Saturday, 16 January 2016 10:06

“የእኛ ጉድ መቼም…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(12 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡—  አጅሬው፣ ደግሞ መጣህ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ፣ አንድዬ፣ ደግሞ መጣሁ፡፡ ሌላ ምን መሄጃ አለኝ!
አንድዬ፡— አሁን፣ አሁንማ…ስትጠፋ አልፎ፣ አልፎ ትዝ ትለኝ ጀምረሀል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሰይ፣ አንድዬ እሰይ! ይኸው አሁን ታስብልን ጀመር ማለት ነው፡፡
አንድዬ፡— እንደ እሱ አላልኩህም፣ እንደ እሱ አላልኩህም፡፡ እርስ በራሳችሁ ትንሽ፣ ትልቁን መጠምዘዛችሁ አነሳችሁና የእኔንም ቃል ትጠመዝዝ ጀመር!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ ምን በወጣኝ፣ አንድዬ፣ ኧረ ምን በወጣኝ!
አንድዬ፡— እሺ፣ አሁን ደግሞ ምን አቤቱታ ይዘህ መጣህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ መረረኝ፣ በጣም መረረኝ!
አንድዬ፡— አንተ ቢመርህ ታዲያ ምን አዲስ ነገር አለው… በመጣህ ቁጥር “መረረኝ” ከማለት በስተቀር ሌላ ምን ብለኸኝ ታውቃለህ! ይልቅ ያልመረረህ ቀን መጥተህ “ዛሬ አልመረረኝም” ብትል አዲስ ዜና ይዘህ መጣህልኝ እላለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ የአሁኑ ሲብስስ! የአሁኑ በጣም ሲብስስ!
አንድዬ፡— ምን የተለየ ነገር ሆንክ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ያልሆንኩት አለ አንድዬ… ምነ ያልሆንኩት አለ! አንድዬ፣ ቢርበኝ፣ ቢጠማኝ እንኳን የአእምሮ ሰላም የማገኝበት ቦታ ወስደህ ወርውረኝ፡፡
አንድዬ፡— ቆይ፣ አንዴ ቆይ… በፊት እኔ ዘንድ ስትመጣ ለወገኖችህም፣ ወገኖቼ ለምትላቸውም አንድ ላይ አይደል አንዴ የምትለማመነኝ! አሁን ምን መጣና ነው እኔ፣ እኔ ማለት ያበዛኸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ሰዉ ሁሉ እኔ፣ እኔ እያለ እኛ ማለት ሞኝነት ሆኗል፡፡ አንዳንዴም እንሰሳዋ ‘መጀመሪያ መቀመጫዬን’ እንዳለችው እኔም ለመቀመጫዬ…
አንድዬ፡— ይኸውልሀ! ከሌላው እኩል እንዳትሆኑ ያደረጋችሁ ሁላችሁም ‘መጀመሪያ መቀመጫዬን’ ስለምትሉ ነው፡፡ ለእኔም ለማን ምን እንደማደርግ ግራ የገባኝ ለማን እሺ ብዬ ለማን ልተው እያልኩ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እውነቴን ነው የምልህ… በጣም ነው የመረረኝ፡
አንድዬ፡— እሺ ምን አድርግልኝ ነው የምትለኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ከዚሀ ቦታ አውጣኝ…
አንድዬ፡— ከዚህ ቦታ ስትል…
ምስኪን ሀበሻ፡— ከዚህ አገር ማለቴ ነዋ አንድዬ፣ ከዚሀ አገር አውጣኝ፡፡
አንድዬ፡— እሺ አውጥቼ የት ልውሰድህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— የፈለግኸው ቦታ! የፈለግኸው ቦታ አውጣኝ፡፡
አንድዬ፡— ሌላም ቦታ ቢሆን እኮ ችግር አለ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ይኑር አንድዬ፣ ሺህ ጊዜ ችግር ይኑር፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ እዛ እኮ የባዕድ አገር ስለሆነ በደል ሲደርስብኝ ‘ከአገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ’ እያልኩ እያንጎራጎርኩ ጊዜዬን አሳልፋለሁ፡፡
አንድዬ፡— እውነቱን ልነገርህ… እኔ የትም አልወስድህም፡፡ የትም ቦታ ብትሄድ፣ ወይም ብትሄዱ እኔ ዘንድ ለአቤቱታ መመላለሳችሁ አይቀርም፡ በልመና ሲያስቸግሩኝ ይሁን ብዬ በየፈረንጅ አገሩ ብወስዳቸው አይደል እንዴ ገና ወር ሳይሞላቸው “አገሬ ናፈቀኝ…” ምናምን እያሉ የሚያለቅሱብኝ እኔ የትም ቦታ አልወስድህም፡፡ ከፈለግህ ራስህ በመሰለህ መንገድ የፈለግኸው ቦታ ሂድ። ሌላ የምትለኝ አለ?
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ አላወጣህም ካልከኝ ሀብታም አድርገኝ፡፡
አንድዬ፡—እንዴት አድርጌ ነው ሀብታም የማደርግህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ሌላውን ሀብታም እንዳደረግኸው ነዋ! አገሩን ሁሉ ሀብታም እንዳደረግህ እኔንም አድርገኛ፡፡
አንድዬ፡—አየሀ ራስህን ችለህ እንደመናገር ስለ ሌላው ታነሳብኛለህ፡፡ እናንተ ከሌላው ጋር ምን ጉዳይ አላችሁ፡፡ ለምን ራሳችሁን ከሌላው ጋር ታመሳስላላችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን አጠፋሁ አንድዬ፣ ምን አጠፋሁ?
አንድዬ፡— ሌሎቹ እንዴት ሀብታም ይሁኑ እንዴት ምን አገባህ? በቃ እናንተ ዘላለም የሌላውን ጓዳ እንደቀላወጣችሁ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ ተጸጽቻለሁ፡፡ ብቻ ሀብታም አድርገኝ፡፡
አንድዬ፡— ምን ሠራህና… ለሀብታምነት የሚያበቃ ምን ሥራ ሠራህና!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንዴ አንድዬ፣ ሌላው ምን ለሀብታምነት የሚያበቃ ሥራ ሠርቶ ነው እንዲህ ብሩን እንደ ጤፍ የሚዘራው! አንድዬ አትታዘበኝና ለሀብት የሚያበቃ ሥራ የሚሠሩት በጣም ጥቂት ናቸው። ሌላው እኮ በመስከረም ቤሳ ቤስቲኒ ሳይኖረው ነው ህዳር ላይ ቅልጥ ያለ ዲታ የሚሆነው፡፡
አንድዬ፡—እና በሁለት ወር ውስጥ ሀብታም ላድርግህ ማለት ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ሁለት ወርማ ብዙ ነው፣ በሁለት ሳምንት ሀብታም አድርገኝ፡፡
አንድዬ፡—እሺ፣ ነገ ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነሳ መኝታ ቤት መስኮትህ ስር አንድ ትልቅ ዛፍ ይኖራል፡፡ እና ከእሱ ዛፍ ላይ የአገርህን ብር ብትል ሌላ አይነት ገንዘብ እየበጠስክ ትወስዳለህ፡፡ እንዲህ አይደል የምትፈልገው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እየቀለድክብኝ ነው አይደል!
አንድዬ፡— አንተ ላይ ያልቀለድኩ ማን ላይ ልቀልድ! በአሥራ አምስት ቀን ሀብታም የማደርግህ እንደው አንደኛውን ሞኝ አደረግኸኝ። ‘በወዝህ ጥረህ ግረህ ብላ’ ያልኩትን የረሳሁ መሰለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ሌሎቹ…
አንድዬ፡— ሌሎቹ! ሌሎቹ! ሌሎቹ…በቃ ሀብታም አድርገኝ የምትለውን ነገር ተወኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ ሀብታም ካላደረግኸኝ አርቲስት አድርገኝ…
አንድዬ፡— አርቲስት ማለት…ከመቼ ወዲሀ ነው ስዕል መሳል የጀመርከው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ስዕል ሳይሆን አርቲስት፣ ማለት ተዋናይ አድርገኝ፡፡
አንድዬ፡— (ከት ብሎ ይስቃል)  ምን እንድትሆን ነው ተዋናይ የማደርግህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ልተውን ነዋ አንድዬ… ገንዘብ ባይኖረኝ ቢያንስ ዝና አገኛለሁ፡፡
አንድዬ፡— ምን ይገርምሀል በለኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አንተንማ እንዲህ አልልም…
አንድዬ፡— ባትልም ልንገርህ፣ አሁን ተዋናይ አይደለህም እንዴ! በተዋናይነትህ ላይ ነው እንደገና ተዋናይ የማደርግህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ እንኳን ተዋናይ ልሆን መድረክ አጠገብ እንኳን ተቀምጬ አላውቅም፡
አንድዬ፡— አንተ ብቻ ሳትሆን ሁላችሁስ ተዋናዮች አይደላችሁም እንዴ! ንገረኛ፣ ማነው ራሱን ሆኖ የሚኖር… እኮ ንገረኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አልገባኝም…
አንድዬ፡— ሁልህም የትወና ኑሮ አይደለም እንዴ የምትኖረው! ቤታችሁ ሰባት ቦታ በተቀዳደደ አንሶላ ላይ እየተኛችሁ በአደባባይ የሰባት መቶ ብር ሸሚዝ የምታደርጉ አይደላችሁም እንዴ፡፡ ቤታችሁ አንድ እንጀራ ለምሳና ለእራት ብላችሁ እየቆጠባችሁ በአደባባይ ለአንዲት ፉርኖና ለቁራጭ ሥጋ መቶ ምናምን ብር የምታወጡ አይደላችሁም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ አበዛህብን…
አንድዬ፡— ዕውቀት ሳይኖራችሁ ለኒውተን የሰጠሁትን ጭንቅላት ያላችሁ የምታስመስሉ አይደላችሁም እንዴ! ትሰማኛለህ… አንድም እናንተንም፣ አገራችሁንም የበደለው የማያውቅ አዋቂ መብዛቱ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱ ላይ ልክ ነህ፡፡
አንድዬ፡— የእናንተ እውቀት ምላስ ላይ ተጀምሮ ምላስ ላይ የሚያልቅ ወደ አእምሮ የማይገባ ነው፡ ስልጣን ስላላችሁ አዋቂ የሆናችሁ ይመስላችኋል፣ ገንዘብ ስላላችሁ አዋቂ የሆናችሁ ይመስላችኋል፣ የእከሌ ዘር፣ የእነእከሌ አገር ሰው ስለሆናችሁ አዋቂ የሆናችሁ የሚመስላችሁ አይደላችሁም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ መፍትሄው…
አንድዬ፡— መቼ ጨረስኩ፣ መቼ ጨረስኩና!…ለነገሩ ሌሎቹ የሚጠብቁኝ ቅር እንዳይላቸው ወደ እነሱ ልሂድና ነገ ተነገ ወዲያ ናና እንደሚሆነው ይሆናል፡፡ ሰላም ውለህ እደር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን! (በሆዱ… “የእኛ ጉድ መቼም አያልቅ…” ይላል፡፡)
እኛም “አሜን!” ብለናል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 4695 times