Saturday, 23 January 2016 13:21

ለኤፍኤም ሬድዮ ባለቤትነት ከተወዳደሩ ድርጅቶች መስፈርቱን ያሟላ አልተገኘም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታ ሊወጣ ነው
    ለ13 የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በወጣው ጨረታ የተሳተፉ 4 ድርጅቶች የተጠየቀውን መስፈርት ሳያሟሉ በመቅረታቸው የብሮድካስት ባለስልጣን ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታ ሊያወጣ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ባለፈው ህዳር ወር ከአዲስ አበባ 6፣ ለክልል በተለያዩ ቋንቋዎች ለሚሰራጩ 7 ኤፍኤም  ሬዲዮ ጣቢያዎች ፍቃድ ለመስጠት ታስቦ በወጣው ጨረታ ላይ ለመሳተፍ ሰነድ ከገዙ 39 ድርጅቶች መካከል አራቱ ብቻ ፕሮጀክታቸውን በማስገባት በጨረታው መወዳደራቸውን የባለስልጣኑ የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣፋ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የጨረታ ሰነድ ገዝተው ከነበሩት 39 ድርጅቶች ውስጥ 33ቱ አዲስ አበባ ላይ ለመስራት አቅደው የነበረ ሲሆን 6ቱ በተለያዩ የክልል ከተሞች ለመስራት አስበው እንደነበር ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻ ግን አራቱ ብቻ በጨረታው የተሳተፉ ሲሆን ሁሉም በፋይናንስ አቅም ምክንያት መስፈርቱን ሳያሟሉ ቀርተዋል ያሉት አቶ ወርቅነህ፤ በጨረታው ለመሳተፍ የሚፈልጉ ተወዳዳሪዎች 8 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡ የራሳቸው ህንፃና ስቱዲዮ ያላቸው ደግሞ በጥሬ ገንዘብ እስከ 6 ሚሊዮን በር ካፒታል ቢያቀርቡ ተቀባይነት ይኖረዋል ብለዋል ኃላፊው፡፡
የንግድ ኤፍኤም ሬዲዮ ፍቃድ ለማግኘት የሚፈልጉ ድርጅቶች ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶች፤ በብሮድካስት ፍቃድ እና በሬዲዮ ፍቃድ አዋጆች ላይ በዝርዝር መገለፃቸውን የጠቆሙት አቶ ወርቅነህ፤ ዋና ዋናዎቹ የፋይናንስ አቅም፣ የሙያ ታማኝነት፣ የስራ ልምድ፣ የስቱዲዮና የመሳሪያዎች ዘመናዊነት እንዲሁም በፕሮግራም ረገድ ማህበራዊ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ ይዘቶችን ማካተት የሚሉ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ያሉ ፍላጎቱና አቅሙ ያላቸው ድርጅቶች፤ በድጋሚ በሚወጣው ጨረታ ላይ እንዲሳተፉ ባለስልጣን መ/ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Read 2867 times