Tuesday, 29 December 2015 07:32

ከሴት ገላ ላይ ጥበብን ፍለጋ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(24 votes)

    የጥበብ አለም ሰው ነኝ፤ እላለሁ ለራሴ። ተደጋግሞ የሚባለውን ነገር ሳላምንበት ለምን ሰው በሌለበት ለራሴ እንደምደጋግም አላውቅም፡፡ የጥበብ አለም ሰው ነኝ!..ምን ማለት ነው? እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምን ማለት ነው ሰው?...ፍቺው ለእኔ ቋጠሮ ነው፡፡ የጥበብ አለም ሰው ነኝ ከማለት ግን ቦዝኜ አላውቅም፡፡
ጥንቅቅ ያለ የሴት ገላ ሳይ አውቃለሁ፡፡ እውቀቴ ላይ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይኼንን እውቀቴን ደግሞ መግለጽ መቻል አለብኝ…፡፡ ስለዚህ ሰዓሊ ሆንኩኝ። ሰዓሊነት የጥበቃ ህይወት ነው፡፡ ጥበቃው የሚሳል ነገር እስኪገኝ ይቀጥላል፡፡ እኔ መሳል የምፈልገውን ነገር አውቃለሁ፡፡  ግን እስካሁን የምፈልገው ተሟልቶ አግኝቼ አላውቅም፡፡
የሴት ገላ ላይ ለነገሩ ሁሉም ጠቢብ ነው። አንዳንዱ “እግዜር እጁን ታጥቦ የሰራትን” ሴት የሚፈልጋት…እጁን ታጥቦ ሊበላት ነው፡፡ አመጋገቡ እንደ ግለሰቡ ይለያያል፡፡ የሴቲቱን ገላ በአይኑ የሚመገብና የሚጠግብ ይኖራል፡፡ ሌላው ደግሞ ጠብሶ ካበሰላት በኋላ በእንጀራ ሳይሆን በብርድልብስና አንሶላ ጠቅልሎ ነው ሊጐርሳት የሚፍጨረጨረው፡፡
የእኔ አመጋገብ ግን የተለየ ነው፡፡ አመጋገቤም ሆነ ርሐቤ ከተለምዶው ወጣ ያለ ነው፡፡ የእኔ ረሀብ የቆንጆ ሴትን ገላ በሸራ ላይ የመግለጽ ነው። አግብቼ ላስረጃት ወይንም ልጅነቴን በልጆቼ ላይ፣ በእሷ መሐፀን በኩል ማየት እንድችልም አይደለም፤ የሴትን ገላ የምናፍቀው፡፡ ውበትን የመጨበጥ ነው። ዘመንና ህይወት ወደ አፈር የሚያወርደውን የሴት ገላ…በጊዜ ደርሼ… አፍሼ በሸራዬ ላይ  ዘላለማዊ ማድረግ ነው ትርፌ፡፡
ግን ይህ ተሳክቶልኝ አያውቅም፡፡ በመሰረቱ፤ በአካል ህይወት ላይ ህያው ሆና፣ ያልተሸራረፈ ውበት ያላት ሴት ሳይረፍድ ደርሼባት አላውቅም። “ወይኔ ከሰላሳ አመት በፊት ባገኝሽ ኖሮ” ብዬ የተቆጨሁባት አንዲት ሆስቴስ ትዝ ትለኛለች፡፡ ከድሮ ፎቶግራፎቿ ላይ እንድስል ፈቅዳልኝ ነበር፤ ቁጭቴን ሰምታ፡፡ ግን ከፎቶግራፍ ላይ የውበት ቋንጣ እንጂ ህያው እስትንፋስ ያለው ጥበብ ማግኘት አይቻልም፡፡ ፎቶግራፉን ሳልመልስላት ሸሸሁዋት፡፡ የድሮ ምግብ ዛሬ እንደማይበላው፣ የድሮ ቁንጅናም ከፎቶግራፍ ላይ አንስቼ ብስለው የእኔን ርሐብ ከመሸንገል በስተቀር ጠኔዬን አያስታግስም፡፡
አብረን ከሥዕል ትምህርት ቤት የተመረቅነው ወዳጄም ሴቶችን መሳል ይወዳል፡፡ እሱም እንደኔው ከፎቶግራፍ ሳይሆን ህያው ገላ ያላቸውን ሴቶች ልብስ አስወልቆ ነው የሚስለው፡፡ ደምና ስጋቸውምን ወደ ሸራው ይገለብጣል፡፡ በእኔና በዚህ ጓዴ መሀል ያለው ልዩነት… እኔ የተሟላ ውበት በራቁት ገላቸው ላይ ስፈልግ… ለእሱ ግን ህያው ስጋና ደም ያላቸው መሆናቸው በቂው ነው፡፡
“እቺን ሞዴል ከየት አግኝተሀት ነው?” አልኩት። አውቃለሁ፤ ልብሷን አውልቃ የሰዓሊው ብሩሽ የጡቶቿ መሀል… በኋላም ወረድ ብሎ በጭኖቿ መሀል ስትኮረኮር … “በጥበብ ስም ነው” ብላ ወደ ሌላ ጥያቄ የማትነዳ ሴት በቀላሉ አትገኝም፡፡
“የጐረቤቴ ልጅ ናት” አለኝ በአጭሩ፤ በስሱ እየሳቀ፡፡ የዚህ ልጅ ማህበራዊ ህይወት በጥበብ ምክንያት ሳይወሳሰብ አልቀረም ብዬ አሰብኩኝ፡፡
“እና ስለሀት ስትጨርስ ያወለቀችውን ልብስ መልሳ ለበሰች?”
“አይ ልብሷን ከመልበሷ በፊት…ስዕሉ ምን እንደሚመስል ራቁቷን ከጐኔ ቁማ አየች” አለኝ፤ አሁንም እየሳቀ፡፡ ስዕሉን ካየች በኋላ አንሶላውን አብረው መጀመሪያ ለብሰው፣ ከዚያ ሁለቱም ያወለቁትን ልብስ በእስቱዲዮው ውስጥ በፀጥታ ሲለብሱ በምናቤ ታየኝ…
የጐረቤት ልጅ እኔም አለችኝ…ግን ለስዕል በጭራሽ ላስባት አልችልም፡፡ ቆንጆ ናት፤ ግን በቻይና ሱሪ መጠን ነው፡፡ በብዛት አምሳያ ያላት ቆንጆ ነች፡፡ ወጣት መሆኗ ራሱ ቆንጆ ያደርጋታል፤ ግን ለእኔ ሸራ ብቁ አያደርጋትም፡፡ ውበት በሁሉም ላይ በጥቂቱ ጭልጭል እያለች ተቀባብታ ትገኛለች፡፡ ከውበት ቅል… ሁሉም ወጣት ሴቶች ትንሽ ትንሽ ተፈጥሮ በእጇ ዝቃ የቀባባቻቸው የሚመስል ነገር አለ፡፡…ለዚህ ሰዓሊ ጓደኛዬ ይኼ ጭላንጭል በቂው ነው …የልብስ ቅርፊታቸውን ካወለቁ ይስላቸዋል፡፡ እኔ ግን የምፈልገው ውበትን የተቀባችውን ሳይሆን ውበትን ራሱን የሆነችዋን ሴት ነው፡፡ ምን አይነት ሴት ናት? ብትሉኝ፤ ልገልጽላችሁ አልችልም፡፡ የተሟላውን ውበት መግለጽ እግዜርን ለመግለጽ ከመሞከር እኩል ነው፤ ወይንም አይተናነስም፡፡
የተሟላ ውበትን ገልፆ ሊፈጥረው የሚችለው ፈጣሪ ራሱ ብቻ ነው፡፡ የእኔ ስራ መጠበቅ ነው። ይህንን የተሟላ ውበት በሴት ገላ አማካኝነት ፈጣሪ ሲገልፀው… እኔ ጠብቄ መቅዳት መቻል ነው ርሐቤ። በህይወት የመኖሬ ምክንያትና ግብም ነው። ግን እድለኝነትም ይጠይቃል፡፡ ፈጣሪ እጁን ታጥቦ የገለፀው ውበት፣ በጐዳና እዩኝ እያለ ሲያልፍ እኔ በአካባቢው ላልኖር እችላለሁ፡፡ ሰላሳ አመት ውበት ሲመላለስ ከነበረበት ጊዜ ዘግይቼ በስፍራው ልገኝ እችላለሁ፡፡ ለሆስቴሷ ውበት እንደዘገየሁት፡፡ ቸኩዬ የማይሆን ገላ ላይ በብሩሽና ቀለሜ ከመስፈር ግን…መጠበቁ ይሻለኛል፡፡
ጥበቃና እምነት በአንድ ላይ ተደራርበው ለረጅም ጊዜ ያለ ውጤት አሹኝ፡፡ የጐረቤትና የጐዳና ሴት በስዕል ስም ሳይሆን በማሽኮርመም ስም እየተጠጋ ልብሳቸውን የሚያስወልቀው የሞያ ጓደኛዬ ስኬታማ ሆነ፡፡ ይስላል፡፡ ይሸጣል፡፡ ከጐዶሎ ገላዎች ውስጥ የተሟላ ውበት ለመፍጠር ይጥራል፡፡ እሱ ተሳክቶልኛል ይላል፡፡ እኔ ከሽፈሃል እለዋለሁ፡፡ እንዲህ እየተባባልን ዘለቅን፡፡
“አንተ የምትፈልጋትን አይነት ሴት ወደ ሲኤምሲ ሰፈር አካባቢ…ወደ ጃክሮስ መስመር አንድ የቡና ላኪ በከፈተው ካፌ ውስጥ አግኝቼልህ ፎቶ አነሳሁዋት” ብሎ ሞባይሉን አውጥቶ አሳየኝ፡፡ ሞባይሉን ተቀብዬው ምስሉን ከመመልከቴ በፊት… ልቤ ደረቴን አፍርሶ ሊወጣ ሲታገል በጆሮ ግንዴ በኩል ንዝረቱ ይሰማኛል፡፡
ልጅ እያለሁ እንደ የመሲህነት ተፈጥሮ ነበረኝ። ለምሳሌ፤ አስተማሪው ብላክቦርዱ ላይ መፃፍ ከመጀመሩ… በፊት እኔ ቀድሜ ምን እንደሚጽፍ በእርግጠኝነት አውቅ ነበር፡፡ ወይንም ይመጣል ብዬ የተነበይኩት ሰው በተነበይኩት ሰዓት የቤታችንን በር መጥቶ ሲያንኳኳ እናቴ ትገረምብኝ ነበር፡፡ ግን ይህ ተፈጥሮዬ እያደግሁ ስመጣ ቀስ እያለ ከናካቴው ጠፋብኝ፡፡
ጠፍቶብኝ ቆይቶ፣ ደግሞ የተከሰተው ሞባይሉ ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ልክ ሲያቀብለኝ ነበር፡፡ ምስሏን ከማየቴ አስቀድሞ፣ ምስሉ እስካሁን ስጠብቅ የቆየሁትን የገላ ውበት የያዘ መሆኑን ብቻ ሳይሆን…ምስሉ ላይ ያለውን ገላ ወደ እኔ ሸራ ስገለብጠው ምን እንደሚሆን ሁሉ ቁልጭ ብሎ እየታየኝ ነበር። የሚታየኝን ሁሉ ያየሁት ሞባይሉን ሳያቀብለኝ በፊት ነው፡፡ ምናቤ ውስጥ ያለው ስዕል በሞባይሉ ላይ ተደግሟል፡፡
“ቡና ቤቱ የት ነው?” አልኩት፡፡ ጠቆመኝ፡፡
“እሁድ እሁድ ብቻ ነው ቤቱ የሚከፈተው፤ ሌላውን ቀን ዝግ ነው፡፡ ፈረንጆች የሚያዘወትሩት  ሰፊ ቤት ነው፡፡ ፎቁ ላይ ደግሞ እንደ ጋለሪ ነገር አለ፡፡ የወጣት ሰዓሊያን ስዕል ይቀርባል፡፡ የእኔ አንድ ስዕል እዛ ስለነበረ… ተሸጦ ይሆን የሚለውን ለማረጋገጥ ስሄድ ነው ያገኘሁዋት፡፡ መጀመያ ቀን ብቻዋን ነበር የመጣችው፡፡ በሁለተኛው ሳምንት የሆነ ሰውዬ አብሯት ነበር…ሳታየኝ ፎቶ አነሳሁዋት፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ለምን ሄደህ ቼክ አታደርጋትም”  አለኝ፡፡ ይሄንን ያለኝ ሀሙስ ዕለት ነበር፡፡
ሶስቱ ቀን እንዲያልፍ ከመጠበቅ በላይ የሚያሰቃይ ነገር ከዚህ ቀደም ገጥሞኝ አያውቅም። ርሐብ የበለጠ የሚያሰቃየው የመመገቢያው ጊዜ መቅረቡ ሲታወቀን… መሰለኝ፡፡ የእኔ ርሀብ፤ ከጥበብ ፍላጐትም በላይ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ጠበቅሁኝ፡፡
ሦስት ቀኑን እንደ ሰላሳ አመት፡፡ ሀሌ ኮሜት…በእኔ እድሜ ተመልሳ አትመጣም ብለውኛል፡፡ ሃሌ ኮሜት ብትመጣ ባትመጣ እኔ ምንም አይገደኝም። እቺ ሴት ግን መጥታ ሳላያት…ሳልስላት ብቀር… ያለጥርጥር ከዚህ ቀደም የነበረው እምነቴ ባለበት ፀንቶ እንደማይቆም ተረዳሁኝ፡፡
እሁድ ወደ ቡና ቤቱ ሄድኩ፡፡  ፎቅ ላይ ወደ ጋለሪው ወጣሁ፡፡ በጣውላ የተሰራው ወለል ስፋት የተንጣለለ አዳራሽ ያክላል፡፡ በአዳራሹ ዙሪያ የተሰቀሉ ስዕሎች አሉ፡፡ ስዕሎቹን ለማየት ቸኮልኩኝ፡፡ የቸኮልኩት፤ እሷ ለሁለት ሳምንት ተመላልሳ ያየችው ስዕል ምን አይነት ስበት ቢኖረው ነው ብዬ በመጓጓቴ ምክንያት ብቻ ነው፡፡
እሷ ወድዳ የተመለከተችው ስዕል እኔ ከምወደው የሷ ገላ ጋር የሚተሳሰርበት አንዳች መረጃ ይገለጥልኛል ማለት እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ስዕሎቹ በሙሉ ተራ ናቸው፡፡ ያ ጓደኛዬ የሚስለውን አይነት ስዕል በተለያየ የሰአሊ ስም የደረደሩት ከመሆኑ በስተቀር ምንም ድንቅ ነገር የለባቸውም፡፡ በስዕሎቹ ላይ የቀረቡት እርቃን የሴት ገላዎች ናቸው፡፡ ግን ለእኔ ውበትም ሆነ ህይወት የሌላቸው ነበሩ፡፡ አእምሮዋ ወደ ኋላ የቀረ መሆን አለበት አልኩኝ… ይሄንን ስዕል ብላ ተመላልሳ የምትመለከት ከሆነ…
ግን እኔ ምን ቸገረኝ! እኔ የፈለኩት የእሷን አእምሮ አይደለም፤ ገላዋን እንጂ፡፡ ገላዋ ተሟልቶ አእምሮዋ እንዴት ወደ ኋላ ቀረ?...የእኔ አእምሮ በውበት (እውቀት) የመጠቀ መሆኑን እንዴት እርግጠኛ ሆንኩ?...አይ አልተሳሳትኩም! ጐዶሎ ስዕሎች ናቸው፡፡ ጐዶሎ ነገርን ነው በአሳሳል እስታይል ሙሉ ለማስመሰል የሚጥሩት፡፡ አስመሳዮች!!
ግን አስመሳዮቹ ጠቅመውኛል፡፡ የእነሱን የማይረባ ስዕል ለማየት ባትመጣ መቼ አገኛት ነበር? አስመሳይ ውበትን ለመቅሰም እውነተኛዋ ውበት መጥታለች…፡፡
መጠበቄን ቀጠልኩ፡፡ እስክትመጣ፡፡ ረጅሙ የጥበቃ አመታቴ… አጫጭር የጥበቃ ደቂቃዎችን እየወለዱ ወደ ሰዓታት ማደግ ጀመሩ፡፡ ሰዓታት ሸምጥጠው “ቀኑ ተገባደደ” አሉኝ፡፡ ተስፋ ቆርጬ ወደ ቤቴ መመለስ አልቻልኩም፡፡ ከመገፍተር ባልተናነሰ ትህትና ከቡና ቤቱ እንድወጣ ለመኑኝ፡፡
“የሚቀጥለው ሳምንት ተመለስ፤ ሌላ ሰዓሊ አዲስ ኤግዚቢሽን ያቀርባል” ሲሉኝ ጉሮሮዬ ላይ የሆነ ሳግ መሰል እልህ ሲጠራቀም ተሰማኝ፡፡
“ልብሷን አውልቃ መሳል አለባት” ስላቸው ግር ተሰኙ፡፡
“ማን?” አሉኝ፡፡
ጥያቸው ወደ ቤቴ ተጓዝኩ፡፡ በምንም አይነት ከዚችኛዋ ጋር አንተላለፍም፡፡ ገላዋ እስኪያረጅ ዝም ብዬ አላያትም… ብዬ እያሰብኩ ነው፡፡
ስልክ ደወልኩኝ፣ ወደ ሰዓሊው፡፡
“መቼ ነው የሚቀጥለው ኤግዚቢሽን የሚቀርበው?” አልኩት፡፡
“የሚቀጥለው ሳምንት”
“መቼ ይጠናቀቃል”
“ሦስት ሳምንት… ሦስት እሁዶች ከታየ በኋላ”
“ስራዎቼን ማስገባት እፈልጋለሁ… ለመጪው ኤግዚቢሽን”
“ማስገባት ትችላለህ፤ እንደ አንተ አይነቱን ሰዓሊማ አይናቸውን ሳያሹ ያስቀድሙሀል፡፡ ግን ምን የሰራሀቸው ስራዎች አሉ?...ለመመረቂያ ከሳልካቸው ስዕሎች በኋላ የሰራኸው መች አለህ?”
“በዚህ ሁለት ሳምንት የምሰራው ይበቃኛል፡፡…ደግሞ መጥፎ ስዕል ለመስራት ምን ጊዜ ይፈጃል? የጐረቤት ሴቶችን ማሽኮርመምና ለወሲብ ልብስ ሲያወልቁ በዛው መሳል ነው…”
“ለምን ለኤግዚቢሽኑ ቸኮልክ…?” አለኝ፤ ምላሼን በጉጉት እየጠበቀ፡፡ እምነቴ እንዳላዋጣኝ፣ ከዚህ ቀደም እመካበት የነበረው አጉል ጉራ እንዳበቃኝ እንድነግረውና… በእሱ እግር ስር እንድንበረከክ ነበር በምላሼ የጠበቀው፡፡
“…እኔ የምፈልጋት ሞዴል…ከተደበቀችበት ስፍራ ወጥታ ወደ እይታ የምትመጣው የእናንተ አይነት የማይረባ ስዕል ሲጠራት  ነው፡፡ አሳ ትልን ለመመገብ ሲል ከጥልቁ ውሃ ወደ አጥማጁ መንጠቆ ይወጣ የለ? ስለዚህ እቺን በዘመን አንዴ የምትገኝ ሴት (ገላ) በሸራዬ ላይ ለማጥመድ መንጠቆ ማዘጋጀት አለብኝ፡፡ መንጠቆው የማይረባ ስዕል ነው፡፡
የእናንተን አይነቱን ስዕል በፍጥነት ስዬ ኤግዚቢሽኑን አቀርባለሁ፡፡ እሷ መጥታ መንጠቆው ላይ ያለውን ትል ስትመለከት፣ እኔ ደግሞ እሷን እየተመለከትኩ ከጀርባ እስላታለሁ፤ ገባህ?”
“ለራስህ ያለህን ግምት ትንሽ ዝቅ ማድረግ ካልቻልክ ወደ አእምሮ ሀኪም ቤት መግባትህ አይቀርም” አለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲበሳጭ፣ ንዴቱን መደበቅ ሲያቅተው አደመጥኩት፡፡ የተናቀ መስሎት ነው የገነፈለው፡፡ ስልኩን ጠረቀመብኝ፡፡
ማሰቤን ቀጠልኩ፡፡
እሷ የማይረባውን ስእል ስትመለከት እኔ እሷን ከኋላ እመለከታታለሁ፡፡ ልብሷን እንድታወልቅ ለማግባባት አልደክምም፡፡ “ይህንን ዓይነት እንደ ሀሌ ኮሜት በመቶ አመት አንዴ የሚከሰት ገላ ይዘሽ አልሳልም ማለት የጥበብ ወንጀል ነው፡፡ ፈጣሪ ላንቺ አካልን፣ ለእኔ ደግሞ አካልን መርጦ የመሳል ችሎታ ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ ቶሎ መጐናፀፊያሽን አውልቂ! በህግ አምላክ” እላታለሁ…ብዬ እያሰብኩ ለራሴ ፈገግ አልኩኝ፡፡   

Read 12595 times