Saturday, 23 January 2016 13:18

የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያውና ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 10 እየተወዛገቡ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

-    “የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቶኝ ነው ሥራ የጀመርኩት” (ባለሃብት)
-     “የግንባታ ፈቃድ ሳያገኙ ነው መገጣጠሚያውን የገነቡት” (ወረዳው)

ኒግማ አግሮ ኢንዱስትሪ የተባለው የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያና የጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 10 መስተዳደር በህገወጥ ግንባታ ጉዳይ እየተወዛገቡ ነው፡፡ ወረዳው ባለፈው ሰኞ ኩባንያውን በግሬደር ማፍረስ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ባለሀብቱ ዶ/ር ብርሃኑ ዘውዴ፤ በወረዳው የሚገኘውን 7500 ካ.ሜ ቦታ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ለብሎኬትና ሲሚንቶ ማምረቻነት ሲጠቀሙበት እንደቆዩ ገልፀው፤ በግማሹ ቦታ ላይም የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡  የወረዳ 10 ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት በበኩሉ፤ “የግንባታ ፈቃድ ሳያገኙ ህገ-ወጥ ግንባታ ሰርተዋል” በሚል ሰኞ ዕለት ፋብሪካውን በግሬደር ማፍረስ መጀመሩን ዶ/ር ብርሃኑ ገልፀዋል፡፡
ባለሀብቱ ከ19 ዓመታት በፊት ቦታውን በሊዝ ተመርተው ብሎኬትና የሲሚንቶ ውጤቶች ሲያመርቱ መቆየታቸውን የሚናገረው የኒግማ አግሮ ኢንዱስትሪ ማርኬቲንግና ሴልስ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ታምራት፤ በኋላም ኢንቨስትመንታቸውን ለማሳደግና የተሻለ ሥራ ለመስራት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ፈቃድ ማውጣታቸውን ይናገራሉ፡፡
የግንባታ መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከውጭ  ከቀረጥ ነፃ በማስገባትም ኩባንያቸው የደቡብ አኮሪያ ሥሪት የሆነውን ዳው እና የአሜሪካውን ቼቭሮሌት መኪኖች መገጣጠም እንደጀመረ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ ከኢትዮጵያዊው ባለሀብት ጋር ዩክሬናዊና እስራኤላዊ ዜጎች በሽርክና ሊሰሩ ተስማምተው፣ ለኢንቨስትመንቱ 1.5 ሚ. ዶላር እንደወጣበት አስረድተዋል፡፡
ሆኖም ፋብሪካው የግንባታ ፈቃድ ሳያገኝ የተገነባ በመሆኑ በሦስት ቀን ውስጥ እንዲያፈርሱ ወረዳው ደብዳቤ እንደፃፈላቸው የማርኬቲንግና ሴልስ ኃላፊው ገልፀው፤ ባለሀብቱምየኢንቨስትመንት ፈቃድ ለሰጣቸው ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የአቤቱታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ይናገራል፡፡ ኤጀንሲውም ለጉለሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ፤ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያው የውጭ ምንዛሬን በማዳን፣ የስራ እድል በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሶ፤ አገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥረት እያደረገች ባለችበት ወቅት እንዲህ አይነት ችግር መፈጠሩ የውጭ ባለሀብቶች በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖራቸውና ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ስለሚያደርግ፤ የመኪና መገጣጠሚያው ህገ - ወጥ ነው በሚል ለኩባንያው የተፃፈው የሦስት ቀን ማስጠንቀቂያ ተነስቶ፣ ስራቸውን እንዲቀጥሉ ለወረዳው አሳስቦ ነበር፡፡
ወረዳው ግን ማሳሰቢያውን አልተቀበለውም፡፡ ባለፈው ሰኞ በድጋሚ ግንባታው ህገ - ወጥ ነው በሚል ኩባንያውን ግሬደር በማፍረሱ ግምቱ ከፍተኛ የሆነ ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን በቦታው ለተገኙ ጋዜጠኞች ያስረዱት አቶ ዳንኤል፤  ንብረቶቹ በድጋሚ በጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርገው ማፍረሳቸው ከአንድ ደንብ አስከባሪ ዜጋ አይጠበቅም ብለዋል፡፡
ባለሀብቱ ለቦታው ካርታ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ መቆየታቸውንና ጉዳዩ ሲንከባለል ዛሬ ላይ መድረሱን አቶ ዳንኤል አስረድተዋል፡፡ የወረዳ 10 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሻምበል አበበ በበኩላቸው፤ ህገ-ወጥ ግንባታ ነው ብለን በተደጋጋሚ በደብዳቤ ብናስጠነቅቅም ሊያቆሙ ባለመቻላቸው ለማፍረስ ተገደናል ብለዋል፡፡
ለምን መጀመሪያውኑ እርምጃ አልወሰዳችሁም በሚል የተጠየቁት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤  “በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል፤ ይህን አይነት ግንባታ ለመስራት ፈቃድ ማግኘት አለባቸው፤ በወቅቱ እርምጃ ያልወሰዱ የወረዳው ኃላፊዎችም በግምገማ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል” ብለዋል፡፡
ባለሀብቱ ወረዳውን በፍ/ቤት የከሰሱ ሲሆን ወረዳው የኩባንያውን ግንባታ ማፍረሱን እንዲያቆምና ለተከሰሰበት ጉዳይ ጥር 27 ጠዋት ፍ/ቤት ቀርቦ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ተብሏል፡፡

Read 2825 times