Tuesday, 29 December 2015 07:26

ዲሞክራሲ በጠና ታሟል!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(24 votes)

የዲሞክራሲ ስላቅ በካርቱን!

   ሰሞኑን በዲሞክራሲ፣ በነጻነት፣ በሰብዓዊ መብቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃዎችና ገራገር ቁምነገሮችን ከጉግል ላይ ሳስስ ለፖለቲካ በፈገግታ ግብአት አገኘሁ፡፡ በነገራችን ላይ ዛሬ ለለውጥ ያህል በጽሁፍ ብቻ ሳይሆን በካርቱንም ነው የምናወጋው፡፡
አብዛኞቹ ካርቱኖች ከእነመግለጫቸው በራሳቸው ጽሁፍ ማለት ናቸው፡፡ የተሟላ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ያውም ዘና እያደረጉ ነዋ። የተመቸኝም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ እንደ ስላቅም እንደ ምጸትም ያደርጋቸዋል፤ካርቱኖቹ፡፡
ለምሳሌ አንደኛው ካርቱን በት/ቤት ክፍል ውስጥ አንዲት መምህር ህጻናትን ታስተምራለች። “ህጻናት ዛሬ የምናወራው ስለ ዲሞክራሲ ነው” ትላቸዋለች፡፡ ህጻናቱም “ለምን?” ሲሉ ይጠይቃሉ። መምህርቷ ምን ብን ብትል ጥሩ ነው? “ብያለሁ ብያለሁ!” አሁን እቺ እንዴት ነው ህጻናትን ስለ ዲሞክራሲ ማስተማር የምትችለው? (አምባገነን ናት!) በእውኑ ዓለምም ያው ነው፡፡ (በጦቢያም ማለቴ ነው!) ዲሞክራሲን በተግባር ያልተለማመደ እንዴት ከሥርዓቱ ጋር ሊጣጣም ይችላል? (ሚስት ከመደብደብ ኋላ ቀር አስተሳሰብ መች ወጣንና?) አስተማሪም እኮ ከተማሪዎቹ ጋር ያለው ግንኙነት የተመሰረተው በምክክርና በንግግር ሳይሆን በዱላና በቅጣት ነው፡፡ ምን ለማለት እንደፈለግሁ ሳይገባችሁ አይቀርም፡፡  ከዲሞክራሲ ጋር አንተዋወቅም፡፡ ደማችን ውስጥ አልገባም፡፡    
በሌላ በኩል ደግሞ በገዢውም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ እንደ ልብ የተትረፈረፈ ቃል ቢኖር ዲሞክራሲ ነው፡፡ ክፋቱ ግን እንደ አንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮቻችን በዲሞክራሲም ላይ አገራዊ መግባባት ላይ (consensus) የደረስን አይመስለኝም፡፡ ከምሬ እኮ ነው፣ልክ እንደ ኢኮኖሚው፣ ዲሞክራሲው በምን ያህል እንዳደገ ወይም እንዳሽቆለቆለ ጥናት ሰርቶ ይፋ የሚያደርግ የግልም በሉት የመንግስት ተቋም የለም፡፡ እናም ስለ ዲሞክራሲያችን የምናወራው በእውር ድንብራችን ነው፡፡ እናም የዲሞክራሲ ግሽበቱ ስንት ደረሰ? ፍላጎቱና አቅርቦቱ ተመጣጥኗል ወይ? ህዝቡ፣ መንግስትና ተቃዋሚዎች በየጊዜው ከዲሞክራሲ ባህል ጋር እየተቀራረቡና እየተዋደዱ ነው ወይስ እየተራራቁና ባዕድ እየሆኑ ነው? እኒህን ሁሉ የምናወራው በግምት ላይ ተመስርተን ነው፡፡
እውነት በጦቢያ ዲሞክራሲ አለ? የምር ነው ወይስ የይምሰል? መንግስት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ያለው ቁርጠኝነት የቱን ያህል ነው? ተቃዋሚዎች ጨርሶ ቁርጠኝነት የለውም ይላሉ፡፡      
እኛ ተራ ተርታ ነዋሪዎች ደግሞ ከሰሞኑ ቀውስ ተነስተን (ጥናት አይፈልግም ብዬ ነው!) ዲሞክራሲው አደጋ ላይ መሆኑን፣ ክፉኛ መታመሙን መገመት እንችላለን፡፡ (ለወትሮም በሽታ ይወደው ነበር!) መቼም ግጭት ባየለበት፣የሰው ህይወት ባለፈበት፣ የአካል ጉዳት በደረሰበት፣ንብረቶች በወደሙበት፣ አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባልተቻለበትና ቢያንስ ለሳምንታት የሰላምና የደህንነት ስጋት አረብቦ በቆየበት ሁኔታ--- ዲሞክራሲው ጤነኛ ነው ማለት ዘበት ነው፡፡
ዘወትር ህመም በማያጣው ዲሞክራሲያችን ተስፋ ያድርብን የነበረው የኦሮሚያው ችግር እንደ አጀማመሩ በሰላማዊ ተቃውሞ ብቻ ወደ ውይይትና መፍትሄ ቢገባ ኖሮ ነበር፡፡ የዲሞክራሲ ሥርዓቱ አሳዳጊ እንደ ሌለው ምስኪን ልጅ ችላ እንደተባለ ሌላው ማሳያ በዚሁ በፈረደበት የማስተር ፕላን ጉዳይ አምናም ተቃውሞና ግጭት ተቀስቅሶ የሰው ህይወት ማለፉ ነው። ግና ከዓምናው ትምህርት በመውሰድ ቀወሱን ለመቀነስ አልቻልንም፡፡ አሁንስ በጠበጠን እኮ! /ጦሳችንን ይዞት ይሂድ!/  ይሄም የዲሞክራሲያችንን መታመም እንጂ ጤንነት አያሳይም፡፡




Read 7160 times