Saturday, 16 January 2016 10:42

የሂችሀይኪንግ ጨዋታ

Written by  ደራሲ፡- ሚላን ኩንዴራ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(0 votes)

   (Hitchhike:- መንገድ ዳር እየቆሙ፣ የመኪና አገልግሎት እየለመኑ፣ ተባበሩኝ እያሉ መጓዝ ነው፡፡ ሊፍትም ይባላል-ተርጓሚው፡፡)
የስፖርት መኪናው የነዳጅ መጠን ጠቋሚ መርፌ ድንገት ‘ባዶ’ የሚለው ፅሁፍ ላይ ተቀሰረ። የመኪናው የነዳጅ ፍጆታ ያናድዳል፡፡ አሁንስ ሳያሳብደኝ አይቀርም አለ ወጣቱ ሾፌር፡፡ “መንገድ ላይ እንዳያልቅብን በርከት አድርገህ አስቀዳ” አለች አብራው ያለችው ልጅ (ሀያ ሁለት አመት ቢሆናት ነው፡፡) መንገድ ላይ፣ በተደጋጋሚ ነዳጅ እንዳለቀባቸው አስታወሰችው፡፡ ሺህ ምንተሺህ ጊዜ ቢያልቅ ጉዳዩ እንዳልሆነ ነገራት፡፡ ሌላ ጊዜ ቢሆን የሚያበሳጩት ችግሮች ከእሷ ጋራ ሲሆኑ ለዛ ይኖራቸዋል፡፡ ከአንቺ ጋር ሲሆን ያስደስቱኛል አላት፡፡ ማራኪ ተሞክሮዎች ይሆናሉ አለ፡፡ ልጅቷ አልተስማማችም፡፡ ነዳጅ መንገድ ላይ ባለቀብን ቁጥር ማራኪ የተባለውን ተሞክሮ አደርግ የነበረው እኔ ነበርኩ አለች፡፡ ነዳጅ ባለቀባቸው ቁጥር እሱ ይደበቅና እሷ በውበቷ ትቆምራለች፡፡ አልፎ ሂያጅ ባለመኪና ሂችሀይክ ትጠይቃለች፡፡ ቅርብ የተገኘው ነዳጅ መሸጫ ጋ ትወርድና፣ ነዳጅ ገዝታ፣ ሂችሀይክ ጠይቃ ትመለሳለች፡፡ ስታወራ ነገርየው እጅግ ያስመረራት ትመስላለች፡፡ ይህን ያስተዋለው ወጣት ባለመኪኖቹ ያስቸግሩሽ ነበር እንዴ ብሎ ጠየቃት። እንዲያውም አንዳንዶቹ በጣም አሪፍ እንደነበሩ ነገረችው፡፡ ከምርጦቹ ባለመኪናዎች ጋር ‘የሆነ ነገር’ ለማድረግ ግን ትሸከመው የነበረው ነዳጅ የተሞላ እቃ እንቅፋት ይሆንባት ነበር፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጊዜው ያጥርና፣ ምንም ነገር ከማድረጋቸው በፊት፣ እሱ ያለበት ጋ ይደርሱና፣ ሰዎቹን በሀዘንና በእንባ ልትለያቸው ግድ ይሆናል፡፡ “አሳማ፡፡” አላት ልጁ። አሳማ አይደለሁም ብላ አጥብቃ ተቃወመች። እሱ አሳማ መሆኑን ግን የዚህም፣ የሌላም አለም ህዝብ እንደሚመሰክር አስረዳች፡፡ ስንት ሴቶች መንገድ ላይ እንዳስቆሙትና ለስንቶቹ ሂችሀይክ እንደሰጠ እግዚአብሔርና የመኪናው ወንበሮች ይቁጠሩት፡፡ በአንድ እጁ መሪ እንደያዘ፣ በሌላኛው ትከሻዋን አቀፋት፡፡ ቀስ ብሎ ግንባሯን ሳማት። እንደምታፈቅረው ያውቃል፡፡ የመጣባት ሀሳብ ቅናቷን ከተኛበት ቀስቅሶታል፡፡ ቅናት ደባሪ ነገር እንደሆነ ያውቃል፡፡ ቅናት ቅጥ-አንባር ካለው (እናም ደግሞ በትህትና ከተደገፈ) ከነኮተቱ ደስ ይላል፡፡ ገና ሀያ ስምንት አመቱ ነው፡፡ እሱ ግን ሀያ ስምንት አመት ሙሉ ስለኖረና፣ በዚህ ረዥም እድሜውም ብዙ ሴቶች ስላየ አንድ ወንድ ስለሴቶች ሊያውቅ የሚችለውን ሁሉ ጠንቅቄ አውቃለሁ ብሎ ያስባል፡፡ አጠገቡ ያለችው ልጅ ብዙ ሴቶች ላይ ፈልጎ ያጣው ነገር አላት፡- ንፅህና፡፡ ንፅህት ናት፡፡ መንፈሷ ገና አልጎደፈም፡፡
የመኪናው የጋዝ መጠን ጠቋሚ መርፌ ባዶ ላይ እንደሆነ፣ እየሄዱ ሳሉ ወጣቱ በስተቀኝ በኩል፣ በአራት መቶ ሜትር እርቀት ላይ የነዳጅ መሸጫ ጣቢያ መኖሩን የሚያበስር ምልክት አየ፡፡ የነዳጅ መሸጫ ጣቢያው ጋ ደርሰው ሲታጠፉ፣ ልጅቷ ደስታዋን ገልፃ አልጨረሰችም ነበር፡፡ ከነዳጅ መቅጃው ትንሽ ራቅ ብለው ቆሙ፡፡
ትልቅ፣ በነዳጅ የተሞላ የብረት ታንክ የተሸከመ፣ ግዙፍ ቱቦ የተገጠመለት፣ ከባድ መኪና የጣቢያውን ማጠራቀሚያዎች እየሞላ ነበር፡፡ ወጣቱ፡- “መጠበቅ ሳይኖርብን አይቀርም፡፡” እያለ ከመኪናው ወረደ። “ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?” ብሎ ጠየቀ ባለ ማንገቻ ቱታ የለበሰውን ሰውዬ። “ትንሽ ብቻ፡፡” አለ ሰውዬው፡፡ “ትንሽ ብቻ የሚል ነገር ከሰማሁ ትንሽ ብቻ ነው የቆየሁት፡፡” አለ ወጣቱ። መኪናው ውስጥ ሆኖ ለመጠበቅ ወስኖ ሲዞር፣ ልጅቷ ከመኪናው ስትወርድ አያት፡፡ ልጅቷ፡- “እስከዚያው ድረስ እኔ ትንሽ ልንቀሳቀስ፡፡” አለች፡፡ “ወዴት?” አውቆ ነው የጠየቃት፡፡ አይነ አፋር ናት፡፡ ስታፍር ሊያያት ፈልጓል፡፡ አብረው መሆን ከጀመሩ አንድ አመት አልፏቸዋል፡፡ አሁንም ግን ታፍረዋለች። አይን አፋርነቷን ይወድደዋል፡፡ አንድም፡- እስከዛሬ ከሚያውቃቸው ሴቶች ልዩ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ አንድም፡- ይህቺን አልፎ ሂያጅ አለም ያጣፍጥለታል፡።ልጅቷን በጉዟቸው ላይ በጣም ያማረራት ነገር (ወጣቱ ያለማቋረጥ፣ አንድም ቦታ ሳያቆም ለረዥም ጊዜ ያሽከረክራል) እጅብ ያሉ ዛፎች ያሉበት አካባቢ መኪናውን እንዲያቆምላት መጠየቅ ነው፡፡ እጅግ የተገረመ መስሎ ለምን መኪናውን እንዲያቆም እንደፈለገች ይጠይቃታል፡፡ ግልፅ ነው፤ ታፍራለች። ማፈር የቂሎችና የፋራዎች እንደሆነ ብታውቅም፣ ልታስቀረው አልቻለችም፡፡ መስሪያ ቤትም ይህን ባህሪዋን ስለሚያውቁ ምክንያት ፈልገው ያሳፍሯትና ይስቁባታል፡፡ ዘመኗን ሁሉ ልክ እንደ ሌሎች ሴቶች ሰውነቷን ተቀብላ ለመኖር ጥራለች፡፡ እንዲያውም ለዚህ የሚያግዛት አንድ የራሷ መላ ፈጥራለች፡፡ ደጋግማ ይህን ለራሷ ትላላች፡- ‘ማንኛውም ሰው የሚወለደው ከብዙ ሚሊዮን ገላዎች አንዱን ለብሶ ነው፡፡ ሚሊዮን ክፍሎች ካሉት ሆቴል ውስጥ የሚደርሰን አንዱ ክፍል ነው፡፡ አንድ ሰው ይዞ የሚወለደውን ገላ አይመርጥም፡፡ በእድል አንዱ ይደርሰዋል፡፡ ገላችን በእጣ ያገኘነው ነው፡፡ ገላ ለባሹን አይወክልም፡፡ ብዙ ተሰርተው የተቀመጡ ገላዎች አሉ፤ ከዚያ መሀል አንዱን አንስተው አንዱ ላይ ይለጥፉታል፡፡ ስጦታ እንኳ አይደለም፡፡ ተውሶ ነው፡፡ ተጠቅመንበት የሆነ ቀን እንመልሰዋለን፡፡’ይህ ሀሳቧን ለራሷ እልፍ አእላፍ ጊዜ ነግራለች። ይህ ፍልስፍናዋም አልሰራላትም፡፡ የገላ-አእምሮ ሁለትዮሽነት  ለእሷ ባዕድ ሀሳብ ነው፡፡ እሷ ሁሌም አሀዳዊ ናት፡፡ ገላ ብቻ፡፡ ስጋ ብቻ፡፡ ሰውነት ብቻ። ለዚህም ነው ሰውነቷን በነፃነት፣ አቅልላ መሸከም ያቃታት፡፡
ሁሌም ትሸበራለች፡፡ ይህ መሸበር አሁን አብሯት ካለው ወጣት ጋር ከተዋወቁም በኋላ እንኳ አለቀቃትም፡፡ አመት ሆኗቸዋል፡፡ በፍቅራቸው ደስተኛ ናት፡፡ ደስተኛ የሆነችው ምናልባትም ወጣቱ አእምሮዋንና ገላዋን ነጣጥሎ ስለማያይ ይሆናል፡፡ ከእርሱ ጋር ስትሆን ምሉዕ ትሆናለች፡፡ አእምሮዋ ሀራምባ፣ ሰውነቷ ቆቦ አይሆንም፡፡ ከእርሱ ጋር ስትሆን አእምሮዋና ገላዋ ጋብቻ ይፈፅማሉ፡፡ ከዚህ ጋብቻ ደስታ ይወለዳል፡፡ ከደስታው ጀርባ ሁሌም ጥርጣሬ ይሉት ነገር ተለጥፎ አለ፡፡ ልጅቷ ጋ ደግሞ ጥርጣሬ በሽ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሌሎቹ ሴቶች (ማለት እንደ እሷ ከወንድ ጋ ሲሆኑ የማይሸበሩት) ከእሷ ይልቅ ማራኪና አማላይ ሆነው ይታይዋታል። ወጣቱ ብዙ እንዲህ አይነት ሴቶች ይተኛ እንደነበር ታውቃለች፡፡ እሱ፣ እራሱ ነው የነገራት፡፡ አንድ ቀን ታዲያ እኚህን ሴቶች ፍለጋ ጥሏት ቢሄድ የማን ያለህ ትላለች? ምን ይውጣታል ያኔ? አንድ ቀን ጥሏት መሄዱ አይቀርም መቼስ፡፡ (ወጣቱ ከእነዚህ ሴቶች ጋ ለዘመኑ ሁሉ የሚበቃውን ያህል ቀብጧል፡፡ ‘ጠግቤያቸዋለሁ፤ ይበቁኛል፡፡’ ብሏታል፡፡ የሚያስበውን ያህል እድሜው እንዳልሄደ በደንብ ታውቃለች፡፡ ገና ወጣት ነው፡፡) አንዳችም የሚጨመር የሚቀነስ ነገር ሳይኖር፣ ሙሉ ለሙሉ የእሷ እንዲሆን ትፈልጋለች፡፡ የእሷ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ የእርሱ ናት፡፡ የሚያበሳጨው ደግሞ ሁሉንም ነገር ልትሰጠው ስትታትር አንድ ወሳኝ ነገር ትነፍገዋለች፡፡ ወንዶች ከአስመሳይ፣ ጨምላቃና አጉል ተሽኮርማሚ ሴቶች የሚያገኙትን የፍቅር ደስታ ትነፍገዋለች፡፡ ብስለትን ከሞልቃቃነት ጋር አጣምዳ መያዝ አለመቻሏ ያስጨንቃታል፡፡
አሁን ጭንቀት የለም፡፡ እንዲህ አይነት ሀሳቦቿ ከአእምሮዋ ተሰደዋል፡፡ ደስ ብሏታል፡፡ አንድ፡- የመዝናኛ እረፍታቸው የመጀመሪያው ቀን ነው። (የሁለት ሳምንታት የመዝናኛ እረፍት ሊያደርጉ አቅደዋል፡፡ አመቱን ሁሉ ስለዚሁ ስታስብ ነበር የባጀችው፡፡) ሁለት፡- ሰማዩ ሰማያዊ ነው፡፡ (አመቱን ሙሉ የሰማዩ ቀለም እንዲህ ጥርት ያለ ሰማያዊ እንዲሆን ስትመኝ ነበር፡፡) ሶስት፡- የምታፈቅረው ወጣት አጠገቧ አለ፡፡ “ወዴት?” የሚለው ጥያቄ አሳፍሯታል፡፡ ምንም ሳትመልስ መንገድ ጀመረች። ከመንገዱ ዳር ያለው የጋዝ መሸጫ ጣቢያ ብቻውን ነው የቆመው፡፡ በዙሪያው ከሰፊ ሜዳ ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡ መቶ ሜትር በሚጠጋ እርቀት (እነሱ ጉዞዋቸውን በሚቀጥሉበት አቅጣጫ) ጫካ ይጀምራል፡፡ ወደ እዚያ ሄዳ ደኑ ውስጥ ተሰወረች። አሁን እንደፈለገች መሆን ትችላለች፤ የፈለገችው ደግሞ ዘና ማለት ነበር፡፡ ዘና አለች፡፡
ተጠናቃ ከደኑ ውስጥ ወጣች፡፡ ትልቁ የጋዝ መኪና ቦታ ሲለቅና የእነሱ መኪና በቦታው ሲተካ ይታያታል፡፡ ወደ ፊት ጉዞ ጀመረች፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ የስፖርት መኪናው መምጣቱን ለማየት ዞር ትላለች፡፡ መጣ፡፡ ቆመች እና ልክ ሂችሀይከሮች፣ ለማያውቁት ባለመኪና እንደሚያደርጉት እጆቿን አውለበለበች፡፡ የስፖርት መኪናው ሾፌር ፍጥነቱን ቀንሶ ልጅቷ ጋ ሲደርስ ቆመ፡፡
ወጣቱ ወደ ጎን ዘንበል ብሎ የመኪናዋን መስኮት ወደ ታች አውርዶ፣ በፈገግታ፡- “ወዴት ነሽ የእኔ እመቤት?” ብሎ ጠየቃት፡፡ “ወደ ባይስትሪትዛ ነው የምትሄደው?” እየተሽኮረመመች ጠየቀችው። “እንዴታ! እባክሽ ግቢ፡፡” ብሎ በሩን ከፈተላት፡፡ ልጅቷ ገባችና መንገድ ጀመሩ፡፡ ወጣቱ እጮኛው ስትደሰት እሱም ይፈነድቃል፡፡ ችግሩ እሷ ሁሌ ደስተኛ አትሆንም፡፡ ስለ ስራዋ ዝም ይሻላል፡፡ ስራዋ እጅግ አድካሚ ነው - አንድ፡፡ የስራ ከባቢው አስደሳች አይደለም- ሁለት፡፡ ከመደበኛው የሥራ ጊዜ በላይ ለብዙ ሰዓታት ትሰራለች - ሶስት፡፡ እነዚህን የሚያካክስ በቂ እረፍት አታገኝም - አራት። ከዚህ ሁሉ በላይ ወደ ቤት ስትመለስ በሽተኛ እናት ይጠብቋታል፡፡ እናም ብዙውን ጊዜ ይደክማታል። እንደ አለመታደል ሆኖ ይህን ሁሉ ጫና ሊሸከም የሚችል የተፈጥሮ ስሪት የላትም፣ ወይም ይህን ጉድለት የሚተካ በራስ መተማመን አላዳበረችም። እኒህ ሁሉ ተደምረው የማይረባ ምክንያት በቀላሉ ገፍትሮ ጭንቀት እና ፍርሀት ላይ ይጥላታል፡፡ ይህን ስለሚያውቅ አንዲት የደስታ ፍንጭ ሲያይባት የጡት አባት የማደጎ ልጁን በሚያባብልበት፣ ልምምጥ አይነት ሙሉ ለሙሉ ዘና እንድትል ይጥራል። አሁንም የተፈጠረውን እድል ለመጠቀም ፈገግ ብሎ፡- “ዛሬ እድለኛ ነኝ፡፡ አምስት አመት ሙሉ አሽከርክሬያለሁ፤ አንድም ቀን እንዲህች አይነት ቆንጅዬ ሂችሀይከር አሳፍሬ አላውቅም፡፡”
ውዳሴው ተመችቷታል፡፡ በውዳሴው እቅፍ ለመቆየት፡-
“አደገኛ ውሸታም ነህ፡፡” አለችው፡፡
“አትይኚም? ውሸታም እመስላለሁ እንዴ?”
“ሲያዩህ ሴቶችን በመዋሸት የምትደሰት ትመስላለህ፡፡” ሳይታወቃት ሁሌም አብሯት ያለው ጥርጣሬ ቃላቶቿ ላይ ተለጥፏል፡፡ ፍቅረኛዋ ለሴቶች ውሸት ከመናገር እንደማይመለስና በዚያም እንደሚዝናና ትጠረጥራለች ሳይሆን ታምናለች፡፡
የልጅቷ ቅናት ወጣቱን ሁሌም ያናድደዋል፡፡ አሁን ግን ቅናቷን ቸል አለ፡፡ የቀናችው ፍቅረኛው ሳትሆን ሂችሀይከሯ ናት፡፡ የቅናቷም መንስኤ ወጣቱ ፍቅረኛዋ ሳይሆን፣ ለሂችሀይኪንግ የተባበራት፣ አሁን እያዋራችው ያለው፣ የማታውቀው ሾፌር ነው፡፡ ይህን በልቡ ይዞ፡-
“በተለይ ሴቶችን መዋሸቴ ያሳስበሻል?” ብሎ ጠየቃት፡፡
“የእኔ ብትሆን ኖሮ፣ በእርግጥ ያሳስበኝ ነበር።” አለች፡፡ አሁንም በስውር ለወጣቱ ማስተላለፍ የፈለገችው መልዕክት አለ፡፡ ወጣቱ አሁንም የአረፍተ ነገሯ የመጨረሻው እኩሌታ የተነገረው ለማታውቀው ሾፌር ነው ብሎ አሰበ፡፡ ቀጠለች፡- “አንተን አላውቅህም፤ ስለዚህ ሴቶችን ዋሸህ አልዋሸህ ጉዳዬ አይደለም፡፡”
“አንዲት ሴት የፍቅረኛዋ ነገር ሁሌም ያስጨንቃታል፣ ለማታውቀው ወንድ ግን ብዙም ግድ የላትም፡፡” (አሁን ደግሞ ወጣቱ በስውር ለፍቅረኛው፣ ለልጅቷ መልእክት እያስተላለፈ ነው።)  “ስለዚህ እኔና አንቺ ስለማንተዋወቅ ፈታ ብለን ነገሮችን በቀላሉ ማስኬድ እንችላለን፡፡”
“እኔና አንተን እንኳ የሚያሳስበን ነገር የለም፡፡ ብዙም ሳንቆይ መለያየታችን አይቀርም፡፡”
“ለምን?” ጠየቀ ወጣቱ፡፡
“እኔ ወደ ባይስትሪትዛ ነው የምሄደው፡፡”
“አብሬሽ ብሄድስ?”
ቀና ብላ አየችው፡፡ አብሯት በሌለ ጊዜ በቅናት ተጥለቅልቃ፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር ሲሆን መልኩ ምን ሊመስል እንደሚችል በምናቧ እልፍ ጊዜ አይታዋለች። አሁን ቁጭ እንዲያ ነው የሚመስለው። ተሰቃዪ ሲላት ከማን ጋር እያወራ እንደሆነ አስታወሰች፡፡ አሁን ለካ እያወራ ያለው ከእሷ ጋር አይደለም፤ ከማያውቃት ሂችሀይከር ጋር ነው፡፡ ሲችልበት! ተናዳለች፡፡ ሆን ብላ ልታበሳጨው፡-
“አጃኢብ ነው መቼስ፡፡ ከእኔ ጋር ሄደህ ምን ታደርጋለህ?”“አንቺን ከመሰለች ቆንጂዬ ጋር ምን ማድረግ እንዳለብኝ ብዙ ማሰብ የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡” ይህን የመለሰው ለሚወዳት ልጅ ነው፤ ለሂችሀይከሯ አይደለም፡፡
ልጅቷ ግን መልሱ በሷ ላይ ከሌላ ሴት ጋር ሲቀብጥ እጅ ከፍንጅ የያዘችው አይነት ሆነባት፡፡ እድሉን ቢያገኝና ከሌላ ሴት ጋር ቢሆን ኖሮ ምን አይነት መልስ ይመልስ እንደነበር ያናዘዘችው አይነት ተሰማት፡፡ ጥላቻ በወላፈኑ ላሳት፡፡
“ሁሉም ሴቶች እንደሚከጅሉህና ከአንተ ጋር ለመተኛት እንደማያቅማሙ እርግጠኛ የሆንክ አይመስልህም?”
አያት፡፡
ፊቷ በእልህ ተኮማትሯል፡፡ አሳዘነችው፡፡ የወትሮው፣ የአዘቦት ፊቷ ናፈቀው፡፡ (ፊቷ የህፃንና ቅልል ያለ ፊት ነው፡፡) ወደ እሷ ዘንበል ብሎ ትከሻዋን አቀፋት፡፡ በስሟ ጠራት፡፡ በስሟ የጠራት ጨዋታውን እንዲያቆሙ መፈለጉን እንድታውቅ ብሎ ነው፡፡
እጁን ከትከሻዋ ላይ አነሳችና፡-
“እየፈጠንክ ነው!” አለች፡፡
ማሳሰቢያዋን ተቀብሎ፡- “ይቅርታ፣ የእኔ እመቤት፡፡” አለ፡፡ በዝምታ አውራ ጐዳናውን እየተመለከተ ማሽከርከሩን ቀጠለ፡፡     
ሳይታሰብ፣ ድንገት ሰፍኖባት የነበረው ቅናት በፍጥነት ለቀቃት፡፡ ሲጀመር ገና ይህ ጨዋታ መሆኑን ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ጨዋታ መሆኑን እያወቀች፣ ቅናት በወለደው ቁጣ ፍቅረኛዋን ማናደዷ ቆጫት። ሳይታወቃት ትንሽ ተጃጅላለች፡፡ ቅናቷ የምር መሆኑን ማወቅ የለበትም፡፡ እንደመታደል ሆኖ ሴቶች የድርጊታቸውን ትርጉም ሁነቱ ከተከሰተ በኋላ የመቀየር ተአምራዊ ችሎታ አላቸው፡፡ ይህ አስማት ለአሁን ያልሆናት ለመቼ ሊሆናት ነው? ችሎታዋን አሁን መጠቀም አለባት፡፡
ያስኮረፈችው ጨዋታቸው እንዲቀጥል አስባ እንጂ ቀንታ አይደለም፡፡ ንዴቷ የውሸት ነበር፡፡ ድንገት የመጣላቸው፣ አስገራሚው ጨዋታቸው ደግሞ ደስ ይላል፡፡ የእረፍታቸውን የመጀመሪያ ቀን በእንዲህ አይነት ጨዋታ እንጀምራለን ብለው ሁለቱም አላሰቡም፡፡ አሪፍ ጅማሮ ስለሆነ ጨዋታቸው መቀጠል አለበት፡፡
እሷ ተመልሳ ሂችሀይከር ሆነች፡፡ እሱ ደግሞ ጠበሳው በፍጥነት እየተሳካለት የነበረ ሾፌር ነው። ያስቀየመችው ጠበሳው እጅግ ስለፈጠነ ትንሽ በመጎተት አጓጊነቱን ከፍ ለማድረግ አስባ ነበር፡፡
ቀጠለች፡፡
“ክቡር ሆይ! ላስቀይምህ ብዬ አልነበረም፡፡” ሳመችው፡፡
“ይቅርታ ከአሁን በኋላ እንዲህች ንክች አላደርግሽም፡፡”
እሳት ለበሰ፡፡ እሳት ጎረሰ፡፡
እሱ የፈለገው ይህን ጨዋታቸውን ወዲያ ትታ እራሷን እንድትሆንለት ነው፡፡ ይህን አልገነዘብ ብላ ሂችሀይከር ሆና ቀጥላለች፡፡ ችግር የለም፡፡ ንዴቱን ልጅቷ በወከለቻት፣ በማያውቃት ሂችሀይከር ላይ ይወጣል፡፡ ቅድም ሲያደርግ እንደነበረው በዙሪያ ጥምጥም፣ በሂችሀይከሯ አስታኮ፣ ፍቅረኛውን ማሞካሸትና ማሽኮርመም የለም፡፡ ምን ገፀ-ባህሪ ነበር መጫወት የነበረበት? ጨካኝ ይሆናል፡፡ ሴቶችን የሚያንኳስስና የሚያንቋሽሽ ተባዕት ይሆናል፡፡ የወንዶችን ያልተገራ፣ የዱር ባህሪ ይላበሳል፡፡
ሰው ጤፉ፡፡
አላጋጭ፡፡
ቀብራራ፡፡
አሁን የሚላበሰው ባህሪ ከዚህ ቀደም ለልጅቷ ያሳይ ከነበረው ትሁት ባህሪ ፍፁም የሚቃረን ነው፡፡ ኬረዳሽ! አንድ እውነት አለ፡- እሷን ከማግኘቱ በፊት የነበሩት ሴቶች ላይ ባለጌ ነበር፡፡ ቅንጣት ታህል አይጠነቀቅላቸውም ነበር፡፡ እንዲያ ማለት ግን ግፍ የማይፈራ፣ አረመኔ ወንድ ነበር ማለት አይደለም። አረመኔ ለመሆን በቂ ቆራጥነት ወይም በቂ ጭካኔ አልነበረው ይሆናል፡፡ አሁንም አረመኔ ለመሆን ቆራጥነቱ ወይ ጭካኔው አልነበረውም ማለት አረመኔ ለመሆን አንድም ቀን ፈልጎ አያውቅም ማለት አይደለም፡፡ አረመኔ ለመሆን መመኘት የቂሎች ምኞት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ምኞቱ ነበረው፡፡ አንዳንድ የህፃንነት እኩይ ፍላጎቶች፣ የጉርምስናን ማጥለያ አልፈው ወደ ጉልምስና፣ ከፋ ሲልም ወደ ሽምግልና እድሜያችን ሊዘልቁ ይችላሉ። ይህን ያንቀላፋ ማንነት ለመቀስቀስ አመቺ ሁኔታ ተፈጠረ። የተላበሰውን ገፀ ባህሪ ተገን አድርጎ የፈለገውን ማድረግ ይችላል፡፡
እነሆ ሜዳ፡፡
እነሆ ፈረስ፡፡
የወጣቱ የንቀት ዝምታ ተመቻት፡፡ እራሷን፣ ከእራሷ የአዘቦት ማንነት ነፃ አደረገች፡፡ ደሞ ለቅናት! በቅናት ከአለም አንደኛ ናት፡፡ ከአስፈለገ የአለም ህዝቦችን ቅናት ሁላ ሰብስባ ለብቻዋ ልትቀናው ትችላለች፡፡
አየችው፡፡
የቅድሙን ጀግና አማላይ አይመስልም። ፊቱ ለማንበብ ያስቸግራል፡፡ እንዲህ ሲሆን የእሷም ቅናት ብን ብሎ ጠፋ፡፡ አሁን እራሷን ጥላ፣ ገፀ-ባህሪዋን ማንሳት ነው፡፡
ገፀ-ባህርይ? ምን ሆና ነው መተወን ያለባት? ሂችሀይከር፡፡ ሲበዛ ቀላል ባህሪ ነው። ቀሽምና ርካሽ ስነ ፅሁፎችና ተውኔቶች ላይ የምትዘወተር ገፀ-ባህርይ ናት፡፡ እንዲህ ነው፡- ቆንጂዬ ሂችሀይከር አለች። መኪና ታስቆማለች፡፡ መኪናውን የምታስቆመው ካለችበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ፈልጋ አይደለም፡፡ ሾፌሩን ለመጥበስ ነው። በአስማተኛ ውበቷ እንዴት አድርጋ መማረክ፣ መመሰጥ፣ ማሳት እንደምትችል ጠንቅቃ ታውቃለች። ልጅቷ ያለምንም ጥረት ተራ አፍቃሪ ሆና አረፈችው። እንዴት በቀላሉ እንዲህ ሊሳካላት እንደቻለ ለእሷ፣ ለእራሷ ገርሟትም አላባራ፡፡ አጃኢብ ነው የሆነባት፡፡
ወጣቱ ፈታ እንዳለ ህይወት የናፈቀው ነገር የለም፡፡ የመጣበትም ሆነ ወደ ፊት የሚጠብቀው የህይወት አውራ መንገድ ምህረት በሌለው ጥንቃቄ የተሞላና በማይዛነፍ እቅድ የታጠረ ነው፡፡ ስራ? ስራው ለስራ የተመደበው ስምንት ሰዓት ሲያበቃ፣ አብሮ የሚበቃ አይደለም፡፡ በድብርት የሰባ ስብሰባ አለ፡፡ አሰልቺ የቤት ውስጥ ጥናት አለ፡፡
ከዚህ ሁሉ የቀረችውን ሰዓት ደግሞ ሴቶቹም፣ ወንዶቹም የስራ ባልደረቦቹ ይሻሙታል፡፡ የግል ህይወት? የግል ህይወትና ምስጢር የሚባል ነገር የለውም፡፡ የግል ህይወቱ የአደባባይ መወያያ ነው፡፡ ምስጢሮቹ የአሉባልተኞችና የሀሜተኞች መደበሪያ ሁነዋል። ይህ የአሁኑ የሁለት ሳምንታት የመዝናኛ እረፍት እንኳ እንዳሰበው ከብዙ ጣጣዎች የፀዳ አይደለም፡፡ እንደፈለገው የሚያስፈነድቅ አልሆነለትም፡፡ በሀገሪቷ ውስጥ በበጋ ሆቴሎች በሙሉ ይያዛሉ፡፡ ታትራስ ውስጥ የሆቴል ክፍል ለማግኘት ከስድስት ወራት በፊት ቀድሞ መመዝገብና ቦታ ማስያዝ ነበረበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የድጋፍ ደብዳቤ ያስፈልጋል፡፡ የድጋፍ ደብዳቤውን ማነው የሚፅፈው? መስሪያ ቤቱ፡፡ መስሪያ ቤቱ የእረፍት ጊዜውን የት እንደሚሳልፍ ያውቃል ማለት ነው፡፡ ሁሉን አዋቂ መስሪያ ቤቱን አሁን እንኳ ማምለጥ አልቻለም፡፡ መስሪያ ቤቱን ተሸክሞት ነው የሚዞረው፡፡ በሄደበት ሁሉ አለ፡፡
ይህን ሁሉ ችሎ፣ ‘እስኪ ይሁና’ እያለ ነበር የሚኖረው፡፡ እንዲያም ሆኖ የህይወት አውራ መንገድ የሚለው ሀረግ ሁሌም አእምሮው ውስጥ መመላለሱ አልቀረም፡፡ በህይወት አውራ መንገድ ላይ ሁሉም ያሳድዱታል፡፡ ለሁሉም ሰው እይታ የተጋለጠ ነው፡፡ እሱ የሚሄድበት የህይወት አውራ መንገድ ቀጥ ያለ ነው፡፡ ወደ ግራም ወደ ቀኝም መታጠፊያ የለውም። ዳር ወጥቶ መቆም አይቻልም። ባልተለመደ የሀሳቦች መስተጋብር ሀሳባዊው የህይወት አውራ መንገድ፣ አሁን እየተጓዘበት፣ አሁን መኪናውን እያሽከረከረ ካለበት እውናዊው አውራ መንገድ ጋር አንድ ሆኑበት፡፡ የሰከረ ነገር አደረገ፡፡ እብደት ሰራ፡፡
“ወዴት ነበር እሄዳለሁ ያልሽኝ?” ጠየቃት ልጅቷን፡፡
“ወደ ባንስካ ባይስትሪትዛ፡፡”
“እዛ ምን ታደርጊለሽ ?”
“ቀጠሮ አለኝ፡፡”
“ከማን ጋር?”
“ከሆነ ወጣት ጋር፡፡”
ይህን እየተባባሉ ሰፊ መስቀለኛ መንገድ ጋ ደርሰዋል፡፡ ሾፌሩ የመንገድ ጥቆማዎቹን ለማንበብ የመኪናዋን ፍጥነት ቀነሰ፡፡ አነበበ፡፡ ወደ ቀኝ ታጠፈ።
“ለቀጠሮው ባትደርሺ ምን የሚከሰት ይመስልሻል?”
“ያ ያንተ ጥፋት ይሆናል፤ እናም ሀላፊነቱን ወስደህ ትንከባከበኛለህ፡፡”
“ወደ ኖቭ ዛምስኪ እንደታጠፍኩ እንዳላስተዋልሽ አይቻለሁ፡፡”
“የምርህን ነው? አብደሃል!”
“አትፍሪ፡፡ ሀላፊነቱን እወስዳለሁ፡፡”
ሾፌሩና ሂችሀይከሯ እንዲህ እያወጉ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ጨዋታቸው በከፍተኛ ማርሽ ሽው እያለ ነው፡፡ የስፖርት መኪናው ከምናባዊው ባንስካ ባይስትሪትዛም ሆነ ከእውኑ መዳረሻቸው፣ የሆቴል ክፍል ካስያዙበት ከታትራስ እየራቀ ሄደ። ሳይታሰብ ህልም፣ እውን ላይ አላገጠ፡፡ ወጣቱ ከእራሱ እየሸሸ ነው፡፡ የህይወቱ አውራ መንገድ መታጠፊያ አልነበረውም፡፡ መነሻውም መድረሻውም የሚታወቅ፣ ቀጥ ያለ መንገድ ነው፡፡ ያንን ለማካካስ የእውኑ አውራ መንገድ ላይ እንኳን ወዳላሰቡት አቅጣጫ ሲጢጢ አድርጎ መታጠፍ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም እንዲያ ነው ያደረገው፡፡
“ወደ ታትራስ ነው እንሄዳለን ብለህ የነበረው!” ገርሟታል፡፡
“ሴትዮ ወዳሰኘኝ መሄድ እችላለሁ፡፡ ያሻኝንና የሚያስደስተኝን ሁሉ ማድረግ እችላለሁ፡፡ ነፃ  ነኝ።”
ኖቭ ዛምስኪ ሲደርሱ፣ እየጨለመ ነበር፡፡ ወጣቱ ኖቭ ዛምስኪን አያውቃትም፡፡ ግርታው እስኪጠፋና እራሱን እስኪያላምድ ጊዜ ወሰደበት፡፡ ደጋግሞ እየቆመ፣ ደጋግሞ የእግር መንገደኞችን በቅርብ የሚገኝ ሆቴል መጠየቅ ነበረበት፡፡ ሆቴሉ ቅርብ ነው፡፡ (ከእግር መንገደኞቹ ጥቆማ እንደተረዱት) እዚያ ለመድረስ ግን ግማሽ ሰዓት ጠየቃቸው፡፡ ብዙ መታጠፍና ብዙ ዘወርዋራ መንገዶች ማለፍ ነበረባቸው፡፡
ደረሱ፡፡



Read 3476 times