Saturday, 23 January 2016 13:21

የሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ከህገ-ወጥ ተግባሩ እንዲታቀብ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

•    “ኮረም ሳይሞላ የተወሰነ ውሳኔ ስለሆነ ህገ ወጥነቱን ተቃውመናል” ኢ/ር ይልቃል

       የሰማያዊ ፓርቲ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን፤ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሥልጣኑ ውጭ በመሄድ ከሚፈጽመው ህገ-ወጥ ተግባር እንዲታቀብ አስጠነቀቀ፡፡ “የፓርቲው የስነ-ስርዓት ኮሚቴ በምክር ቤት አባላቱ ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ኮረም ያልተሟላበት ስለሆነ የስራ አስፈፃሚው ህገወጥነቱን ተቃውሟል” ብለዋል - የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፡፡
የሰማያዊ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ትላንት ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ ከጠቅላላ ጉባኤው ቀጥሎ ከፍተኛ ስልጣን ያለው ብሄራዊ ምክር ቤቱ፤ ከፓርቲው ህግና ደንብ ውጭ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከፋፋይና በህዝቡ መካከል ጥላቻን የሚፈጥር ፅሁፍ አሰራጭተዋል ባላቸው 4 አባላት ላይ ክስ መስርቶ፣ የስነ ሥርዓት ኮሚቴው ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ አባላቱ እንዲባረሩ መወሰኑን አስታውሶ፤ ሥራ አስፈፃሚው ከተሰጠው ስልጣን ውጭ  ውሳኔውን አልቀበልም ማለቱ ህገወጥነት ነው ብሏል፡፡
ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽኑ፤ አንደኛው ተሰናባች አቶ ዮናታን ተስፋዬ አሁን ባለበት ሁኔታ ራሱን መከላከልም ሆነ ይግባኝ መጠየቅ ስለማይችል በሱ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የጠየቅናቸው የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ “ስራ አስፈፃሚው፤ ችግር ሲፈጠር ለኦዲትና ምርመራ ኮሚሽኑ ይግባኝ አይባልም ወይም የስነ-ስርዓት ኮሚቴው የመወሰን መብት የለውም አላለም፤ ውሳኔው መተላለፍ ያለበት የስነ-ስርዓት ኮሚቴው ምዕላተ ድምፅ ሲሞላ ነው፤ ሆኖም ባልተሟላ ድምፅ ውሳኔው በመተላለፉ ህገወጥነቱን ተቃውመናል” ብለዋል፡፡ በፓርቲው ህግና ደንብ መሰረት ውሳኔ ለማስተላለፍ ምዕላተ ድምፁ 50 + 1 መሆን እንዳለበት ያብራሩት ኢ/ሩ፤ በምክር ቤት አባላቱ ላይ ውሳኔ ያስተላለፉት ከሰባቱ የስነ-ሥርዓት ኮሚቴ አባላት ሶስቱ ብቻ እንደነበሩና አንደኛው አባል በሂደቱም በፊርማውም እንዳልተሳተፈ ምስክርነቱን ሰጥቷል ይላሉ፡፡ “እኛ ተቃውሞ ያነሳነው ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ እንጂ ገና በእንጥልጥል ላይ ባለ ጉዳይ ባለመሆኑ ህጉን ተከትለን እየሰራን ለመሆናችንን ማሳያ ነው” ሲሉም ኢ/ር ይልቃል - ተሟግተዋል፡፡ የፓርቲው የስነ-ስርዓት ኮሚቴው በአባላቱ ላይ ውሳኔ ሲያስተላልፍ ኮረም መሙላት አለመሙላቱን በተመለከተ የጠየቅናቸው የኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ሀና ዋለልኝ፤ በውሳኔው ላይ ከሰባቱ የኮሚቴ አባላት አራቱ መገኘታቸውንና አራቱም በውሳኔው መስማማታቸውን ገልፀው፣ ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ሲሳይ ካሴ የተባሉት አባል ከውሳኔው ማፈንገጣቸውን እንዲሁም ውሳኔውን መካዳቸውን ጠቁመዋል፡፡ “ያም ሆነ ይህ ውሳኔው ሲተላለፍ ከሰባት አባላት አራቱ መገኘታቸው ኮረም እንደሞላ ያሳያል” ያሉት ሰብሳቢዋ፤ አቶ ሲሳይ ካሴ ውሳኔውን ቢክዱም ሶስታችን በመስማማታችን ኮረም አልሞላም መባሉ አግባብ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

Read 3841 times