Saturday, 23 January 2016 13:18

12 የአድዋ ተጓዦች ደብረ ብርሃን ደርሰዋል

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(1 Vote)

በመጪው የካቲት 23 የሚከበረውን 120ኛ ዓመት የአድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ፣ ባለፈው ሰኞ 12 የእግር ተጓዦች ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ አድዋ መገስገስ የጀመሩ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ደብረብርሃን መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ “ጉዞ አድዋ” በሚል ስያሜ በየዓመቱ ወደ አድዋ የሚደረገው ጉዞ፣ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ የጉዞው አዘጋጅ የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤መነሻውን አዲስ አበባ ጣይቱ ሆቴል ባደረገው የተጓዦች ቡድን ውስጥ 10 ወንዶችና 2 ሴቶች የተካተቱ ሲሆን የካቲት 23 አድዋ
የሚገቡት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከተውጣጡ 120 የሚደርሱ ሰዎች ጋር በመሆን ነው፡፡
“የጉዞው አላማ፤ የአድዋ ድል በአልን የዕረፍት ቀን እያደረጉ ከማሳለፍ ባለፈ፣ የህዝብ በአል ሆኖ
እንዲከበርና ወደፊትም ትልቅ የበአል ስሜት በመፍጠር አድዋ ከተማን የአፍሪካ የነፃነት ማዕከል ማድረግ ነው” ብሏል - ያሬድ ሹመቴ፡፡ በቀጣይ ዓመታት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በአድዋ
ድል በዓል ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ መታቀዱን የጠቆመው ያሬድ፤አባቶቻችን ይህንን ሁሉ ንገድ
በባዶ እግራቸው ተጉዘው ጠላትን ድል መንሳታቸው ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን  ፍሪካውያንም
ጭምር ታላቅ የነጻነት አርማ በመሆኑ አፍሪካውያን በየዓመቱ አድዋ እየመጡ የአባቶቻችንን የጀግንነት ስሜት መጋራት ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት በተደረገው “ጉዞ አድዋ” 6 ሰዎች
(5 ወንድና 1 ሴት) ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን የአድዋ ድል በዓልን ለመዘከር ከአዲስ አበባ አድዋ 1ሺ10 ኪ.ሜትር በእግራቸው ተጉዘዋል፡፡

Read 1986 times