Saturday, 19 December 2015 11:50

ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በሰሞኑ የኦሮሚያና የጎንደር ግጭቶች ዙሪያ …

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

-    እዚህ አገር የኤርትራ መንግሥት እጅ የሌለበት ችግር የለም
-    ሁሉም ችግር የውጭ ኃይሎች ያመጡት ነው አልተባለም
-    የተቃውሞው ባሕርይ ከመሠረቱ ተቀይሯል
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ባለፈው ረቡዕ በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ጋዜጠኞች በተለይ  በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችና ግጭቶች፣ አተኩረው ላቀረቧቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ሚኒስትሩ የሰጧቸውን ማብራሪያዎች በመግለጫው ላይ የነበረው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቦታል፡፡
ስለ ኢትዮ-ሱዳን ድንበር መከለል፣ በአንዋር መስጊድ ስለደረሰው የቦንብ ጥቃት፣ ስለድርቁና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጥያቄው የማስተር ፕላን ነው የሚባለው በሁለት መንገድ ነው የሚታየው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ተረት የተወራባቸው፣ ብዥታ የነበራቸው፣ ለፌደራል ስርአቱ በየዕለቱ መጠናከር የተሟላ ቁርጠኝነት ያላቸው ወገኖች በእንደዚህ አይነቱ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ላይ ተመሥርተው ስጋት ውስጥ መግባታቸው የሚገርም ነገር አልነበረም፡፡
አንዳንዶቹ ከመነሻው ይሄ ማስተር ፕላን የሚባለው የፊንፊኔን ግዛት በኦሮሚያ ዞን ከተሞች ላይ ለመጫን ነው፤ ብለው ቢሰጉ፣ ለፌደራል ስርአቱ ካላቸው ቀናኢነት የመነጨ ስለሆነ ብዙ የሚያስገርም አይደለም፡፡ እንደተባለው ማስተር ፕላኑን በተመለከተ ማብራሪያ በመስጠት በኩል በክልልም በፌደራል መንግሥት ባለሥልጣኖችም በትክክል እንደተነገረው የመዘግየት ነገር ነበር፡፡ ይሄ አንደኛው ነው፡፡ በሁለተኛው ግን፣ አጋጣሚውን መጠቀም የሚፈልጉ ወገኖች ነበሩ፤ እነዚህ ወገኖች እነማን ናቸው፤ ለሚለው እገሌ እገሌ የሚለው ተራ ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡ ባለፈው ምርጫ ስልጣን ማግኘት የሚያስችል ቁመና ሊፈጥሩ ሞክረው ያልተሳካላቸው ወገኖች ብዥታውን ተጠቅመውበታል፡፡ በዚያ ላይ ተመሥርተው አብዛኛውን ህዝብ ግራ ማጋባት አልቻሉም፤ በነገራችን ላይ በዩኒቨርሲቲዎች ለመንቀሳቀስ ያደረጉት ጥረት ተቀባይነቱ ውስን ነበር፡፡ ስለዚህ ትኩረት ያደረጉት በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ነው፡፡
ማስተር ፕላኑን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ ለምን አልተፈጠረም፤ ለተባለው ፕላኑ ገና በረቂቅ ደረጃ ስላለ ነው፡፡ ፕላኑ ህዝቡ ተወያይቶበት የመጨረሻውን ቅርፅ የያዘና ለፖለቲካ ውሳኔ ለመቅረብ በሚያስችለው ቁመና ላይ የደረሰ አልነበረም፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ስለነበሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜ ሰጥቶ ለማብራራት የተደረገው ጥረት ውስን ነው፡፡ ይሄ ራሱን የቻለ ችግር ፈጥሯል፡፡ ይሄን አስታኮ በ4 እና በ5 የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ ሁከቱ ተቀስቅሷል፡፡ ማብራራት ለሚባለው ነገር ዘግይቶም ቢሆን መልስ መስጠት ሲጀመር በዚህ ብዥታ ላይ ተመስርቶ ሁከቱን ማስቀጠል አልቻለም፡፡ ያን ጊዜ ሌሎች ቅስቀሳዎች መካሄድ ጀመሩ፤ ድሮውኑም ከማስተር ፕላኑ ጋር ጥያቄ ያልነበራቸው፣ ችግሩን አራግበው ሌላ አላማ ለማሳካት የሚፈልጉ ወገኖች በየመንገዱ ይሄን ችግር በማራገብ፣ በተለይ ህፃናትና ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መሳርያ እስከ መንጠቅ የደረሰ ትንቅንቅ ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ከፍተኛ ዘመቻ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ፡፡
ያ ዘመቻ በባሕርው ከሁከትና ከብጥብጥ የተለየ ከቁጥጥር ውጭ ይወጣል ተብሎ አልተጠበቀም፤ ይሁንና እንቅስቃሴው በባሕርይው መለየት ጀመረ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተወሰኑ ግጭቶች በተለያዩ ከተሞች ተከሰቱ፡፡ በዚህም የጠፋ የሰው ህይወት አለ፤ የወደመ ንብረትም አለ፡፡ ይሄን ተከትሎ መንግስት መግለጫ በመስጠቱ፣ ጉዳዩን በሰከነ ሁኔታ ማየትና ከሁከትና ከብጥብጥ መንገድ ይልቅ መንግስትና ድርጅቱ የሚሉትን ብንሰማ ይሻላል ብለው በተረጋጋበት አጋጣሚ እነዚህ ኃይሎች መንገድ መቀየር ነበረባቸው፡፡ የተቀየረው መንገድ ደግሞ ድሮውም ጥያቄው የማስተር ፕላን ጉዳይ እንዳልነበረ አመላክቷል፡፡
በተቃውሞው በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል ነው?
በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ በባህርይው እየተቀየረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ጉዳቱ አይሏል፡፡ እዚህ ወገኖች ተቃውሞአቸውን የሚገልፁት በመፈክር አልነበረም፤ በተራ ድንጋይ ውርወራም አልነበረም፡፡ በዋናነት የሚዘውሯቸው ወገኖች ዒላማ እንዲያደርጉ የሚፈልጉት የመንግስት ተቋማትን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራር መኖሪያ ቤቶችን፣ የልማት ተቋማትንና የሞዴል አርሶ አደር ማሳዎችን ሳይቀር ነው ማጥቃትና ማቃጠል የጀመሩት፡፡ ከዚህ አንፃር ቁጥሩ የማይናቅ ዜጋ የአካል ጉዳት እና የሞት አደጋ ደርሶበታል፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነው፤ ምክንያቱም የጥያቄው መነሻ የአንድም ሰው ህይወት ማስከፈል የሚገባው አልነበረም፡፡ ነገር ግን በተሳሳተ መንገድ ስለተመራ ለሀብት ንብረት መውደምና ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡
የችግሩ መነሻ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ሊሆን አይችልም?
ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ ችግር አለብኝ ብሎ አምኖ፣ እነዚህን ችግሮች እፈታለሁ ብሎ ቃል የገባ መንግስት ነው ያለው፡፡ በማንኛውም መድረክ እነዚህ ጥያቄዎች ሲነሱ ምላሽ ማግኘት አለባቸው ብሎ የሚያምን መንግስት አለ፡፡ ከዚህ አንፃር በዚህ ተቃውሞ ውስጥ የገቡ ኃይሎች ጥያቄያቸው በተሳሳተ፣ በውጭ ኃይሎች ፍላጎት ላይ ብቻ ተመስርቶ የተፈጠረ ብቻ ነው ብሎ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ አብዛኛው የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ብሎ ከልቡ የሚማረር ዜጋም ጭምር፣ ከመንግስት ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት ይቻላል ብሎ በማመን ራሱን ከሁከትና ከግርግር አርቆ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ዜጎች ግጭቱ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ጥያቄ የምናቀርብበት መንገድ ስርአትን የሚያጠናክር እንጂ የሚንድ መሆን የለበትም የሚል አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ በዚያ ምክንያት ነው ግርግሩ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ሊቀንስ የቻለው፡፡ በተለይ ብጥብጡን የመሩት ወገኖች በግርግሩ ተስፋ የቆረጠ ዜጋ ተፈጥሮ ወደለየለት ስርአተ አልበኝነት እንዲገባ ነበር የፈለጉት፡፡ ይሄንን ማስቀረት የተቻለው  ወሳኝ ጥያቄ ያለው አብዛኛው ዜጋ ጥያቄው መቅረብ ያለበት በሰላማዊ መንገድ ነው ብሎ በማመኑ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ችግር የውጭ ኃይሎች ያመጡት ነው የሚል ድምዳሜ በመንግስት በኩል የለም፡፡
በክልሉ መንግስት፣ በፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጡት መግለጫዎች አስፈላጊነት በተመለከተ ….
እነዚህን መግለጫዎች መስጠት ያስፈለገበት ምክንያት፣ ባለፉት ሦስት ሳምንታት በተወናበደ መልኩም ቢሆን ወሳኝ ጥያቄ አነሳለሁ በሚል በርካታ ወጣት ዘንድ ተቃውሞው ሲጋጋል ነበር፡፡ አሁን ግን ከጀርባ ያሉ ኃይሎች ይሄን ጉዳይ ወደለየለት ብጥብጥ ካልመሩት በስተቀር ጥያቄዎቹ ከተመለሱ የነሱ ህልውናም ሆነ እንቀሰቅሳለን የሚሉት  አብዮትም መጨረሻው መሆኑን በትክክል በመገንዘባቸው ምክንያት የተቃውሞ ባሕርይው ከመሰረቱ ተቀይሯል፡፡
በተለይ በምዕራብ ሸዋ እና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ባሉ ጥቂት ከተሞች ያለው እንቅስቃሴ ከማስተር ፕላንም ጋር አይገናኝም፤ ሌሎች እንደመፈክር ከሚነሱ መልካም አስተዳደር ከመሳሰሉትም ጋርም አይገናኝም፤ አሁን ወደለየለት ስርአተ አልበኝነት እያመራ ያለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ሰአት፣ ምን ያህል ሰዎች ሞተዋል በሚለው ላይ መነጋገር ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው፡፡ ትንቅንቁ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ነበር፡፡ አንዳንድ ወጣቶች የፀጥታ ኃይሎችን ትጥቅ ለመንጠቅ ያደርጉ በነበረው እንቅስቃሴ ጭምር ያለፈ የሰው ህይወት አለ፡፡ በተቃውሞ ስም ስርአት እናፈርሳለን ብለው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ጋንጎች ምክንያት የሞዴል አርሶ አደሮች፣ ያልታጠቁ የፀጥታ ሰራተኞች፣ በአካባቢው የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በወረዳና በቀበሌ ባለስልጣናት ላይ በግልፅ ዘመቻ ተከፍቶ በጥይት ተደብድበው፣ በቢላዎ ታርደው የሞቱ በርካታ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ሰአት የተፈጠረው ጉዳይ አሳዛኝ ነው ከማለትና፣ መቆም አለበት ብሎ ከመነጋገር በዘለለ በቁጥር ላይ የምንነጋገረው ነገር ትርጉም ያለው መስሎ አይሰማኝም፡፡ የተቃውሞ ባሕርይ ተቀይሯል፡፡ የማስተር ፕላን ጥያቄው ሽፋን ነው፡፡ አሁን ጉዳዩ ወደለየለት ስርአተ አልበኝነት አምርቶ በጥቂት የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ከተሞች ውስጥ መንገዶች ይዘጋሉ፤ አስፋልቶች ይቆፈራሉ እንዲሁም የገበሬ ማሳዎች በእሳት ተቃጥለዋል፡፡ የመንግስትና የህዝብ ንብረቶች በእሳት እንዲጋዩ ተደርገዋል፡፡ የባለሀብቶች ፋብሪካዎችና የልማት ተቋማትም ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ጥቃቱ አሁንም እየቀጠለ ነው ያለው፡፡ ህብረተሰቡም በእንደዚህ አይነቱ ስርአተ አልበኝነት በመደናገጥ ለምን ርምጃ አይወሰድም፤ ብሏል፡፡
መንግሥት ከጀርባ ኃይሎች አሉ እያለ ይገልፃል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በስም ቢጠቀሱ እነማን ናቸው?
እነዚህ ኃይሎች ስም ያላቸው ኃይሎች ናቸው፡፡ እዚህ ሀገር ለምዝገባ ሲባል ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ በእንደዚህ ያለ የግርግርና ሁከት አጋጣሚ ራሳቸውን ቤተ መንግሥት ውስጥ እናገኛለን ብለው የሚያልሙ ወገኖች ናቸው፡፡ እነሱም እዚህ ላይ በስፋት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከምንም በላይ ግን ከነሱ ጋር በመሆን በውጭ ያሉ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችም በስፋት በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰማሩበት፣ በርካታ የሰው ህይወት አልፎ ንብረት ወድሞ የለየለት ስርአተ አልበኝነት ካልሰፈነ፣ ዓላማችን ሊሳካ አይችልም ብለው የተቻላቸውን ሁሉ እየተፍጨረጨሩ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
የታጠቁ ወንበዴዎች በየመንገዱ በየመንደሩ እየዞሩ ህዝብን የሚያሸብሩበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፤ ወደለየለት ሽፍትነት ተገብቶ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ሰዎች የተላለፈላቸው መመሪያ ይሄ ነበር ወይስ አልነበረም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በሀገራችን ላይ ሁከት የጠራ ወገን፣ ጋኔል የጠራ ወገን ጋኔሉን ስለመቆጣጠሩ እርግጠኛ መሆን አይችልም፡፡ አሁን የጠሯቸው ሰዎች የጠሩትን ጋኔል ስለመቆጣጠራቸው እርግጠኛ አይደሉም፡፡ ይህንን ጋኔን ልክ ማስገባት የሚችለው የተደራጀ ህዝብና መንግስት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በመንግስት በኩል እነዚህን በውንብድና ላይ የተሰማሩ ወገኖች ወደመጡበት ለመመለስ የሚያስችል ሥራ የግድ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
በቁጥር ላይ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ የገቡ ወገኖችም አሉ፡፡ መድረክ ስም ይጠራል፤ ኦፌኮ እገሌ እገሌ ይላል፡፡ እነ ኦፌኮ፣ እነ ግንቦት 7፣ እነ ኦነግ የጠሯቸውን አጋንንት የመመለስ ስራ ላይ መንግስት አተኩሮ መንቀሳቀስ በጀመረበት ሰዓት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን በተመለከተ ዝርዝር ውስጥ እየተገባ የሚኬድበት አይደለም፡፡ አሁን እነዚህ ኃይሎች ተጨማሪ ሁከትና ውድመት ሳያስከትሉ የማስቆም ስራ ላይ ነው ያተኮርነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አንድም ሰው ህይወቱ  ማለፍ አልነበረበትም ብሎ ለሚያምን መንግስት የቁጥር ጨዋታ መግጠም ስለሰው ልጅ ህይወት ደንታ ቢስ መሆን ነው፡፡
መንግስት ግጭቱን ለማርገብ ምን እያከናወነ ነው?
ተገቢ ጥያቄ ይዘው የተነሱ ሰዎችን በቅርበት በማነጋገር ብዥታውን ለማጥራት መንግሥት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ውይይቶች በስፋት ቀጥለዋል፡፡ የተጠሩትን አጋንንት ወደ የሰፈራቸው የመመለስ ስራ ላይም መንግስት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ ጥቃት ደርሷል በሚል ለተነሳው ጥያቄ፤ ለነዚህ ኃይሎች የዳንጎቴ ሲሚንቶ ቤተ ክርስቲያን አይደለም፤ ማንኛውንም ተቋም ለማፍረስ ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡ በአዲስ አበባ መስፋፋት የተነሳ የገበሬው ህይወት ህልውና ያጣል ብሎ የሚያምን ሰልፈኛ፣ የአካባቢን ማህበረሰብ የሚቀይርን ትልቅ ኢንቨስትመንት ካላቃጠልኩ አላማዬ አይሳካም ሊል አይገባውም ነበር፡፡ እነዚህ ተቋማት በህዝቡ ጠንካራ ጥረትና በፀጥታ ኃይሎች መስዋዕትነት ጭምር እየተጠበቁ ነው፡፡
በምርጫው ሙሉ ለሙሉ የህዝብ ይሁንታ አግኝቻለሁ ያለው መንግስት፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ይሄን ያህል ተቃውሞ ሊገጥመው ቻለ?
የግርግሩ አጋፋሪዎች ሆነው ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በተለይ መሪዎቻቸው በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ቁጥሩ የማይናቅ ሰው እንደመረጣቸው ይታወቃል፡፡ አብዛኛው ኢህአዴግን የመረጠው ሰውም ኢህአዴግ ስህተት እንዳለበት ያውቃል፤ ነገር ግን ስህተቱን ያርማል ብሎ ነው የመረጠው፡፡ አሁንም ቢሆን ሁከት ውስጥ የገባው፣ ትክክለኛ ጥያቄ ያነሳው የኦሮሚያ ህዝብ አይደለም፡፡ ኢህአዴግን የመረጠው ህዝብ በሙሉ የረካ ህዝብ ነው ብሎ ኢህአዴግ አያምንም፡፡ አሁን ሁከት የፈጠሩት ሰዎች ግን የአብዛኛውን ህዝብ ስሜት የወከሉ ተደርገው መውሰድ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡
በአማራ ክልል ጎንደር አካባቢ የተፈጠረው ችግር ምንድን ነው? መንግስት ግጭቱን ለማስቆም ምን እየሰራ ነው?
የተፈጠረው ግጭት ከቅማንት ብሔረሰብ የማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የቅማንት ብሔረሰብ ማንነት በመንግስት እውቅና ተሰጥቶት ተከብሮ ሳለ፣ “ይሄኛው ቦታ ለኔ ይገባል፤ ላንተ አይገባም” በሚል በተወሰነ መልኩ የተቀሰቀሱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ በግጭቶቹ ውስጥ ሌላ ዓላማ ያላቸው የውጭ ኃይሎች ጭምር የገቡበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚያ ላይ የመንግስት መዋቅርም በጉዳዩ ላይ ያለው ግንዛቤ የጠራ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ በዚህ የተነሳ የሰው ህይወት የጠፋባቸውና ንብረት የወደመባቸው ግጭቶች ነበሩ፡፡ አሁን ያ ግጭት በመንግስት ጥረት ረግቧል፡፡ በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል የነበረውን ሰላማዊ ግንኙነት ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል በተፈጠሩት ችግሮች ውስጥ የኤርትራ መንግስት ሚና ይኖረው ይሆን?
እዚህ ሀገር ውስጥ የኤርትራ መንግሥት እጅ የሌለበት ችግር የለም፡፡ የኤርትራ መንግሥት በቀጥታ በወታደራዊ አቅም ሊሰራው የሚችል ነገር ስለሌለ፣ ማጥቃት እፈልጋለሁ የሚልን ማንኛውም ኃይል ከመደገፍ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ጎንደር አካባቢ ለማስረግ የሚፈልጋቸው ታጣቂዎች አሉ፡፡ ታጣቂዎቹ አንዳንዶቹ ከልባቸው እናሸንፋለን ብለው አምነው ሊሆን ይችላል አላውቅም፤ ብዙዎቹ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፡፡ በምሥራቅ የሀገራችን ክፍልም የሚቻላቸውን ያህል ሰው ለማስረግ ሙከራ እያደረጉ ነው፡፡    
ጥንቃቄ ባይታከልበት፣ የኤርትራ መንግስት የሚሰራው ግድብ ስለሌለው የተገኘችዋን ፈረንካ ግርግር ፈጣሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ነው የሚጠቀመው፡፡ ከዚህ አንፃር ጭስ በሚታይበት አካባቢ ሁሉ የኤርትራ መንግስት እጅ ቢኖርበት ብዙም ሊያስገርመን አይገባም፡፡
የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር መካለል ጉዳይን በተመለከተ፤
በየአካባቢው የሚከሰቱ ትንንሽ ግጭቶችን ለማራገብ ጊዜ እየጠበቁ ከሚመጡ መፈክሮች አንዱ፣ የኢትዮ - ሱዳን ድንበር ይከለላል የሚለው መፈክር ነው፡፡ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እንኳ ከ6 ጊዜ በላይ ይኸው ድንበር ሊከለል ነው በሚል ዳያስፖራዎች መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ሁሉም በሚቀጥለው ወር ወይም ሳምንት ሊከለል ነው፤ ይላሉ፡፡ ወሩ ወይም ሳምንቱ ሲያልቅ ውሸቱ ይጋለጣል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን አሁንም ይሉኝታ የላቸውም፡፡ የሚከለል ድንበር በዚህ ወቅት አይኖርም፡፡ ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ ነው ድንበሩ ይከለል ሲባል የቆየው፡፡ ድንበሩ መከለል እንዳለበት እሙን ነው ግን ቀንና ቀጠሮ አልተሰጠውም፡፡ አሁን ሁለቱ አገገሮች በጋራ በሚለሙበት ጉዳይ ላይ ነው ትኩረት የተደረገው፡፡ ለዚህም የጋራ የልማት ኮሪዶር የማቋቋም ስምምነቶች አሉ፡፡ ይሄ ወደ ተግባር ቢገባ ጥሩ ነበር፤ ግን በቀጠሮ የተያዘ ነገር የለም፡፡
የድርቁን ጉዳይ በተመለከተ መንግሥት ምን እየሰራ ነው የሚገኘው?
በድርቁ የተጎጂዎች ቁጥር 10.2 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ እንደ በልግና መኸር ዝናብ ውጤት የተረጂዎች ቁጥር ይቀያየራል፤ ሊቀንስም ይችላል፡፡ አሁን ለምሳሌ በበልግ አምራች አካባቢዎች ላይ ጥሩ ዝናብ አለ፤ እሱ የሚቀጥል ከሆነ የተረጂዎች ቁጥር ይቀንሳል፤ አሁንም ትርፍ ምርት አለኝ እያለ መንግስት እስከ ወዲያኛው ይቀጥላል ማለት አይደለም፡፡ በተቻለ መጠን የውጭ እገዛ ቢመጣ ደስታውን አንችለውም፤ ጥሪም አድርገናል፡፡

Read 10983 times Last modified on Saturday, 19 December 2015 12:35