Saturday, 23 January 2016 13:22

ኢቢሲ፣ በ50ኛ አመት በዓሉ ትርፍ አገኛለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

     ኢቢሲ፣ 50ኛ ዓመቱን ለማክበር ከሚካሄዱ ዝግጅቶች ትርፍ እንደሚያገኝ የገለፀ ሲሆን፤ ከፍተኛ የገንዘብ ምንጮቹና ዋና ስፖንሰሮቹ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያ ክልል መስተዳድሮች እንዲሁም ኢትዮቴሌኮም ሆነዋል፡፡ ከዋናዎቹ “የፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰሮች” በተጨማሪ፤ ሌሎች የክልል መስተዳድሮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቢራ ኩባንያዎች፣ እንዲሁም ሌሎች መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶች ስፖንሰር እንደሚሆኑለት ታውቋል፡፡
በአሉ በጭፈራና በመዝናኛ ዝግጅቶች ብቻ እንደማይከበር የኢቢሲ ሃላፊዎች ገልፀው፤ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማገናዘብ ሰብአዊ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል - ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፡፡
2200 ሰራተኞች የደም ልገሳ እያከናወኑ ናቸው ያሉት ሃላፊዎቹ፤ ከሰራተኞች በተዋጣ ገንዘብ፣ የተለያዩ የረድኤት ተቋማት ድጋፍ ያገኛሉ ብለዋል፡፡
ከጥር 24 እስከ 29 ቀን ለሚከበረው በአል ከታሰቡት ዝግጅቶች መካከል አንዱ፣ የኢቢሲ የሃምሳ ዓመት ታሪክ የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ነው፡፡ በ “ሰራዊት መልቲ ሚዲያ” የሚቀርበውን ኤግዚቢሽን፤ ከሃምሳ ሺ በላይ ሰዎች ይመለከቱታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
የጥያቄና መልስ ውድድሮች፣ የተለያዩ ዶክመንተሪ ፊልሞች፣ የጥናታዊ ፅሁፎች ውይይትም፣ በበዓሉ ይካተታሉ ተብሏል፡፡
“ከዘመናዊነት አንፃር ብዙ የሚቀሩት ነገሮች እንዳሉ እናውቃለን” ያሉት የኢቢሲ የስራ ሃላፊ አቶ ኤልያስ አዋቶ፤ “በቴክኖሎጂ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ፣ አለማቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡ ኢቢሲ፣ ነፃነቱንና ገለልተኝነቱን ለማስጠበቅ ደንቦችና መመሪያዎችን እያዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል - ሃላፊዎቹ፡፡

Read 3393 times