በከተማዋ የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደር እጦትና የኑሮ ውድነቱን በተመለከተ ምን ማሻሻያ ሊደረግ ታስቧል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰፋ ያለ ምላሽ ከመስጠት የተቆጠቡት ምክትል ከንቲባው፤ በጥቅሉ ሥራ ነቀል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ የሚያመጡ ዕዶችን ይዘናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ከ100ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጐችን በጥቃቅንና አነስተኛ ለማደራጀት የተያዘው ዕቅድ ከኢኮኖሚ ዕቅዶቹ ውስጥ ተጠቃሽ እንደሆነም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በቅርቡ ተጀመረ ባሉት የ42ሺ ቤቶች ግንባታ ከ210ሺ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና በዚህም ከ50ሺ የሚበልጡ ዜጐች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ መደረጉ ከተማዋ እያካሄደችው ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት አመላካች ነው ብለዋል፡፡ እስከመጪው ህዳር ወር ድረስ ይዘልቃል በተባለው በዚህ የምስረታ በዓል አከባበር ፕሮግራም ላይ አውደርዕዮች፣ የፓናል ውይይቶች፣ የኪነጥበብ ዝግጅቶች፣ ዶክመንትሪ ፊልሞች ለእይታ እንደሚቀርቡና የተለያዩ የጉብኝት ፕሮግራሞችም እንደተዘጋጁ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ዛሬ በይፋ በሚጀመረው በዚሁ በዓል የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ ከ1200 በላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች እንደሚገኙና በመክፈቻ በዓሉም የምስረታውን በዓል አርማ /ሎጐ/ የማስተዋወቅ፣ የከተማዋ ድረ ገፅ/ዌብሳይት ምረቃ ሥነ ስርዓትና ለበዓሉ የተዘጋጀውን መዝሙር ይፋ የማድረግ ፕሮግራም መዘጋጀቱን አቶ አባተ ጨምረው ገልፀዋል፡፡