Saturday, 16 January 2016 10:04

“የበላችው ያቅራታል በላይ በላዩ ያጐርሷታል!”

Written by 
Rate this item
(16 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ቆንጂት ልትዳር ሽማግሌዎች መጥተው ልጅዎን ለልጃችን ብለው ይጠይቁና እሺ ተብለው፤ ቀን ተቆርጧል፡፡ የሠርጉ ዝግጅትም ተጠናቋል፡፡ ተደገሠ፡፡ ተበላ፡፡ ተጠጣ፡፡
“ሙሽሪት ልመጅ
ሙሽሪት ልመጅ
እሰው ሀገር ሄዶ የለም የእናት ልጅ
እንዝርቱን ልመጅ
ደጋኑን ልመጅ
ምጣዱን ልመጅ
ሰፌዱን ልመጅ
እሰው ሀገር ሄዶ የለም የእናት ልጅ!” ተባለላትና ተሸኘች፡፡
ለመደች ለመደችና እናት አባቷን ለመጠየቅ መጣች፡፡
እናቷ ከአባቷ ይልቅ በሴትነት ለመወያየት ይቀርባሉና፤
“እንዴት ከረምሽ ልጄ?” አሏት፡፡
ልጅ፤
“ደህና ከርሜያለሁ እማዬ”
እናት፤
“ሳይሽ ወፈርፈር ብለሻል፤ እንዲያው ለመሆኑ ፀንሰሽ ይሆን እንዴ? አርግዘሽ ከሆነ የገንፎ እህልም፣ ሌላም አስፈላጊ ነገር እንዳዘጋጅልሽ ቀኑን ንገሪኝ፡፡ ለመሆኑ ያረገዝሽበትን ጊዜ ታውቂዋለሽ?”
ልጅ፤
“አይ እማዬ፤ ቀኑን እንዴት አውቀዋለሁ፡፡ እሱ በላይ በላዩ ይጨምርበታል!!”
*          *         *
በላይ በላዩ የምንጨምርበት ነገር በበረከተ ቁጥር ችግራችን ቅጥ - እያጣ፣ ህይወታችን ቅጥ - እያጣ፣ በመጨረሻም አገራችን ዕቅድ - አልባ ወደመሆን እያመራች ትሄዳለች፡፡ ቅጥ - አልባ መሆን ለሀገር ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ታቀደ የተባለው ሁሉ ዕልባት ሳያገኝ በላይ በላዩ ዕቅድ ካወጣንበት ሩጫችን ፍሬ-አልባ ነው የሚሆነው። ኑሯችንን እናጣጥም፡፡ ኢኮኖሚአችንን እናጣጥም፡፡ ፖለቲካችንን እናጣጥም፡፡ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ያልነውን እናጣጥም፡፡ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” የሚለውን ተረት እናጣጥም፡፡ ማንኛውም አዲስ መንግስት በመጣ ቁጥር ያለፈውን ሥርዓት መኮነኑ የተለመደና ምናልባትም ግድ ሊሆን ይችላል፡፡ የተለመደነቱ አዲሱ አሮጌውን መጣሉ አይቀሬ (Invincible) ስለሆነ ነው ይባላል፡፡ ግድነቱ ግን ከአሮጌው የተሻለ ነገር ሰርቶ ማሳየት ስላለበት ነው፡፡ ኩነና (condemnation) ብቻውን አቅም አይሆነንም፡፡ የኩነናችንን ምክን ከህልውናችን ምክን (raison d’être) ጋር ማያያዝ አለብን እንጂ ባዶ ኩነና (Vacant condemnation እንዲሉ) ምንም አይፈይደንም፡፡ ሁለተኛው ችግራችን ፍረጃ ነው (branding) ለየችግሩ ሁሉ እነእገሌ ናቸው ተጠያቂ ማለት፡፡ እነ እገሌ ደግሞ ይህን የሚያደርጉት እንትን ስለሆኑ ነው ብሎ ቦቃ ማበጀት፡፡ ፈርጅ መፍጠር፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ከዋናው ችግር ስለሚያራርቀን መፍትሄውም የዚያኑ ያህል ይርቅብናል፡፡ ችግሮቻችን የሚደራረቡት በቅጥ በቅጥ እየፈታናቸው ስለማንሄድ ነው፡፡ የፖለቲካውን ለፖለቲካ፣ የኢኮኖሚውን ለኢኮኖሚው ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ “የቄሣርን ለቄሣር” እንዲል መጽሐፍ፡፡ ሁሉን ችግር ፖለቲካዊ ፍረጃና መፍትሄ እንስጠው ካልን አገርን የፖለቲከኞች እንጂ የአገሬው አናደርጋትም፡፡ ዜጎቿን የማታከብር አገር ደግሞ አገር አትሆንም፡፡ ደካማ ትምህርት ያላት አገር ዕውቀት እንጂ ፖለቲካ አያሻትም፡፡ ደካማ ጤና ያላት አገር የጤና ባለሙያ እንጂ ፖለቲከኛ አያስፈልጋትም፡፡ ደካማ ኬላ ያላት አገር ሀቀኛ ተቆጣጣሪ እንጂ ፖለቲከኛ የግድ አያሻትም፡፡ መልካም ልማት የራባት አገር የልማት ባለሙያ እንጂ ፖለቲከኛ ገምጋሚ ባለውለታ አይሆናትም፡፡
አሁንም “የየሱስን ለየሱስ፤ የቄሣርን ለቄሣር እንስጥ!” ፍትህ የሚሻን ነገር ሌላ ሰበብ አንፈልግለት፡፡ ፍትሕ እንስጠው፡፡ ለምሳሌ በየኬላው የሚካሄዱ ፍተሻዎች ሚዛናዊ አይደሉም ከተባሉ ፈታሾቹን ፈትሾ ፍትሕ መስጠት ነው፡፡ ምሬቶችን አለማጠራቀም ለአገር ሰላም ይበጃል፡፡ ትናንሽ ጅረቶች ተጠራቅመው ወንዝ እንደሚሆኑ አለመርሳት ወሳኝ ብልሃት ነው፡፡ የቢሮክራሲው ቀይ ጥብጣብ (አሻጥር/bureaucratic red-tape እንቅፋት እንደማለት) አሁንም አልተበጠሰም፡፡ እንዲያወም ተተብትቧል ቢባል ይሻላል፡፡ ይህንንም መታገል ከልማት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነትና ተቀጣጣይነት ያለው ነው! በቅርብ እናስብብት!
እስከዛሬ አገራችን ተሰርቶላታል የምንለውን ነገር፤ ካልተሰራላት ጋር አነፃፅረን፤ የበላችውን ከተራበችው ጋር አወዳድረን፤ ከግብርናዋ ኢንዱስትሪዋን፣ ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዋ ያልተሰራውን ቤትና ያልገባላትን መንገድ አጢነን፤ ገና የሚቀረንን ጉዞ ማየት እንጂ በላይ በላይዋ ውዳሴ ብናበዛባት የአገራዊውን አባባል “የበላችው ያቅራታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሷታል” የሚለውን መዘንጋት ይሆንብናል፡፡ ከዚህ ይሰውረን!

Read 6310 times