Saturday, 18 February 2012 10:36

አዴሌ 6 የግራሚ ሽልማቶች ወሰደች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

እንግሊዛዊቷ አቀንቃኝ አዴሌ የዛሬ ሳምንት በተካሄደው የግራሚ ሽልማት ላይ በስድስት ዘርፎች በማሸነፍ ፊት አውራሪ ሆነች፡፡ ሆኖም በማግስቱ ለአምስት አመታት ሙዚቃን በመተው የፍቅር ህይወቴን ለማጣጣም ወስኛለሁ ማለቷ ለብዙዎች ዱብ እዳ ነበር፡፡ በዊትኒ ሂውስተን ሞት ዋዜማ የተካሄደው የግራሚ ምሽት የሃዘን ድባብ ያጠላበት እንደነበር ተገልጿል፡፡ ይሁንና ዝግጅቱን  40 ሚሊዮን ተመልካች እንደታደመው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሎስአንጀለስ ውስጥ በሚገኘው ስቴፕልስ የተባለ የህክምና ማዕከል አዴሌ በጉሮሮዋ ላይ የቀዶ ህክምና ካደረገች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በግራሚ ምሽት የተጫወተች ሲሆን ኒኪ ማንጅ፤ ፖል ማካርቲኒ፤ ቴይለር ስዊፍት፤ ክሪስ ብራውን፤ ኮልድ ፕሌይና ሪሃናም በዕለቱ አቀንቅነዋል፡፡አዴሌ በአንድ የግራሚ ምሽት 6 ሽልማት በመሰብሰብ ከቢዮንሴ ጋር ክብረወሰን ተጋርታለች፡፡

በ1984 ዓ.ም ማይክል ጃክሰን፣ በ2000 ዓ.ም ደግሞ ካርሎስ ሳንታና ስምንት የግራሚ ሽልማቶች በአንድ ምሽት ወስደው እንደነበር ይታወሳል፡፡ አርቲስቷ በከፍተኛ የአልበም ሽያጭ ገበያውን በሚመራው “21” የተሰኘ አልበሟ የ”ዓመቱ ምርጥ አልበም”፣ “ሮሊንግ ዲፕ” በሚለው ዘፈኗ የ”ዓመቱ ምርጥ ሪኮርድ” እና “ምርጥ ዘፈን” ያገኘቻቸው ሽልማቶች ትልቅ ግምት አስገኝተውላታል፡፡ “21” በሳምንት ሩብ ሚሊየን እየተሸጠ ለ20 ሳምንታት ገበያውን ሲመራ ቆይቷል፡፡ አዴሌ ሰሞኑን ለአምስት አመት ከሙዚቃ ኢንዱስትሪው እንደምትርቅ በመናገሯ ገበያው እንዳይቀዘቅዝባት የተፈራ ሲሆን በእረፍት ጊዜዋ ትዳር መስርታና ልጆች ወልዳ መነሳት እንደምትፈልግ ገልፃለች፡፡  በዘንድሮው 54ኛ ግራሚ “የዓመቱ ምርጥ የአር ኤንድ ቢ አልበም” ተብሎ የተሸለመው የክሪስ ብራውን “ፌም” የተሰኘ አልበም ነው፡፡ የካናዬ ዌስት “ማይ ቢውቲፉል ዳርክ ትዊስትድ ፋንታሲ” የዓመቱ ምርጥ የራፕ አልበም ተብሏል፡፡ “ዎክ” በተባለው ዜማ የዓመቱን ምርጥ የሮክ ሙዚቃ ያሸነፉት ፉ ፋይተርስ፤ “ዌስቲንግ ላይት” በተባለው አልበማቸው የዓመቱ ምርጥ የሮክ አልበም ሽልማትን አግኝተዋል፡፡

 

 

 

Read 1300 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 10:41