Monday, 11 January 2016 12:09

ዊዝኪድስ 39 የጤና ፊልሞችና 12 መፃህፍትን ያስመርቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ፀሐይ መማር ትወዳለች” በተሰኘው የፓፔት ትርኢት የሚታወቀው ዊዝኪድስ ወርክሾፕ፤ በጤናና በጤና ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 39 ፊልሞችንና 12 መፃህፍትን አዘጋጅቶ ሊያስመርቅ መሆኑ ተገለፀ።
በህፃናት ጤና ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የባህርይ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ተብሎ ከዩኤስኤይድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰሩት የህፃናት ፊልምና መፃህፍት፣ በመጪው ጥር 26 በኦሮሞ ባህል ማዕከል እንደሚመረቁ የዊዝኪድስ ወርክሾፕ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ፤ “ፀሐይ መማር ትወዳለች” የተሰኘውን የፓፔት ትርኢት በመጠቀም በአራት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ራስን ከአደጋ ስለመከላከልና ስለንፅህና አጠባበቅ ለህፃናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለመስራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑንም ሥራ አስኪያጇ ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ 350ሺህ ህፃናት እንደሚሞቱ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከእነዚህ ህፃናት መካከልም 90 በመቶ የሚሆኑት የሚሞቱት በቀላሉ አስቀድሞ መከላከልና ህክምና ማግኘት በሚችሉ የሳንባ ምች፣ ተቅማጥ፣ ወባ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ኤችአይቪ ኤድስን የመሳሰሉ በሽታዎች መሆኑን የጠቆሙት ስራ አስኪያጇ፤ የህፃናቱን ግንዛቤ በማሳደግ እነዚህን ሞቶች ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ይቻላል ብለዋል፡፡ በቅርቡ የሚመረቁት ፊልሞችና መፃህፍት አካል ጉዳተኛ ህፃናትንም ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሲሆን የምልክት ቋንቋን እንዳካተቱም እንደሆነም ተገልጿል፡፡

Read 3841 times