Saturday, 18 February 2012 10:36

ኦስካር ከቲቪ ይልቅ በኢንተርኔት ትኩረት እያገኘ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በየዓመቱ የሆሊዉድ ፊልሞችን በተለያዩ ዘርፎች እያወዳደሩ የሚሸልሙት ትላልቆቹ የሽልማት ኩባንያዎች በሽልማት ሥነስርዓታቸው ዋዜማና በዕለቱ ዝግጅታቸውን በቀጥታ የቲቪ ሥርጭት በማስተላለፍ ለጣቢያዎቹም የገቢ ምንጭ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ ግን የሽልማት ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ሶሻል ሚዲያዎች እያዞሩ መጥተዋል፡፡ ሎስ አንጀለስ ታይምስ እንደሚለው በዋና የሽልማት ዘርፎች የሚሸለሙትን ፊልሞች ለመለየት የፊልም ኩባንያዎች ከፍተኛ የኢንተርኔት ዘመቻ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ ኦስካር ባሉ ታላላቅ ሽልማቶች የቴሌቭዥን ታዳሚው ቁጥር በየዓመቱ በሚሊዮኖች እየቀነሰ መምጣቱን ሲኤንኤን ጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል ፌስቡክ እና ትዊተር የተባሉት የሶሻል ሚዲያ መድረኮች በሽልማቶቹ ዋዜማና ማግስት ከቲቪ ጣቢያዎች በላቀ ትኩረት እያገኙ ናቸው ተብሏል፡፡

የጆርጅ ኩሉኒ “ዲሴንዳንትስ”፤ የብራድ ፒት “መኒ ቦል”ና “ዘ ኸልፕ” የተሰኙት ፊልሞች በመላው አሜሪካ “በምርጥ ፊልም” ዘርፍ የኦስካር ሽልማትን የራሳቸው ለማድረግ በነፍስ ወከፍ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ በጀት መድበው በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያዎች የፕሮሞሽን ዘመቻ እያካሄዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በተያያዘ ዜና በብሪቲሽ አካዳሚ ኦፍ ፊልም ኤንድ ቴሌቭዥን አርት በሚዘጋጀው “ባፍታ አዋርድስ” ላይ “ዘ አርቲስት” ከታጨባቸው 12 ሽልማቶች ሰባቱን በመውሰድ ስኬት ተቀዳጅቷል፡፡ ፊልሙ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው የኦስካር ሽልማት ላይ በተመሳሳይ ሊሳካለት እንደሚችል ተገልጿል፡፡ “ዘ አርቲስት” ፊልምን ዲያሬክት ያደረገው ማይክል ሃዛኒፊከስ በ”ባፍታ” ሽልማት በምርጥ ዲያሬክተርነት እንደተሸለመ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የእንግሊዟን ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር በመወከል “አይረን ሌዲ” በተባለው ፊልም ላይ የተወነችው ሜሪል ስትሪፕ እንዲሁ በምርጥ ተዋናይትነት የ”ባፍታ” ተሸላሚ ሆናለች፡፡ የማርቲን ስኮርሴሲ ፊልም “ሁጎ” በዘጠኝ የሽልማት ዘርፎች ታጭቶ የነበረ ሲሆን በሁለቱ ተሳክቶለታል፡፡ “ባፍታ አዋርድስ” የኦስካር አሸናፊዎችን በመጠቆም ረገድ ብዙም ፍንጭ አይሰጥም የሚለው ቢቢሲ፤ ለዚህም ዋናው ምክንያት ከአሜሪካ ውጪ በተሰሩ ፊልሞች ላይ በማተኮሩ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

 

 

 

Read 1261 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 10:38