Saturday, 02 January 2016 11:46

እንብላም ካላችሁ እንብላ አንብላም ካላችሁ እንብላ (የአያ ጅቦ ፍልስፍና)

Written by 
Rate this item
(30 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ አንድ ክፉ ሚስት ነበረችው፡፡
ጠዋት አልጋ ላይ እያለች፤
“ተነስ አቶ ባል፤ እሳት አያይዝና ቁርስ ሥራ!” ብላ በቁጣ ታዘዋለች፡፡
አቶ ባል፤
“ኧረ እሺ መቼ እምቢ አልኩና ትቆጪኛለሽ የእኔ እመቤት!” ይላታል፡፡
ሚስት፤
“ተነስ ብያለሁ ተነስ! የምን መልስ ነው ደሞ!”
ባል ፍንጥር ብሎ ካልጋ ወርዶ ወደ እሳት ማያያዙ ይገባል፡፡
እጇንና ፊቷን አስታጥቦ ሲያበቃ፤ ቁርሷን ያበላታል፡፡ ከዚያ ሞፈር ቀንበሩን ይዞ ወደ እርሻው ይሄዳል፡፡
ማታ ሲመለስ ደሞ “ና እግር እጠብና፤ እራት አቅርብ፣ ና ታጠብና ተኛ!” ትለዋለች፡፡
ከዚች ክፉ ሚስቱ ጋር ብዙ ዓመት ኖረው ባጋጣሚ ታመመችና ሞተች፡፡ ብዙ ዓመት ደግሞ ያለ ሚስት ኖረ፡፡ መንደሬው ሀዘን ይበቃሃል ብሎ ለሌላ ሚስት ዳረው፡፡
ይህችኛዋ ሚስት ደግሞ “ምን ሲደረግ ማዕድ ቤት ባል ይገባል? ምን ሲደረግ ሴት እያለች ባል ወጥ ቤት ይገባል? ምን ሲደረግስ ወንድ ሥራ ሲደክም ውሎ ቤት ሲገባ በሴት ሥራ ገብቶ ጉድ ጉድ ይላል?” የምትል ሆነች፡፡
ስለዚህም፤
ከአልጋ ሲወርድ ገንፎውን አዘጋጅታ፤ ባፍ በአፉ ታጐርሰው ጀመር፡፡
ከሥራ ሲመጣም፣ አግሩን ለማጠብ ውሃ አሙቃ አዘጋጅታ እግሩን አጥባ፣ ራቱን አብልታ፣ ገላውን በቅባት አሽታ ታስተኛዋለች፡፡
ይህ እንክብካቤ እጅግ አድርጐ አስደሰተው፡፡ ሆኖም የሰው ነገር ሁሌም የተሻለ መመኘትና የያዝኩት አይበቃኝም ማለት ነውና እንዲህ ሲል ፀለየ፡-
“ከዚች የተሻለች የማገባ ከሆነ
ምነው እቺም በሞተች?”  
*   *   *
የሰው ልጅ በቃኝን አያቅም፡፡ የኢኮኖሚ ምርምር አባት የሆነው አዳም ስሚዝ እንዳለው፤ “Human wants are unlimited” (የሰው ልጅ ፍላጐት ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም) ይህንን ፍላጐት ወደ ህብረተሰብ ፍላጐት ስንመነዝረው የአገር ጥያቄ ይሆናል፡፡ የመጠለያ ጥያቄ፣ የምግብ ጥያቄ፣ የአልባሳት ጥያቄ፣ ከዚያ ደግሞ የነፃነት ጥያቄ፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ፣ የፍትሕ ጥያቄ ይዥጐደጐዳል፡፡ አንዱ ቢሟላ ሌላው ይቀጥላል፡፡ ይህ የሰው መሠረታዊ ባህሪ ከጥንስሱ የማይቆምና አይቀሬ ሂደት ነው፡፡ ከቤተሰብ እስከ መንግሥት ድረስ ያሉት አካላት እነዚህን ፍላጐቶች አውቀው፣ ተረድተው፣ መልክና ቅጥ አበጅተው ኑሮን የሚያሳኩ ናቸው፡፡ ፍላጐት በመነጨ ቁጥር ሳይቆጡ፣ ሳያፈጡ፣ ዐይን ሳያጉረጠርጡ መፍትሔውን መሻት ግዴታ ነው፡፡ ኃላፊነት ነው፡፡ አሊያ ተጠያቂነት አይቀሬ ነው፡፡ የመጠለያ ችግር መሠረታዊ ነው፡፡ የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ችግር መሠረታዊ ነው፡፡ አንገብጋቢም ነው፡፡ መፈታት አለበት፡፡ የህዝቡ ኑሮና የአገር ኢኮኖሚ መጣጣም አለባቸው፡፡ ያ ካልሆነ ብሶትና ምሬት ይወለዳሉ። እነዚህ በፈንታቸው እምቢተኝነትን፣ አመጽን ይፈለፍላሉ፡፡ ስለዚህ ችግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው፣ መላ ሊመታባቸው፣ መፍትሔ ሊያገኙ፣ በብስለት ሊቃኙ ይገባል፡፡ መልካም አስተዳደር እኒህን ሁሉ ይጠቀልላል፡፡
ስለመልካም አስተዳደር እያወራን ስለሙስናም ካላሰብን፣ ስለሙስና እያወራን ስለፍትህ ካላሰብን፣ ስለፍትህ እያወራን ስለዲሞክራሲያዊ መብቶች ካላሰብን፣ ስለዲሞክራሲ እያወራን ስለኢንቨስትመንት እንቅፋቶች ካላወሳን የምናውጀው መሬት አይረግጥም፡፡ አንዱን ቀዳዳ ደፈንን ብለን በሚዲያ ስንኩራራ፣ ሌላው ቀዳዳ የበለጠ አፉን ከፍቶ ይውጠናል፡፡ “አይጧ ከሌለች ጉድጓዱ ከየት መጣ?” ማለት አለብን፡፡ አሁንም የባለሀብትንና የቢሮክራሲውን ሽርብ አሻጥ መፈተሽ አለብን። ምክንና ውጤቱን (Cause and effect እንዲሉ) ማጤን አለብን፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ካፈጠጠው ሙስና ጋር ይጋጫል፡፡ መሬት ሸንሽኖ ከሸጠ፣ የኪራይ ቤቶችን ቤት በእጁ ካስገባ፣ በሥልጣኑ ያሻውን እያረገ በፍርደ ገምድልነት ህዝብን ካስለቀሰ በኋላ፤ እንደ ጨዋ ስለመልካም አስተዳደርና ስለህዝብ መበደል የሚለፍፈው እጅግ እየበረከተ መጥቷል፡፡ የኋላዬ አይፈተሽም፣ አይመረምርም በሚል በአደባባይ ኮርቶ የሚናገረው በዝቷል፡፡ ሁኔታው ቢያመች በለመደው ሌባ እጁ ያገኘውን ከመመዝበር ወደ ኋላ አይልም፡፡ ምነው ቢሉ? ልቡ በአያ ጅቦ ፍልስፍና የተጠመቀ ነውና “እንብላም ካላችሁ እንብላ፡፡ አንብላም ካላችሁ እንብላ” ከማለት አይመለስም፡፡  

Read 9563 times