Monday, 11 January 2016 11:14

እንደ እኛ ሽንኩርትና ቲማቲም ፍለጋ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(12 votes)

“ቦሶቻችን ኑሯችንን ኖረውት ይዩልንማ”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!   
ስሙኝማ… ምን አስባለሁ መሰላችሁ… ‘ቦሶች’፣ ማለት እኛ የዕለት ዕለት ህይወት ላይ ውሳኔዎች የማሳለፍ ስልጣን ያላቸው ‘ቦሶች’፣  ለምን ለአንድ ሳምንት የእኛን ስፍራ አይወስዱም! አሪፍ ሀሳብ አይደል! በዛ ጊዜ ውስጥ እኛ እንኳን የእነሱን ወንበር ‘ልንተካ’ በአጠገቡ ላላማለፍ ቃለ እንገባለን፡፡
እናማ…አለ አይደል…ለሰባት ቀናት ያህል ይተኩንና ኑሯችንን ‘ኖረውት’ ይዩልንማ፡፡ አለበለዛ ሸክማችን አልታወቀልንም፣ ወይም ታውቆ እንዳልታወቀ ሆኖብን ተቸግረናል፡፡ ታዲያማ በዛች በሰባት ቀን ውስጥ እኛ የምንይዛትን ያህል ፈረንካ ነው መያዝ ያለባቸው፡፡  አለበለዛ ነገርዬው ሁሉ ፉርሽ ይሆናላ!
እናላችሁ…እህል በረንዳ ይሂዱልን፡፡ (እህል በረንዳ ማለት እህል የሚሸጥበት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ቦታውን ለማሳየት ፈቃደኞች ነን፡፡) እናማ… “አንድ ኩንታል ጤፍ…” ብለው ይጠይቁ፡፡ “አንድ ኩንታል ጤፍ ሁለት ሺህ ምናምን ብር…” ሲባሉ ሰውነት እንዴት ኩምሽሽ እንደሚል ደርሶባቸው ይዩልን፡፡
የእነሱ መሶብ ለእኛ መሶብ ቅርብ በነበረችበት ዘመን “ምን የመሰለና ሻሽ የሚመስል አንደኛ ደረጃ ጤፍ ሁለት መቶ ምናምን ብር…” የሚባለው ነገር ታሪክ የመሆን ሂደቱን አጠናቆ ወደ ‘አፈ ታሪክነት’ እንደተለወጠ ይዩልንማ! እናማ “ጤፉ ከአቅማችን በላይ ሆነብን፣ መሶባችን ሳሳብን…” ስንል ጠግበን እንዳልሆነ ልብ ይባልልን፡፡
ስሙኝማ…ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ጤፍና እኛ እየተራራቅን ስንሄድ “በጤፍ መሥራት ይቻላል” የሚባለው የምግብ አይነት መብዛቱ!  ‘የጤፍ ጨጨብሳ፣’ ‘የጤፍ ኬክ፣’ ‘የጤፍ ገንፎ፣’ ምናምን ብሎ ነገር… ያኔ ‘አቅሙ ያለን ጊዜ’ ለምን አልነገራችሁንም!
እናማ…ቦሶች ‘ኑሯችንን ኖረውት’ የጤፍን ነገር ይዩልንማ፡፡
ደግሞ…እንደ እኛ ሽንኩርትና ቲማቲም ፍለጋ አትክልት ተራ ይሂዱልን፡፡ (አትክልት ተራ ማለት አትክልት የሚሸጥበት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ቦታውን ለማሳየት ፈቃደኞች ነን፡፡) እናማ… አዎ…ይሂዱና “አንድ ኪሎ ሽንኩርት…” ወይ “አንድ ኪሎ ቲማቲም…” ምናምን ብለው ይጠይቁ፡፡ “አንድ ኪሎ ሽንኩርት አሥራ ምናምን ብር…” ሲሏቸው፣ ትከሻቸው ላይ ያለችው (ይቅርታ…‘ያለው’) ‘ክብደት’ እርግፍ እንደምትል የእኛም እንዲሁ ነው እርግፍ የምትለው፡፡ እናማ…ትከሻችን ‘ከመሬት ተነስቶ’ አልሳሳም ለማለት ነው፡፡ እነሱ ከእኛ እንዲህ ባልራቁበት ዘመን…አለ አይደል…እንደ አሎሎነት ሊያገለግል የሚችል ‘እኔ ነኝ ያለ’ ሽንኩርት ኪሎው በሁለት ብርና በሦስት ብር የሚሸመትበት ዘመን ታሪክነቱ አብቅቶ አፈ ታሪክ እንደሆነ ይዩልንማ!
እናማ…ቦሶች ኑሯችንን ኖረውት የሽንኩርትና የቲማቲም ነገር ይዩልንማ፡፡
ደግሞላችሁ…እንደ እኛ ሸማቾች ሱቅ ስኳር መጣ አልመጣ እያሉ አሥራ አምስት ቀን ይመላለሱልንና መጣ በተባለ ቀን በሌሊት ሄደው ይሰለፉልን። ሦስት ሰዓት ሙሉ ተሰልፈው ከጠበቁ በኋላ “ስኳር ዛሬ አልደረሰም…” ተብለው ‘ወሽመጥ መበጠስ’ የሚባለው ነገር ምን ማለት እንደሆነ እነሱ ላይ ደርሶ ይዩልንማ! “ደግሞ ለእናንተ ስኳር ምን ያደርግላችኋል!” ካልተባልን በስተቀር ማለት ነው፡፡
እናማ…ቦሶች ኑሯችንን ኖረውት በቀን አንድ ብርጭቆ ለምንቀምሳት ሻይና፣ በሳምንት አንድ ስኒ ከንፈሮቻችንን ለምናረጥብባት ቡና ነገር ስኳር ለማግኘት የምንሳቀቀውን ይዩልንማ፡፡
ደግሞ እስቲ ‘ሥራ አጥ’ ሆነው ሥራ ማጣት ምን ማለት እንደሆነ ይዩልንማ፡፡ ‘ኮሌጅ በጥሰው፣’ የ‘ግራጁዌሽን’ ፓንች ቀምስው አቃምስው፣ የምረቃ መጽሔት ላይ “የእኔ ዓላማ በሙያዬ አገሬን ማገልገል ነው…” ምናምን የሚል አይነት ‘ፓትሪዮቲክ’ አስተያየት ከሰጡ በኋላ ሦስት ዓመት ሙሉ ሥራ ሳያገኙ መንከራተት ምን ማለት እንደሆነ ይዩልንማ። ከዛ ደግሞ ለሁለት ክፍት የሥራ ቦታ ለመመዝገብ ከሁለት ሺህ ሰው ጋር ሲጋፉ መዋል ምን አይነት ስሜት እንደሚያሳድር እነሱም ለሰባት ቀናት ‘አንኢምፕሎይድ’ ምናምን ሆነው ይዩልንማ፡፡
እናማ…ቦሶች ኑሯችንን ኖረውት… “እሰይ ልጃችን ደረሰልን/ደረሰችልን…” ከተባለ በኋላ ሥራ አጥቶ መቀመጥ ምን ማለት እንደሆነ ይዩልንማ፡፡
ደግሞ…እስቲ የራሳቸውን አምስትና ሰባት መኝታ ቤት ቪላ ምናምን ይርሱትና አንዲት ክፍል የቤት ኪራይ ይፈልጉ፡፡ እናማ…እንደ እኛ ይንከራተቱና ጣራና ግድግዳ የሌለው ቤት—አልባ ተከራይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይወቁልን፡፡ ጣራዋ አራት ቦታ፣ ግድግዳዎቿ አምስት ቦታ ለተበሳሳ ሁለት ክፍል፣ ምናምን ዲግሪ ለተንጋደደች ‘ቤት’ ሁለት ሺህ አምስት መቶ  ብር…” ሲባሉ ልባቸው እንዴት ዘፍ እንደምትል ይዩትማ፡፡ ደግሞላችሁ…ቤት ከተገኘ በኋላ ከአሥርቱ ትዕዛዛት የገዘፉ ሌሎች ትዕዛዛት እንዴት እንደሚጫኑብን ይወቁልንማ…
“መብራት ሦስት ሰዓት ላይ ይጠፋል…”
“የቴሌቪዥን ድምጽ ከፍ ማድረግ የተከለከለ ነው…”
“ማንም እንግዳ መምጣት አይችልም…”
“በቀን ከአንድ ባድሊ በላይ ውሀ መቅዳት አይቻልም…”
“የኤሌትሪክ ምድጃ መጠቀም አይቻልም…
“ካውያ መጠቀም አይቻልም…”
አይቻልም…አይቻልም…አይቻልም…
አሥርቱ ትዕዛዛት እንኳን እንዲህ አይጠነክሩም!
ደግሞላችሁ…ጉዳይ ለማስፈጸም ፋይላቸውን ተሸከመው እንደ እኛ ከቢሮ ቢሮ ይዘዋወሩልንማ።  ያኔ ነው…አለ አይደል… እዚህ አገር ሳይንከራተቱ ጉዳይ ከማስፈጸም ኋይት ሀውስ ውስጥ ‘ጌት ቱጌዘር’ ለማድረግ ጠይቆ ማስፈቀዱ ሳይቀል እንደማይቀር የሚጠረጥሩት…ልክ እንደኛ ማለት ነው፡፡ የምር እኮ ጉዳይ ማስፈጸም በባለ ጉዳዩ ላይ የሚያስከትላቸውን አካላዊና አእምሯዊ ጉዳቶች የሆነ ባለሙያ ሊያጠናልን ይገባል፡፡
እናማ… ቦሶቻችን ጉዳይ ሊያስፈጽሙ ይሂዱና የሚያናግራቸው ሲያጡ፣ የሚያናግራቸው ሲገኝም ዋናው ፋይላቸው ‘ሲጠፋ፣’ ፋይሉም ሲገኝ ፈራሚው ባለስልጣን “ስብሰባ ላይ ናቸው…” ሲባል፣ ባለስልጣኑም ሲገኝ “ይሄ ፋይል እኔን አይመለከትም…” ብሎ ወደመጣበት ሲመልሰው… ያኔ እዚሀ አገር ጉዳይ ማስፈጸም ምን ማለት እንደሆነ ያዩልናል፡፡ እናማ…ቦሶች ‘ኑሯችንን ኖረውት’ ጉዳይ ማስፈጸም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይዩልንማ፡፡
ደግሞላችሁ…በሚኒ ባስ ታክሲ ይሳፈሩልንና፣ ሌሎች ችግሮቻችን አልበቃ ያሉ ይመስል፣ እንዴት ከታሪፍ በላይ ለመክፈል እንደምንገደድ፣ እንዴት መጨረሻው ሳንደርስ “መጨረሻው እዚህ ነው…”  ተብለን ለመውረድ እንደምንገደድ፣ “አጭር መንገድ አንሄድም…” ተብለን ከተሳፈረንበት ታክሲ እንዴት ‘እንደምንራገፍ’፣ እንዴት ‘እንደ ልባቸው’ የሆኑ አንዳንድ ሾፌሮችና ረዳቶች ስድብ መለማመጃ እንደምንሆን… ቦሶቻችን የእኛን ኑሮ ለሳምንት ኖረው ይዩልንማ፡፡
እንደ እኛ አውቶብስ ይሳፈሩልን፡፡ እናማ…በተጨናነቀ፣ አየር በማይዘዋወርበት አውቶብስ ውስጥ ተፋፍጎ መሄድ ምን ማለት እንደሆነ ይዩልንማ፡፡ ያኔ ምናልባት በጥቂት መቶ አውቶቡስ ከመኩራራት ወደ ሺዎች ቁጥር እንገባ ይሆናል፡፡
እናማ…
የአምናን ቀን ረገምኩት ለአፌ ለከት የለው
የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው
የምንለው ‘ተረት መተረት ስለለመደብን’ ሳይሆን ትናንት አንድ መቶ የነበረው ሸክም ዘንድሮ አንድ መቶ ሀምሳ እየሆነ ሲያስቸግረን እንደሆነ ቦሶች ኑሯችንን ለሳምንት ኖረው ይዩልንማ!
ደግሞ እንማሳሰቢያ… “ወክለናቸዋል…” ብለን በውልና ማስረጃ የተረጋጋጠ የተፈራረምነው ነገር ስለሌለ…አለ አይደል… በአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚሰጠው ሀሳብና አስተያየት የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሀሳብ ብቻ እንደሆነ ይታወቅልንማ፡፡ “ይሞታል እንዴ…” ያለው ዘፋኝ ሌላ ተመሳሳይ ዘፈን አውጥቷል እንዴ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3953 times