Saturday, 19 December 2015 11:11

ብሩንዲ ወደ አስከፊ የእርስ በርስ ግጭት እያመራች ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

     በብሩንዲ ሶስት ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በመንግስት ተቃዋሚዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ዜጎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን አገሪቱ ዳግም ወደ አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት እያመራች ነው ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሩንዲ የተለያዩ አካባቢዎችና በመዲናዋ ቡጁምቡራ እየተባባሰ የመጣው ግጭት እንደሚያሳስባቸው የገለጹት አል ሁሴን፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን በምርጫ እንደሚወዳደሩ መግለጻቸው የቀሰቀሰው ቁጣ በተቃዋሚ ሃይሎችና በመንግስት ደጋፊዎች መካከል ለወራት የዘለቀ ግጭት መፍጠሩንና በርካታ ዜጎች መሞታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የፖለቲካ መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትርጉም ያለውና አካታች የሆነ ውይይት በማድረግ በብሩንዲ የተከሰተውን ግጭት ለመግታትና አገሪቱን ከከፋ ጥፋት ለመታደግ እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው ሳምንት አርብ እጅግ የከፋ የተባለ ግጭት መከሰቱንና በመዲናዋ ቡጁምቡራ በሚገኙ ሶስት ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በመንግስት ተቃዋሚዎች በተፈጸመ ጥቃት 79 ያህል የመንግስት ተቃዋሚዎችና ስምንት ወታደሮች መሞታቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡
አገሪቱ ለረጅም አመታት ከዘለቀውና ከፍተኛ እልቂት ካስከተለው በጎሳ የተከፋፈለ የእርስ በርስ ጦርነት የወጣችው ከአስር አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ስልጣናቸውን ለማራዘም ማሰባቸው የፈጠረው ተቃውሞና አመጽ፣ አገሪቱን ወደቀድሞው አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያስገባት ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ገልጧል፡፡
ካለፈው ሚያዝያ ወር አንስቶ የተከሰተው ግጭት፣ በፕሬዚዳንቱ ላይ በተሞከረ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት ሳያበቃ ተባብሶ መቀጠሉን የዘገበው ቢቢሲ፣ ከአመቱ መጀመሪያ አንስቶ በአገሪቱ ከ600 በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንና ከ220 ሺህ በላይ ዜጎችም አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን አስታውሷል፡፡

Read 1802 times