Saturday, 18 February 2012 10:20

እኔና ጸሃይ

Written by  አንድነት ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ውጭ ላይ ቁጭ ብዬ ሳብሰለስል ጸሃይ ስታዘቀዝቅ አየሁዋት፡፡ ስትሰራ ውላ ደክሟታል መሰል ሙቀቷ በርዷል፤ ብርሃኗ ደብዝዟል፡፡ የትካዜዬ መንስኤ እሷ እንደሆነች ነው የተረዳሁት፡፡ ተጠጋሁዋት፡፡

“ሌባ” … አልኳት ፊት ለፊት፡፡

ዝም ብላ ቁልቁል ተንሸራተተች፡፡ የሰማችውን ያረጋገጠች አትመስልም፡፡ “ሌባ ነሽ፡፡ ሌባ ….” ደገምኳት፡፡ መመለሷን የረሳሁ ነው የሚመስል - ለነገ ልቆጥብ አልፈለኩም፡፡ ዝም ብላኝ ወረደች፡፡ የልቧን አድርሳ፡፡ ከአይኔ ተሰወረች፤ ጨለመብኝ፡፡ ጠዋት አስራ ሁለት ሰአት ከመሙላቱ በፊት ተነሳሁ፡፡ ዳገት ስትወጣ ባገኛት ጠበኳት፡፡ በምስራቅ በኩል ብቅ አለች፡፡ ሽቅብ መውጣት ጀመረች፡፡ ጉልበት ሰንቃለች፡፡ የልቤን ብሶት ለመግለጥ ቃላት መምረጥ ጀመርኩ፡፡ አንድ ቦታ ረጋ ያለች ሲመስለኝ

“መልሺልኝ”

“ምኑን?” አለችኝ፡፡ አሁን ነገር እንዳለ ገብቷታል፡፡ “ማታ በምእራብ በኩል ይዘሽ የወረድሽውን፡፡”

“ምን ይዤ ወረድኩ?”

“የእድሜዬን ቁራሽ ነዋ፡፡ አንቺ ስታዘቀዝቂ በእድሜዬ ላይ 12 ሰአታት ተቀንሷል፡፡ አንቺ ወጥተሽ በገባሽ ቁጥር የኔ እድሜ መቀነስ አለበት? በየቀኑ ስትቀንሺ ይኸው አሁን ባዶዬን ቀረሁ፡፡ ለምን እንደሚከፋኝ የገባኝ አሁን ነው፡፡”

“በእድሜህ ላይ ጨመርኩ እንጂ ቀነስኩ አይባልም፡፡” ልትሞግተኝ ጀመረች፡፡ እንዳልተቀበልኳት በሁኔታዬ ሳትረዳ አልቀረችም፡፡ ሄደች እኔም መንገዷን አልዘጋሁም - ደግሞ ቃጠሎዋን እጥፍ ብታደርገውስ /ወይም በአንድ ጀምበር የሁለት ቀን እድሜ ይዛብኝ ብትሄድስ?

በነጋታው ደግሞ ከወትሮው ይልቅ ስትፍለቀለቅ ወጣች፡፡ በተለይ እኔ ላይ የምትረጫቸው ጨረሮች ልዩ ነበሩ፡፡

“ይኸውልህ እሺ… ማታ ለወሰድኩት ካሳ ይሁን፡፡ 12 ሰአታት ይዤ መጣሁ” አለችኝ፡፡ ማንገራገሪያ ምክንያት አላገኘሁም፤ እሺ ብዬ አመስግኛት ሄድኩ፡፡ እንደውም እኔም ተፍለቀለቅኩ፡፡ ፈገግታዬና ሙቀቴ የሷን ሊሆን ምን ቀረሁ ብላችሁ ነው፡፡ ቦታዋን ብትለቅልኝ በሙቀቴ አንበሸብሻችሁ ነበር፡፡

መታለሌ የገባኝ ቀኑ ሲገባደድ ነው፡፡ የከተማዋ አድማስ ጥግ ቀድሜ ጠበኳት፡፡ “ማለዳ የሰጠሽኝን ወይም ሠጥቼሀለሁ ያልሺውን እንደተለመደው ጠቅልለሽ ወሰድሽው” አልኳት፡፡

“ስራ አልሰራህበትም እንዴ በጊዜህ?” ጠየቀችኝ፡፡

“ሰርቼአለሁ፡፡ ግን እድሜ ልኬን ሰርቼ የሰበሰብኩትን ልመልስልሽና አንድ ቀን በምትኩ ስጭኝ፡፡”

“ይህማ አይሆንም” … አለችኝ፡፡

በጊዜ የሚነግድ ሁሉ እንደሚከስር ገባኝ፡፡ ምክንያቱም የሸጠውን መልሶ መግዛት አይችልም፡፡ “ግን እኮ ጥሩ ነበር፡፡” አልኳት ሃሳብ ብልጭ ብሎልኝ፡፡

“ምኑ? …”

“አንቺ የንግድ ማእከል ብትሆኝ”

“በምን ስሌት?”

“ማለቴ ቀኑን በአግባቡ ለተጠቀመ ማታ ስትጠልቂ እጥፍ አድርገሽ ብትመልሺለት” ሳቅ አለች፡፡

“እኔ እኮ የምሬን ነው ደግሞሞ አዝኛለሁ” አልኳት፡፡

“ቆይ አላሳዝንሽም?” ቀጠልኩ ምሬቴን - የሚራራ አንጀት ቢኖራት፡፡ ለስዋ የኔ እድሜ ቀልድ ነው፡፡ በየእለቱ የምትቀንስብኝ እድሜ ምንም አይመስላትም፡፡ ለነገሩ እሷ ምን የሚራራ አንጀት አላት? ሆዷ ሁሉ የሚፋጅ ፍም አይደለም እንዴ የሚመስለው - የሚጠብስ፡፡ በዚህ ምክንያት ተኮራረፍን፡፡ በመፍትሄነት ቀኑን ሙሉ እሷን ላለማየት ተኝቼ እውላለሁ፡፡ በዚህ መልኩ ወራት ካለፉ በኋላ … አንድ ጠዋት እሷ ስትወጣ ላለማየት ከተኛሁበት ቀስቅሳ፣

“ሌባ፣ ሌባ ነህ” አለችኝ፡፡ አላቆመችም … “ሳስበው የኔም እድሜ ሄዷል፡፡ ከተፈጠርኩ ጀምሮ ብርሃንና ሙቀት ስሰጥ ኖርኩ፡፡ አንተም ያለአንዳች ክፍያ ስትበዘብዘኝ ቆየህ፡፡ አሁን ጉልበቴ እያለቀ ነው፡፡ እያረጀሁ ነው፡፡ በፊት መጽናኛዬ ለናንተ መኖሬ ነበር፡፡ ስሜን ታጠፋለህ ብዬ አልገመትኩም፡፡ እንዲህ እንፋጠጣለን ብዬ አልጠረጠርኩም፡፡”

ሳዳምጣት ቆየሁ፡፡ ነገሩ ገባኝ፡፡ ለካስ እሷን ጉልበተኛ አድርጌ ያሰብኩት ስህተት ነው፡፡ ሁለታችንም እያረጀን ነው፡፡ ሁለታችንም ወዳጃሞች ነን፡፡

“አሁን ገባኝ ለካ ጉልቤ አይደለሽም፡፡ አሁን ብርሃንሽ አይኔ ላይ ቢያርፍ ግድ የለኝም፡፡ ሙቀትሽ ቢያገኘኝ አልቀየምሽም” አልኳት፡፡

“ግን እኮ እድሜህ መቀነሱ አልቀረም” አለችኝ በስሱ እየሳቀች፡

“ቢሆንም” አልኳት፡፡ ከታረቅን በኋላ ለሚሆነው ግድ የለኝም፡፡

ቀኑን ሙሉ ቀና እያልኩ በትንግርት ስመለከታት ዋልሁ፡፡ ማታ አድማስ ጥግ ስትጠልቅ ጠበኳት፡፡

“ዛሬ ምነው ቸኮልሽ?”

“ቸኮልኩ እንዴ? ደስ ብሎኝ ነው የዋልኩት” … ሳቀች፡፡ ሆሆ… ድንገት ማለዳ ቢሆንስ ደግነቱ ሳቋን ቀነሰች፡፡

“ጠዋት ትመጫለሽ እንዴ?” … ላገኛት ጉዋጉቼ፡፡

“እግዚአብሔር ያውቃል” አለችኝ፡፡

 

 

Read 3132 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 10:24