Saturday, 02 January 2016 11:49

“በቀላሉ ባቡር መንሸርሸር ለምደሽ …”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ያው እንደተለመደው ከተማችን “ታላቅ ቅናሽ” ‘Sale’ ምናምን የሚሉ ማባበያዎች በብዛት እየታዩ ነው፡፡ ኮሚክ እኮ ነው… እዚሀ አገር መጀመሪያስ ነገር ብዙዎቹ ዕቃዎች፣ በተለየ ደግሞ አልባሳት፣ በድርድር አይደል እንዴ ሸመታ የሚካሄደው! እናማ…ከምኑ ላይ እንደቀነሱ ለማወቅም አስቸጋሪ ነው፡፡ መጀመሪያ የ‘እርግጡን ዋጋ’ ሳናውቀው…“ምናምን ፐርሰንት ቅናሽ…” የሚሉትን ባናምን አይፈረድብንም፡፡
ሌላ ደግሞ ‘Sale’ ማለት በሚጢጢው እንደሚመስለን ‘ማጣሪያ’ ሽያጭ ነው እንጂ ‘ታላቅ ቅናሽ’ ቅብርጥስዮ አይደለም፡፡ እናማ ‘Sale’ የምትሉ ሰዎች የመቶ ብሯን ዕቃ በአሥርና በአምስት ብር ምናምን መሸጥ ነው፡፡ ልክ ነዋ… ከ‘አማሪካን’ ሦስትና አራት ሻንጣ ልብስ በስጦታ የሚመጣው ምስጢሩ ‘Sale’ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እኔ የምለው፣ የባቡር ሀዲድና ቀላል ባቡር በየድራማው ላይ ብቅ፣ ብቅ ማለት ጀመሩ አይደል! ገና ወላ የዘፈን ክሊፕ፣ ወላ ምን በሉት…ሀዲድ በሀዲድ… ባቡር በባቡር ባይሆን! ደግነቱ እስካሁን ሀዲዱ ላይ መጨፈር አልተፈቀደም መሰለኝ፡፡
ያኔ ቀለበት መንገዱ ‘አዲስ’ የነበረ ጊዜ እንዲሁ ነበር፡፡ የትራፊክ ህግ የለ…‘አካፋዩን መዝለልና ላዩ ላይ ‘አይ ላቭ ዩ ሞር ዛን አይ ካን ሴይ’ አይነት ለአደጋ ያጋልጣል ማለት የለ…ብቻ ምን አለፋችሁ… ሲደነከርበት ከረመላችሁ፡፡
እናላችሁ… ከባቡር ሀዲዱ ጋር መክረማችን ካልቀረ ለምን የዘፈን የምናምን ግጥሞች በዛው አይጻፉልንም፡
ትመጫለሽ ብዬ ማዶ ማዶ ሳይ
ይሄ ቀላል ባቡር መቅረቱ ነው ወይ
አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ… ያውም በኤሌትሪክ መቋረጥ አንዳንዴ ቀጥ እያለ ነው እየተባለ ባለበት ጊዜ…በሰዓቱ ትድረስ፣ አትድረስ ማን ያውቃል!
ደግሞም ሌላ አለላችሁ…
በቀላሉ ባቡር መንሸርሸር ለምደሽ
ከእኔ ከድሀው ጋር መች ትሄጃለሽ
ልክ ነዋ! ዘንድሮ ልጄ…
“ድሀ የዋህ ነው…”
“ከጠገበ ሀብታም የተራበ ድሀ ይሻለኛል…”
ምናምን የሚባሉ ነገሮች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አብቅቷል፡፡ ተወደደም ተጠላም እንዲሉት አማርኛ…ተወደደም ተጠላም ፈረንካ ዘንድሮ ሁሉንም ነገር እያሽከረከረ ነው፡፡
እናማ…
“ከእሱ ጋር ቆሎ ቆርጥሜ እኖራለሁ…ከዕለታት አንድ ቀን ያልፍልናል…” ብሎ ነገር የለም፡፡
እናላችሁ ባቡርና ሀዲድ ድራማ ላይ መምጣታቸው ካልቀረ ውሀ ባይኖርም ነገ፣ ተነገ ወዲያ እንደ ‘ቢች’ ማገልገላቸው ካልቀረ ግጥሞች አሁኑኑ ይገጠሙልንማ፡፡
እንደ ባቡሩ ሀዲድ የተጠመጠመው
እንደ ባቡሩ ሀዲድ የተጠማዘዘው
ምን መስሎሽ ነበረ የእኔ ልብ እኮ ነው
ቂ…ቂ…ቂ…. የምር ግን እንዲህ ብሎ የሚገጥም ሰው መጀመሪያ ኤ.ኬ.ጂ. ነው ምናምን የሚሉትን ነገር ነው መታየት ያለበት፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ከተማችን ‘ህንጣ በህንጣ’ አይደል…ህንጻዎቹ አናት ላይ ሳይቀር ዘፈንና ምናምን ሁሉ ተጀምሯል፡፡ የምር ግን…በዚህ አይነት ነገር ከዓለም ከቀዳሚዎቹ መሀል ሳንሆን አንቀርም። ታዲያላችሁ…
 በህንጻው አናት ላይ የቆምኩት አሁን
 ከሺህ ሰው መካከል አይሽ እንደሆን
ምናምን ማለት አሪፍ አይደል! “ስንቱን አሳልፌው እዘልቀው ይሆን…” የሚለውን ‘አፕዴት’ እንደማድረግ ማለት ነው፡፡
የምር ግን ይሄ የኮፒራይት ነገር መልክ ሲይዝ የዘፈን ግጥም መሞከር አለብኝ፡፡
እንደ ባቡሩ ሀዲድ ልብሽ የረዘመው
አልጎተት አለኝ ብስበው፣ ባስበው
ይሄ አሁን ምን ይወጣለታል!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በየፊልሙና በየድራማው ላይ መአት ተዋንያን እያየን ነው፡፡ አንዳንዴ ግን… አለ አይደል… “እንደው አሁን ከዚህኛው/ከዚችኛዋ ሻልየሚል  ሰው ጠፍቶ ነው!” እንላለን፡፡
በዛ ሰሞን… አንድ ሬድዮ ጣቢያ ላይ “እንዴት እንደማይተወን የሚያሳዩ ተዋንያን…” ምናምን ተብሎ የተጠቀሰው አይነት ማለት ነው፡፡ እኔ የምለው…እሱ ፕሮግራም ምነው ባለፈው ሳምንት ቄሱም ጭጭ፣ መጽሐፉም ጭጭ ሆነ! ‘ሰዎች አስቀየመ’ እንዴ!
እናማ…‘የማለዳ ኮከቦች’ ላይ የምናያቸው ልጆች የምርም ይቺ አገር የተዋንያን ችግር እንደሌለባት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዳኞቹ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሟትን ቃል ለመጠቀም “የሚገርም ችሎታ” ያላቸው መአት ልጆች አሉ፡፡ እናማ… የተዘጉ በሮች በበዙበት ዘመን የትወና ዓለምን ቶሎ እንዲቀላቀሉ አንድዬ በሩን ወለል አድርጎ ይክፈትላቸውማ!
ስሙኝማ… የድራማዎችን ነገር ካነሳን አይቀር…አሁን፣ አሁን አንዳንዴ ግራ የመጋባት ነገር እየገጠመን ስለሆነ ታሪኮቹን እያጠራችሁልን ሂዱማ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ስሙኝማ፡፡ እሷዬዋ ለጓደኛዋ ስለሆነ ሰው እየነገረቻት ነው፡፡
“ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ… ‘በጣም ታምሪያለሽ’ አለኝ፣” ትላታለች፡፡
ጓደኝዬዋ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው…
“ፍቅር እውር ነው የሚሉት እውነታቸውን ነው፣” ብላት አረፈች፡፡
የዘንድሮ ጓደኝነት! ያቺኛዋ እኮ በሆዷ… አለ አይደል… “ቆይ ብቻ፣ ቀላል ባቡር ሀዲድ ላይ ክሊፕ ሠርቼ ኮረንቲ ባላስጨብጣት!” ምናምን ልትል ትችላለች፡፡
እናማ ቀላል በባሩንና ሀዲዱን ታሳቢ ያደረጉ ግጥሞች አሁኑኑ ተዘጋጅተው ይቀመጡልንማ፡፡
እኔ እዚህ ታቹን ኮብልስቶን ላይ
አንቺ ከበላዬ በሀዲዱ ላይ
ምሰሶ ቧጥጬ ልመጣ ነው ወይ!
ይቺ የምር አሪፍ ነች፡፡ በነገራችን ላይ ሁሉም ‘ስንኞች’ (“ተባለ!” የሚሉ አራዶች አንድ ዘመን ላይ ነበሩ፣) ለ‘ፍሪ ዳውንሎድ’ ዝግጁ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው፡፡
እስቲ ሸመታውም በልኩ ይሁን…
ሲፑም’ በልኩ ይሁን…
በሰው ሰው ላይ ‘ጆፌ መጣሉም’ ለሌላ ጊዜ ይተላለፍና መልካም የበዓል ሰሞን ይሁንላችሁማ!
ገንዘብ ካጠረ ‘ጥቆማ’…“ገንዘብ ስትበደር ከጨለምተኛ ሰው ተበደር…” የሚሏት ነገር አለች። ለምን መሰላችሁ… ጨለምተኛ ስለሆነ “ገንዘቤን ይመልስልኛል…” ብሎ አያስብማ፡ አሪፍ ስትራቴጂ አይደለች!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 3367 times