Saturday, 11 February 2012 11:09

ትንሿ ዛምቢያ ወይስ ታላቋ አይቬሪኮስት?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነገ ሲገባደድ ለፍፃሜ ጨዋታ ለሻምፒዮናነት ቅድሚያ ግምት የተሰጣት አይቬሪኮስትና ምንም ያልተጠበቀችውን ዛምቢያ አገናኘ፡፡ ዛሬ ለደረጃ ጋና እና ማሊ ይጫወታሉ፡፡ ዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫው 5 ያህል የአህጉሪቱን ሃያል ብሄራዊ ቡድኖች ባለማሳተፉ ቀዝቃዛ ይሆናል ተብሎ ነበረ ይሁንና የ2 አዘጋጅ አገራትን ድንቅ መስተንግዶና ተሳትፎ በማሳየት፤ አዳዲስ ጠንካራ ቡድኖችን በማውጣትና ለዋንጫ የተጠበቁ ቡድኖችን ባልተጠበቀ ውጤት ለስንብት በመዳረግ ድምቀት ተላብሷል፡፡ በአንፃሩ የአፍሪካ ዋንጫው በግብ ድርቅና በተመልካች እጦት በተወሰነ ደረጃ መደብዘዙ አልቀረም፡፡የደቡብ አፍሪካ ዞንን በመወከል ለዋንጫ የተጠበቁትን ሴኔጋልን በምድብ ማጣርያ እንዲሁም በግማሽ ፍፃሜ ጋና በመገርሰስ ለነገው የዋንጫ ጨዋታ የቀረበችው ዛምቢያ ለመጀመርያ ሻምፒዮናነት ታነጣጥራለች፡፡ በብዙ ሚሊዬነሮችና በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች በሚጫወቱ ምርጥ ተጨዋቾቿ ለፍፃሜ የደረሰችው የምእራብ አፍሪካዋ ተወካይ አይቬሪኮስት በበኩሏ ለሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድል የምትቀርብ ይሆናል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫው ለተቀናቃኞቻቸው ያስቸገሩ ቡድኖች በማሰለፍና በምርጥ ማጥቃትና መከላከል መጫወታቸው የዋንጫ ጨዋታውን ያሳምረዋል በሚል ተጠብቋል፡፡

የሁለቱም ቡድኖች አምበሎች የአይቬሪኮስቱ ዲዲዬር ድሮግባ እና የዛምቢያው ክሪስቶፈር ኩቶንጎ ባስመዘገቧቸው እኩል 3 ጎሎች የዋንጫ ጨዋታውን ለኮከብ ግብ አግቢነትም ይፎካከሩበታል፡፡ ኩቶንጎ የቡድናችን ተጨዋቾች በአይቬሪኮስት ላይ ግብ ማስቆጠር እንደሚችሉ በተደጋጋሚ በመንገር አነሳስቻለሁ ብሎ ተናግሯል፡፡ በሌላ በኩል በፍፃሜው ለአይቬሪኮስት ግብ ያስቆጥራል በሚል ግምት የተሰጠው ዠርቪንሆ እንዳኮራቸው የተናገሩት የአርሰናሉ ቬንገር ተጨዋቹ በሻምፒዮናው ከፍተኛ ልምድና መሻሻል ማሳየቱን ገልፀው ዋንጫውን ይዞ ከተመለሰ ለቡድናችን ከባድ መነቃቃት ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ዋንጫው ዛሬ ከሚደረገው የደረጃ እና ከነገው የዋንጫ ጨዋታ በፊት በተደረጉ 30 ግጥሚያዎች 74 ጐሎች ተመዝግበዋል፡፡ በየጨዋታው በአማካይ 2.47 ጐሎች ተቆጥረዋል፡፡ አጠቃላይ የተመልካች ብዛት ደግሞ 456‚332 ሲሆን እያንዳንዱ ጨዋታ በማካይ 15‚211 ተመልካች ነበረው፡፡

የመዳብ ጥይቶች ወይም ቺፖሎፖሎ በሚል ቅፅል ስያሜው የሚታወቀው የዛምቢያ ቡድን ለዋንጫ ጨዋታ ሲቀርብ የዘንድሮው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን በተሳትፎ ታሪኩ ሁለቴ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ ዛምቢያ ከነገ በፊት በቀረበችባቸው የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታዎች አንዱን ካይሮ ላይ በ1974 እኤአ በዛዬር ተሸንፋ አጥታለች፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ከነገ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ለዋንጫ የቀረበው በ1994 እኤአ በቱኒዚያ ተደርጎ በነበረ ጊዜ ሲሆን በወቅቱ ከዓመት በፊት በአውሮፕላን አደጋ በርካታ ተጨዋቾች አልቀው ከዚያ በሃላ ምትክ ሆነው በተሰለፉ ተጨዋቾች ከናይጄርያ ጋር ለዋንጫ ቀርባ 2ለ1 በመሸነፍ ሻምፒዮናነቱ አምልጧታል፡፡ ከ20 ዓመት በፊት ብቸኛ የአፍሪካ ዋንጫ ድልን ያስመዘገበው የአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ ለፍፃሜ ጨዋታ ሲቀርብ የነገው ፍልሚያ 3ኛው ነው በቅርብ ጊዜ የዋንጫ ድሉን ለፍፃሜ ደርሶ በመለያ ምቶች የተነጠቀው ከ6 ዓመት በፊት በግብፅ ተካሂዶ በነበረው 25ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው፡፡

 

 

Read 2159 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 11:15