የጆርጅ ኩሉኒ “ዲሴንዳንትስ”፤ የብራድ ፒት “መኒ ቦል”ና “ዘ ኸልፕ” የተሰኙት ፊልሞች በመላው አሜሪካ “በምርጥ ፊልም” ዘርፍ የኦስካር ሽልማትን የራሳቸው ለማድረግ በነፍስ ወከፍ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ በጀት መድበው በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያዎች የፕሮሞሽን ዘመቻ እያካሄዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በተያያዘ ዜና በብሪቲሽ አካዳሚ ኦፍ ፊልም ኤንድ ቴሌቭዥን አርት በሚዘጋጀው “ባፍታ አዋርድስ” ላይ “ዘ አርቲስት” ከታጨባቸው 12 ሽልማቶች ሰባቱን በመውሰድ ስኬት ተቀዳጅቷል፡፡ ፊልሙ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው የኦስካር ሽልማት ላይ በተመሳሳይ ሊሳካለት እንደሚችል ተገልጿል፡፡ “ዘ አርቲስት” ፊልምን ዲያሬክት ያደረገው ማይክል ሃዛኒፊከስ በ”ባፍታ” ሽልማት በምርጥ ዲያሬክተርነት እንደተሸለመ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የእንግሊዟን ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር በመወከል “አይረን ሌዲ” በተባለው ፊልም ላይ የተወነችው ሜሪል ስትሪፕ እንዲሁ በምርጥ ተዋናይትነት የ”ባፍታ” ተሸላሚ ሆናለች፡፡ የማርቲን ስኮርሴሲ ፊልም “ሁጎ” በዘጠኝ የሽልማት ዘርፎች ታጭቶ የነበረ ሲሆን በሁለቱ ተሳክቶለታል፡፡ “ባፍታ አዋርድስ” የኦስካር አሸናፊዎችን በመጠቆም ረገድ ብዙም ፍንጭ አይሰጥም የሚለው ቢቢሲ፤ ለዚህም ዋናው ምክንያት ከአሜሪካ ውጪ በተሰሩ ፊልሞች ላይ በማተኮሩ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡