱ እንቅስቃሴዎች ወደፊት ከሚፈጥሩባት አላስፈላጊ ጭንቀቶች፣ ቀድማ ተበድራ ትጨነቅ

የነበረች ልጅ፣ አሁን በማይታመን ሁኔታ፣ ሙሉ ለሙሉ ፈታ ብላለች፡፡ አሁን ያለችበት አዲስና ባዕድ ህይወት፡-

ሀፍረት የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ ታሪክ? የላትም፡፡ ትናንት? ኖሮ አያውቅም፡፡ ነገ? መቼም አይመጣም፡፡ ሀላፊነት?

ብሎ ዘፈን የለም፡፡ ገደብ የለሽ ነፃነት አላት፡፡ ልጅቷ፣ ሂችሀይከሯን ሆና የፈለገችውን ማድረግ ትችላለች፡፡ ሁሉ ነገር

ተፈቅዶላታል፡፡ የፈለገችውን ማለት፣ የፈለገችውን ማድረግ፣ የፈለገችውን መሆን ትችላለች፡፡
በክፍሉ ውስጥ ስትራመድ ሁሉም ጠረጴዛ ላይ የነበሩት፣ ሁሉም ሰዎች እያዩዋት ነበር፡፡ እያዩዋት እንደሆነም

ታውቋታል፡፡ አዲስ አይነት እርካታ ተሰማት፡፡ የማታውቀው እርካታ ነው፡፡ ቁሌታም ሴቶች ከገላቸው የሚያገኙት

ጨዋ ያልሆነ እርካታ ነው፡፡ እስካሁኗ ቅፅበት ድረስ እሷ ውስጥ የነበረችውን የአስራ አራት አመት ኮረዳ

አልተፋታቻትም ነበር፡፡ በዚህ ቅጽበት ተፋታቻት፡፡ ጡቶቿ በአስራ አራት አመቷ ቀጥ ብለው፣ ተቀስረው ለአለም

ህዝብ በሙሉ ይታዩ ነበር፡፡ ጡቶቿ እንዲያ መሆናቸው ያሳፍራትና ያስጨንቃት ነበር፡፡ ባለጌ የሆነች ይመስላት ነበር፡፡

በውብ መልኳና በሚያምረው ተክለ ሰውነቷ ብትኮራም፣ ይህን ደስታዋን ሁሌም ሀፍረት ያደፈርሰው ነበር፡፡ የሴት

ውበት ከቅንዝር ጋር ብቻ መታሰቡ ያስጠላት ነበር፡፡ እሷ ገላዋን የምታስበው ከፍቅር ጋር እና ከምታፈቅረው ሰው ጋር

አጣምራ ነበር፡፡ በመንገድ ላይ ወንዶች አፋቸውን ከፍተው ጡቶቿ ላይ ሲያፈጡ፣ ሽሽግ የሆነውን የእሷንና

የፍቅረኛዋን ምስጢር ያረከሱባት ያህል ይቀፋታል፡፡ አሁን ሂችሀይከር ናት፡፡ ግብ፣ አላማ፣ መድረሻ የሌላት ሴት ናት፡፡

የፍቅር ቁርኝት ከሚሻው ጥንቃቄ ነፃ ሆናለች፡፡ ውብ ገላዋ አትኩሮቷን ሁሉ ወስዶታል፡፡ ድሮ ባእድ አይኖች ገላዋ ላይ

ሲርመሰመሱ ይሰማት የነበረ አለመመቸት አሁን የለም፡፡ ብዙ ባእድ አይኖች፣ ብዙ ሲያፈጡባት፣ ቅንዝር ተሰማት፡፡
የመጨረሻውን ጠረጴዛ ልታልፍ ስትል፣ ሙክክ ያለ ሰካራም፣ አራዳ መሆኑን ሊያሳያት በፈረንሳይኛ፡-
“ስንት ትያለሽ ወይዘሪት?” አላት፡፡
ምን እንዳላት ገብቷታል፡፡
ጡቶቿን ወደፊት ወርወር አደረገቻቸው፡፡ ዳሌዋን አመሰችው፡፡
ግራ አጋቢ ጨዋታ ነው፡፡ ግራ አጋቢነቱን ለማሳየት፡- ለምሳሌ ወጣቱ የክስተቱን ጨዋታነት ተቀብሎ የማይታወቅ

ሾፌር በመሆን በብቃት እየተወነ ነው፡፡ በእያንዳንዷ ቅፅበት ግን ሂችሀይከሯ ውስጥ ፍቅረኛውን ማየት አልተወም፡፡

የማታውቀውን ሰው ስታማልል በቦታው የመገኘትና የመመልከት ‘እድል’ አግኝቷል፡፡ በቅርብ እርቀት ሆኖ በሱ ላይ

ልትባልግ ስትል ምን እንደምትመስል አይቷል፡፡ ምን እንደምትል ሰምቷል፡፡ (በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ሆና ነው ያያትም

የሰማትም፡- ልትባልግ ስትል፣ እየባለገች እያለ፣ ከባለገች በኋላ፡፡)
መርጦ የፈለገውን መሆን ይችላል፡፡ ወይ እራሱን ወይ ሾፌሩን፡፡ ልጅቷ በሱ ላይ ባልጋለችን? አይ፡፡ አዎ፡፡ አያዎ፡፡
ክስተቱ ከአያዎም የከፋ ነው፡፡ ወጣቱ ማፍቀር ብቻ አይደለም ልጅቷን ያመልካታል፡፡ ልጅቷ ለሱ እውን ሆና ልትኖር

የምትችለው ታማኝና ንፁህ በሚባሉ ቅጥሮች ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቅጥር ውጪ ልጅቷ የለችም፡፡ አትኖርም፡፡

ውሃ መፍላት ከጀመረበት ነጥብ ለጥቆ ውሃ መሆኑ ይቀራል፡፡ አሁን እሷም የታማኝነትና የንጽህናን አደገኛና አስፈሪ

ድንበር ፈታ ብላ አለፈችው፡፡
እሳት ለበሰ፡፡ እሳት ጎረሰ፡፡
ልጅቷ ከሽንት ቤት መጣች፡፡
“እዚያ ጋ ያለ ወጣት ስንት ትያለሽ ወይዘሪት አለኝ፡፡”
“ሊገርመሽ አይገባም፡፡” አለ ወጣቱ፡- “ሸርሙጣ ነው የምትመስይው፡፡”
“ይህቺን ታህል ግድ እንደሌለኝ ታውቃለህ?”
“ለምን አብረሽው አትሄጅም ታዲያ!”
“አንተ አለህ ብዬ ነው፡፡”
“እኔን ካስተናገድሽ በኋላ ወደ እሱ ትሄጃለሽ፡፡ ሂጂና አብረሽው እንደምትሆኚ ሁኚ፡፡”
“አልማረከኝም፡፡”
“ቢማርክሽ ኖሮ ግን በአንድ ምሽት ከብዙ ወንዶች ጋር መተኛት አይደብርሽም ነበር፡፡”
“ማራኪ ይሁኑ እንጂ ችግር የለውም፡፡”
“እንዴት ብትተኚያቸው ነው የምትመርጪው? በየተራ ነው ወይስ አንድ ላይ?”
“እንዴትም ቢሆን ግድ የለኝም፡፡”
ንግግራቸው ወደ ፅንፍ አልባ ስድነት ተሸጋገረ፡፡ ልጅቷ ደንግጣለች፡፡ መቃወም ግን አትችልም፡፡ ጨዋታ እንኳ ነፃነትን

ይነጥቃል፡፡ በጨዋታው ህግ መገዛት የሚባል ነገር አለ፡፡ በጨዋታው ህግ መገደብ ይመጣል፡፡ አሁን ይህ ጨዋታ

ባይሆን ኖሮ ሂችሀይከሯ ነገርየው ድሮ ገና ቀፏት፣ ጥላ ትሄድ ነበር፡፡ ከጨዋታ ግን ማምለጥ ብሎ ዘፈን የለም፡፡ አንድ

ቡድን ለጨዋታው የተመደበው ጊዜ ከማለቁ በፊት የጨዋታውን ሜዳ ትቶ አይወጣም፡፡ መቼ ነው የቼዝ ጠጠሮች

ደበረኝ ብለው የቼዝ መጫወቻ ሰሌዳውን ጥለው ወጥተው የሚያውቁት? የጨዋታው ሰሌዳም ሆነ፣ ሜዳ ቅጥር

አለው፡፡ ከቅጥሩ አይታለፍም፡፡ ከሜዳው አይወጣም፡፡ ልጅቷ ጨዋታው እንደፈለገው ለዛውን ቢያጣም መጫወት

መቀጠል እንዳለባት ታውቃለች፡፡  ጨዋታ ነዋ በቃ፡፡ አሁን የያዙት ጨዋታም ቅጥ አንባሩ በጠፋ መጠን፣ ለዛ ቢስ

በሆነው ያህል፣ ለከት ባጣ ልክ፣ ጨዋታ እየመሰለ ይመጣል፡፡ መጫወት መቀጠል ግድ ይሆናል፡፡ ‘ይህን ጨዋታ

ከቁም ነገር አትፃፊው፤ ብትተይው ይሻላል’ ብትባል መስሚያዋ ድፍን ነው፡፡ ብትሰማም አትቀበልም፡፡ ጨዋታ ስለሆነ

ፍርሃት አልተሰማትም፡፡ ተቃውሞ የላትም፡፡ ጨዋታው እንዲያውም ናርኮቲክ እንደወሰደ ሰው አጦዛት፡፡
ወጣቱ አስተናጋጁን ጠራውና ከፈለ፡፡
“ተነሺ ልንሄድ ነው፡፡”
“ወዴት?” የተገረመች መስላ፡፡
“መጠየቅ የለም፡፡ ዝም ብለሽ ነይ፡፡”
“እንዴት፣ እንዴት ነው የምታዋራኝ?”
“ሸርሙጦችን እንደማዋራው፡፡”
ጨለምለም ባለው ደረጃ ወደ ላይ ወጡ፡፡
የአንደኛው ፎቅ ደረጃ የሚያልቅበትና የሁለተኛው ፎቅ መውጫ ሊጀመር የሚልበት ቦታ ጋ፣ ሽንት ቤቱ አጠገብ፣

ጥምብዝ ብለው የሰከሩ ሰዎች ቆመዋል፡፡ ልጅቷን ብዙ ፀያፍ ነገር ተናገሯት፡፡ ሁለተኛው ፎቅ ላይ ደርሰው ወጣቱ

ክፍላቸውን ከፈተና መብራት አበራ፡፡
ጠባብ ክፍል ናት፡፡ ክፍሏ ውስጥ ያሉት፡- ሁለት አልጋዎች፣ ትንሽዬ ጠረጴዛ፣ አንዲት ወንበርና እጅ መታጠቢያ

ናቸው፡፡ በሩን ቆለፈና ወደ ልጅቷ ዞረ፡፡ ተሸራሙጣ ፊቱ ቆማለች፡፡ የሚወደውን የህፃንና ንጹህ ፊት ፈለገ፡፡ ነገርየው

በአንድ ሌንስ ሁለት ምስሎችን እንደ መመልከት ነው፡፡ አንደኛው ምስል ሌላኛው ላይ ተደርቧል፡፡ በአንደኛው ምስል

ዘልቆ ሌላኛውን ማየት ይቻላል፡፡ እኒህ አንዳቸው ሌላቸውን አሳልፈው የሚያሳዩ ምስሎች ልጅቷ ውስጥ ሁሉ ነገር

እንዳለ አመለከቱት፡፡ ነብሷ ቅርፅ የለሽ ነው፡፡ ነብሷ ጭቃ ነው፡፡ እንደ አበጁት ይበጃል፡፡ ነፍሷ የተፈለገውን ሆኖ

መገኘት ይችላል፡- ታማኝ-ከሀዲ፤ አጭበርባሪ-የዋህ፤ ንፁህ-ዝሙተኛ፡፡ ሁሉንም ናት፡፡ ቡትቶ ናት፡፡ አቅለሸለሸው፡፡

ከሌሎች ሴቶች የምትለየው ላይ ላዩን ብቻ ነው፡፡ ውስጡን ልክ እንደነሱው ናት፡፡ ልታስተናግደው የማትችለው

ሀሳብ፣ ስሜትና ክፋት የለም፡፡ ሁሉንም ትችላለች፡፡ ያቺ ከሌሎች ሴቶች ሁሉ ልዩ ናት ብሎ የሚያስባት ሴት የለችም፡፡

የሚያፈቅራትን ሴት ሀሳቡ፣ ፍላጎቱና እምነቱ ተባብረው የፈጠሯት ናት፡፡ የአእምሮው የፈጠራ ውጤት ብቻ ናት፡፡

ቅዠት ናት፡፡ እውኗ ሴት ይኸው ፊቱ ቆማለች፡፡ ተስፋ በሌለው ሁኔታ ባዕድ ናት፡፡ ተስፋ በሌለው ሁኔታ አወዛጋቢ

ናት፡፡
አስጠላችው፡፡
“ምን እየጠበቅሽ ነው? አውልቂ፡፡”
“አስፈላጊ ነው?”
የድምጽዋን ቃና በደንብ ያውቀዋል፡፡ የሆነች ሴት፣ የሆነ ጊዜ እንዲህ ብላዋለች፡፡ የትኛዋ እንደሆነች አያስታውስም

እንጂ፡፡ ሊያረክሳት ፈለገ፡፡ ሊያዋርዳት ፈለገ፡፡ ሂችሀይከሯን አይደለም፡፡ የእራሱን ፍቅረኛ ነው ማዋረድ የፈለገው፡፡

ጨዋታው ከእውነተኛ ህይወት ጋር ተቀላቀለ፡፡ ሂችሀይከሯን ማዋረድ፣ ፍቅረኛውን ለማዋረድ ሽፋን ብቻ ነው፡፡
አሁን ጨዋታ ብሎ ዘፈን የለም፡፡ ነገርየው ጨዋታ መሆኑን የምር ረስቶታል፡፡ ፊቱ የቆመችው ሴት እንዴት

እንደምትቀፍ መግለፅ አይችልም፡፡ እያያት የኪስ ቦርሳውን አወጣ፡፡ ባለ ሀምሳ ክራውን ቢል አወጣ፡፡ ሰጣት፡፡
“አይበቃሽም?”
ልጅቷ ባለ ሀምሳ ክራውኑን ቢል ተቀበለች፡፡
“ከዚህ በላይ አታወጣም ብለህ ነው የምታስበው፡፡” አለች፡፡
“ከዚህ በላይ አይገባሽም፡፡”
ልጥፍ አለችበት፡፡
“ይኼ አልተመቸኝም፡፡ ሌላ ሞክሪ፡፡”
እቅፍ አደረገችውና አፏን ወደ አፉ አስጠጋች፡፡
“የማፈቅራቸውን ሴቶች ብቻ ነው የምስመው፡፡” ገፋት፡፡
“እናም እኔን አታፈቅረኝም?”
“ጨርሶ፡፡”
“ማንን ነው የምታፈቅረው?”
“ይመለከትሻል? አውልቂ፡፡”
በእንዲህ አይነት አኳኋን ልብሷን አውልቃ አታውቅም፡፡ ሀፍረቱ፣ የውስጥ ስቃዩዋ፣ መንከርፈፉ፣ ልጁ ፊት ልብሶቿን

ስታወልቅ ይሰሟት የነበሩ ነገሮች ሁላ (አሁን ደግሞ እንደሌላው ጊዜ ጨለማው ውስጥ መደበቅ አልቻለችም) ብን

ብለው ጠፉ፡፡ አሁን በራስ መተማመን አላት፤ ከዚያም አልፋ፣ ብልግናም ጨምራበት፣ በኤሌክትሪክ ብርሃን

ተጥለቅልቃ ከፊቱ ቆማለች፡፡ የቡና ቤት ዳንሰኞች የተካኑበትን፣  ዝግ ብለው ስሜትን ለጉድ በሚያነሳሳ መልክ ልብስን

ማውለቅ ከየት እንደተማረች ለራሷም ገርሟታል፡፡ ወጣቱ እያያት በሰለጠነ ዝግታ፣ እያንዳንዱን እንቅስቃሴዋን

እያጣጣመች፣ ልብሶቿን አወለቀች፡፡ በትንሽ፣ በትንሹ መጋለጥ፣ መራቆት ውስጥ ደስታን አገኘች፡፡
ሙሉ ለሙሉ እርቃኗን ሆነች፡፡
ጨዋታው እዚህ ጋር ማብቃት እንዳለበት ብልጭ አለላት፡፡ ልብሶቿን ማውለቅ እስካሁን ለብሳት የነበረችውን ገፀ ባህሪ

እንደማውለቅ ታውቆ ጨዋታው እልባት ሊደረግለት ይገባል፡፡ አሁን እራቁቷን ናት፡፡ እራቁት ሆና የምን ጨዋታ ነው?

እራቁት ተሁኖ የምን ሌላ ሰው መምሰል ነው? እራቁቷን ስለሆነች እራሷን ነች፡፡ ወጣቱ ይህን አውቆ ጨዋታ

ተብዬውን ወደዚያ አራግፎ ሊቀርባት ይገባል፡፡ ከዚያ እንደለመዱት በገላዎቻቸው የፍቅር ወሬ ማውራት፡፡ ጨዋታውን

አቆመች፡፡ የሷ እንደሆነ የማያሳስተውን ፈገግታ ፈገግ አለች፡፡ አይን አፋርና ደንገር ያለ ፈገግታ፡፡
ወጣቱ አልቀረባትም፡፡ ጨዋታውንም አልተወም፡፡ የወትሮውን ሳቋን አላስተዋለውም፡፡ የታየው ይወዳት የነበረች፣

አሁን ግን ያስጠላቸው ልጅ ውብ ገላ ነው፡፡ ጥላቻው የተድበሰበሰ ምናምን አልነበረም፡፡ ምርር፣ እርር ያለ ጥላቻ

ነው፡፡ ልትቀርበው ስትል፡- “እዚያው ሁኚ፡፡ በደንብ ልይሽ፡፡” አላት፡፡ ሸርሙጦች እንደሚደረጉት ነው ሊያደርጋት

የፈለገው፡፡ ብዙ ሴቶች ቢያውቅም፣ ከእውነተኛ ሸርሙጦች ጋር ተኝቶ አያውቅም፡፡ እውነተኛ ነጋዴዎቹ ጋ ሄዶ፣

ገንዘብ ከፍሎ፣ ወሲብ ገዝቶ አያውቅም፡፡ ስለ ሸርሙጦች ያለው እውቀት ከንባብ የተገኘና ከሰዎች የሰማው ነው፡፡

እነዚህን ሀሳቦቹን ሊያስታውስ ሞከረ፡፡ ጥቁር የጡት ማስያዣና ጥቁር ፓንት  የለበሰች (እና ጥቁር ስቶኪንግ ያደረገች)

እና ፒያኖ ላይ የምትደንስ ሴት በሃሳቡ መጣችለት፡፡ ትንሿ የሆቴል ክፍል ውስጥ ግን ፒያኖ ብሎ ነገር የለም፡፡ ያለው

የናይለን ጨርቅ ለብሶ፣ ግድግዳውን ተደግፎ የቆመ፣ ትንሽ ጠረጴዛ ነው፡፡ ጠረጴዛው ላይ እንድትወጣ አዘዛት፡፡ ልጅቷ

ልምምጥ አሳየች፡፡ “ከፍዬሻለሁ፡፡” አላት፡፡
የማይረታ የወሲብ ጥማቱን ስታይ ጨዋታውን መቀጠል እንደሚኖርባት ገባት፡፡ ችግሩ እሷ አሁን ጨዋታውን መቀጠል

አልፈለገችም፤ ብትፈልግም እንዴት መጫወት እንደሚገባት ተደናግሯታል፡፡ ሁሉ ነገር ጠፋባት፡፡ እንባ በአይኗ

እንዳቀረረ ጠረጴዛው ላይ ወጣች፡፡ የጠረጴዛው ስፋት ግፋ ቢል አንድ ሜትር ስኩዌር ቢሆን ነው፡፡ በዚህም ላይ

አንደኛው እግሩ ከሌሎቹ ያጥራል፡፡ ጠረጴዛው ላይ ረግታ መቆም አልቻለችም፡፡
ፊት ለፊቱ የተገተረው ራቁት የገላ ማማ ተመችቶታል፡፡ ደንታ ቢስነቱን አባሰው፡፡ ሌሎች ደንበኞች ይህን ገላ እንዴት

ነበር ያዩት? እንዴት ይሆን ሊያዩት የሚፈልጉት? ሌሎች ደንበኞች ይህን ገላ አይተውታል እና ሊያዩት ይችላሉ ብሎ

በጠረጠረው መንገድ ሁሉ አዛዙሮ አየው፡፡ ውርጋጥ ሆነ፡፡ ዝሙት በዝሙት ሆነ፡፡ ቀፋፊ ቃላትን ተናገረ፡፡ እነዚህን

ቃላት ከእሱ ሰምታቸው አታውቅም፡፡ እንቢ ብላ፣ ከዚህ ጭንቅ መገላገል ፈለገች፡፡ ለዚህ እንዲያግዛት በመጀመሪያ

ስሙ ጠራችው፡፡ የመጀመሪያ ስሜን ለመጥራት የሚያስችል ቅርበት የለሽም ብሎ ጮኸባት፡፡ በሀይለኛ ውዝግብ ሆና፣

በከባድ እንባ ሆና የሚለውን አደረገችለት፡፡ አጎነበሰች፡፡ ዳሌዋን ትዊስት ዳንስ እንደሚጫወት ሰው ነቀነቀች፡፡

የጠረጴዛው ጨርቅ አንሸራትቷት ልትወድቅ ስትል፣ ያዛትና እየጎተተ ወደ አልጋው ወሰዳት፡፡
ወሲብ አደረጉ፡፡
ያ የስቃይ ጊዜ፣ ምን ያ የስቃይ ጊዜ፣ ያ የስቃይ ዘመን ስላበቃ ደስ አላት፡፡ አሁን ተመልሰው እንደ ድሮዋቸው መሆን

ይችላሉ፤ ወደ ፍቅራቸው ይመለሳሉ፡፡ አፏን፣ አፉ ላይ ማድረግ ፈለገች፡፡ ልጁ እራሷን ወዲያ ገፋው፡፡ የሚስመው

የሚወዳቸውን ሴቶች ብቻ እንደሆነ ደግሞ ነገራት፡፡ አለቀሰች፡፡ ማልቀስ እንኳ አልተፈቀደላትም፡፡ አሁንም ለወሲብ

ፈለጋት፡፡ ገላዋ በባእድ ሀይል ወረራ ተካሄደበት፡፡ ገላዋ ስሜት የሚባል አደገኛ መሳሪያ በታጠቀ አካል ቅኝ ግዛት ስር

ወደቀ፡፡ ነፍሷ ተቃውሞ አላሰማም፡፡ ፀጥ፡፡ ከዚህ በፊት የሚተዋወቁ የማይመስሉ ገላዎች በወሲብ ተዋሀዱ፡፡ ልጅቷ

ዘመኗን በሙሉ ስትፈራውና ለጉድ ስትሸሸው የነበረ ነገር ተከሰተ፤ ፍቅርና ስሜት የሌለው ወሲብ ማድረግ ቻለች፡፡

ያላንዳች ተቃውሞ፣ ሙሉ ተሳታፊና ተባባሪ ሆና አደገኛ ድንበር ጥሳ አለፈች፡፡ ይህ አይደለም የገረማት፣ ያስደነቃትና

ያስፈራት፤ የፍቅርንና የስሜትን ድንበር ተሻግሮ ያለው ወሲብ አስደማሚ ሆኖ አገኘችው፡፡ ይህን መካድ ብትፈልግም

አልቻለችም፡፡ በህይወቷ እንዲህ የሚያስደስትና የሚያረካ ወሲብ ሰርታ አታውቅም፡፡
ሁሉ ነገር አበቃ፡፡ ወጣቱ፣ ከልጅቷ ላይ ተነሳ፡፡ ተንጠራርቶ መብራቱን አጠፋው፡፡ ፊቷን ማየት አልፈለገም፡፡

ጨዋታው አብቅቷል፡፡ ተመልሰው እንደድሮዋቸው መሆን አይችሉም፡፡ ወደ ድሮው መመለስ ሲያስብ ገና አስፈራው፡፡

ገላዋን እንዳይነካ፣ ገላዋ እንዳይነካው ተጠንቅቆ ነው ጨለማው ውስጥ የተኛው፡፡
በፀጥታ ስታለቅስ ይታወቀዋል፡፡
እጆቿ እንደ ህፃን ልጅ እጆች እየተርበተበቱ ነኩት፡፡ ነኩት፤ ተመለሱ፡፡ ነኩትና  በአልቃሻና ተለማማጭ ድምፅ

በመጀመሪያ ስሙ ጠራችው፡፡ “እኔ እኔ ነኝ …” ብላ ፀጥታውን አጠፋች፡፡
ዝም ብሎ ሰማት፡፡ ድምጽዋ ባዶ ነው፡፡ እርግጠኝነት ብሎ ነገር የለውም፡፡ እኔ እኔ ነኝ ማለት ምን ማለት ነው?

የማይታወቅ ነገርን በሌላ የማይታወቅ ነገር ማብራራት፣ መፍታት፣ መተርጎም፣ መበየን ነው! እኔ እኔ ነኝ ብሎ

ትርጉም፡፡
ድምፅ አውጥታ ማልቀስ ጀመረች፡፡ እነዚያን ረብ የለሽ ስሉስ ቃላት ትደጋግማለች፡፡
“እኔ እኔ ነኝ …”
ወጣቱ ሀዘኔታ ከየት ያምጣ? ልጅቷን ዝም ለማሰኘት እንዲረዳው ሀዘኔታን ከሩቅ፣ በጣም ከሩቅ ጠራው (በቅርቡ

አንዳችም መራራት የሚባል ነገር አልነበረም፡፡)
አስራ ሶስት የእረፍት ቀናት ይቀሯቸዋል፡፡
(የእንግሊዝኛው ርእስ፡- The Hitchhiking Game)

ስለ ደራሲው፡-
ሚላን ኩንዴራ እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 1 ቀን 1929 ዓ.ም. ቼኮዝሎቫኪያ ውስጥ ተወለደ፡፡ አባቱ ታዋቂ ፒያኖ ተጫዋች ነበር፡፡

ሚላን ኩንዴራም ወጣት እያለ ሙዚቃ ተምሯል፡፡ ሚላን ኩንዴራ የአጫጭርና የረዣዥም ልብ-ወለዶች ደራሲ፣ ፀሀፌ

ተውኔት፣ ገጣሚና ወግ ፀሀፊ ነው፡፡ ታዋቂ የሆነውም፣ ለስደት የበቃውም በ1967 በታተመው The Joke በሚለው

መፅሀፉ ነው፡፡ ይህ መፅሀፉ ከደርዘን በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡ ወደ ፊልምም ተቀይሯል፡፡ የፊልሙን ፅሁፍ

የፃፈውም፣ ዳይሬክት ያደረገውም እራሱ ነበር፡፡ በ1973 Life is Elsewhere በሚለው መፅሀፉ በፈረንሳይ ሀገር The

Medicis Award ተሸልሟል፡፡ ሚላን ኩንዴራ ከፃፋቸው መጻሀፍት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡- The Farwell

Party (1976)፣ The Book of Laughter and Forgetting (1979)፣ The Unbearable Lightness of Being

(1984)፣ Immortality (1990)፣ Identity (1997)፣ Ignorance (2000) እና The Festival of Insignificance

(2013)::




Read 4547 times