እንኳን ለመውሊድ በአል በሰላም አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው ጭልጥ አድርጎ ይጠጣል፡፡ እናም ጓደኞቹ…
“ለምን መጠጥ ታበዛለህ…” ምናምን ነገር ብለው እንደ ምክር አይነት ይሞክሩታል፡፡
እሱዬው ምን ቢል ጥሩ ነው… “የሰው ልጅና ብሎኬት ውሀ ያስፈልጋቸዋል…” ብሏቸው አረፈ፡፡
ምን መሰላችሁ…አንድ ቀን ለብሎኬት ‘ማጠጫ’ ተብሎ ጉድጓድ ውስጥ በተጠራቀመ ውሀ ውስጥ ተኝቶ ሲያድር ምን እንደሚተርት በሰማነው፡፡
ስሙኝማ…አሁን፣ አሁን ሰዎች ተቆፍሮ ክፍቱን በተተወ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ጉዳት መድረሱን በተደጋጋሚ እንሰማለን፡፡
እናላችሁ…ጥያቄና ጠያቂ በበዛበትና ተጠያቂና መልስ ሰጪ ማን እንደሆነ ግራ በገባበት ዘመን ውስጥ ነን፡፡ ‘መላሽ የተገኘ’ ጊዜም… አለ አይደል… “እንደውም እሱን ጉድጓድ ማን እንደቆፈረው አናውቅም…” አይነት ነገር ሁሉ ሰምተናል፡፡ አስቸጋሪ ጊዜ ነው፡፡ ታዲያላችሁ… “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ…” በተባለው መሰረት ‘ጨርቅ መስሎን የገባንበት’ መንገድ ላይ ‘ያልተጠበቀ ጉድጓድ’ እየተጋረጠብን ተቸግረናል፡፡
የምር እኮ…በዚህ ዘመን ምን በመሰለውና ‘ላይ ላዩን’ በሸለለው መንገድ ላይ (‘የውስጡን’ የሚያውቁት አንድዬና መንገዱን የሠሩት ብቻ ናቸዋ!) አገር ሰላም ብላችሁ ስትሄዱ ‘ማን ቆፈረው የማይሉት ጉድጓድ’ ፊታችሁ ገጭ!
እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በሌላ ሌላውም ነገር ሁሉ “ጨርቅ ነው…” ብለን በገባንበት መንገድ ላይ ‘ማን ቆፈረው የማይሉት ጉድጓድ’ እየገጠመን ተቸግረናል፡፡
የሆነ ወይ እንትና አዲስ ጓደኛ ያበጃል፡፡ (‘የጥንት’ ጓደኛ የሚባል በጠፋበት ዘመን አዲስ ጓደኛ ማግኘት አሪፍ ነው፡፡) ታዲያማ…በቃ በ‘ሲፕ’ ቤቱ እየዞሩ “ለእኛም አምጪ፣ ለአንቺም ጠጪ” ሲሉ…በየኮንሰርቱና ሲኒማ ቤቱ “ያቺኛዋን አንተ ተሟሟት፣ ይቺኛዋን እኔ አሰምጣለሁ…” ምናምን ሲባባሉ ምንም ሀይል የሚለያያቸው አይመስልም፡፡
እሱዬው በየደረሰበት “እንዴት አይነት የተባረከ ሰው መሰላችሁ…” ምናምን እያለ የምድሩንም የሰማዩንም ሲቪ ያሳምርለታል፡፡ ታዲያላችሁ ‘ጓደኝነት’ በተመሰረተ በአሥራ ሦስተኛ ቀኑ… “በሁለት ቀን ውስጥ የምመልስልህ አንድ ሺህ ብር ታበድረኛለህ?” ሲል አዲስ ጓደኛ ይጠይቃል፡ እሱዬም… “ምን ችግር አለ፣ ጓደኝነት ለመቼ ነው!” ብሎ ለማንም ሳያማክር አሥሯን ‘ሳይንቲስት’ መስጠት፡፡
ሁለቱ ቀን ሃያ ሁለት ይሆናል፡፡ እናማ… እሱዬውም “አንድ ሺህ ብሩን ለጉዳይ ስለፈለግሁት ስጠኝ…” ሲል ከመልአክ ጋር ሲያመሳስለው የከረመውን ‘ቤስት ፍሬንድ’ ይጠይቀዋል፡፡ ያኛው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አንድ ሺህ ብር! የምን አንድ ሺህ ብር?”
“ረስተህ ይሆናል አንጂ በሁለት ቀን እመልስልሀለሁ ብለኸኝ አንድ ሺህ ብር አበድሬህ ነበር…”
“ለእኔ! ከሌላ ሰው ጋር ተምታቶብህ ይሆናል…”
ከዚያ በኋላ አዲስ ጓደኛ ሆዬ ደብዛው ይጠፋል። ነገርዬው ‘ሚሽን አኮምፕሊሽድ’ ነዋ! እናማ… ወዳጃችን ከዛ በኋላ…
“የለየለት ሞላጫ ነው…”
“እኔ እኮ ዝም በዬ ነው እንጂ በፊቱንም ሁኔታው አላማረኝም ነበር…”
“ስሰማ እኮ አገሩን ሁሉ እየዞረ የሚያታልል ነው አሉ…”
ምናምን እያለ ቢለፈልፍ ማን ይስማው! ነገርዬው…
እቴ አበባሽ ስትለኝ ከርማ
ጥላኝ ሄደች በሐምሌ ጨለማ
አይነት ነው፡፡
እናማ… መተማመንን የሚያጠፉ… አለ አይደል…‘ማን ቆፈረው የማይሏቸው ጉድጓዶች’ በዝተዋል፡፡ ሰውየው…ማንንም ቢሆን አያምንም፡፡ እናላችሁ፣ ምን ቢል ጥሩ ነው… “አንድ እንግዳ ስሸኝ የማደርጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የእሱ የሆነ ምንም ዕቃ ረስቶ አለመሄዱን፣ ሁለተኛ የእኔ የሆነ ምንም ዕቃ ይዞ አለመሄዱን ማረጋገጥ፡፡”
(ዘንድሮ እንደሁ… ስንካካብም ‘ሰማይ ጫፍ ድረስ፣’ ስንናናድም ‘ገሀነም ወለል’ ድረስ ሆኗል። ልክ ነዋ…‘እቴ አበባሽ’ ሲባሉ ከርሞ ‘በሐምሌ ጨለማ’ ባዶ ቤት ማጨበጨብ የተለመደ ነዋ!)
እናላችሁ… “ጨርቅ ነው…” ብሎ በገባበት መንገድ ላይ ‘ማን ቆፈረው የማይሉት ጉድጓድ’ ሄዶ ዘው!
የሆነ የሙያ ምናምን አይነት ማህበር ይቋቋሟል። እናማ ቅስቀሳው ሞቅ ያለ ነው… “ስማ…ለየብቻችን ከምንዳክር ተሰባስበን ብንንቀሳቀስ በአጭር ጊዜ አሪፍ ቦታ እንደርሳለን…” ምናምን ይባላል፡፡
ታዲያላችሁ…በመጀመሪያዎቹ ወራት ምን አለፋችሁ…እንቅስቃሴው ለብቻ ይሆናል፡፡ በዚህ ከቀጠለ አይደለም ለአገራችን፣ ለዓለምም ምሳሌ እንሆናለን…” ምናምን ይባላል፡፡ (ስሙኝማ…እግረ መንገዴን ዘንድሮ መሥሪያ ቤቱ ሁሉ “ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን…” “የምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ምናምን ለመሆን…” አይነት አባባሎችን ማነው ‘ያከፋፈላቸው!’ ኮሚክ እኮ ነው…አይደለም ምሥራቅ አፍሪካ፣ አፍሪካ ምናምን… ለሚጢጢ ወረዳ እንኳን የሚመጥን ሥራ መሥራት ሳይችሉ ማዶ፣ ማዶውን ማለታቸው አይገርማችሁም!)
እናላችሁ…ጥቂት ወራት ቆይቶ ‘ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም’ ይሆናል፡፡ እናላችሁ… ለካስ አመራሮቹ ሆዬ የአባላቱን መዋጮውን ምን ያገቡት ምን ሳይታወቅ የባንክ ደብተሩ ባዶ! እንደውም የተወሰኑት ከአሜሪካ ደውለው ለዘመዶቻቸው… “ደህና ደርሰናል…” ምናምን ብለዋል ይባላል፡፡
እናማ… አባል ሆዬ “ጨርቅ ነው…” ብሎ በገባበት መንገድ ላይ ‘ማን ቆፈረው የማይሉት ጉድጓድ’ ሄዶ ዘው!
እናላችሁ፣ እየዞርን… “የእንትን ማህበር ቢሮ የት ነው?” እያልን ቦታውን አንጠይቅ ነገር አጨብጭቦ ዝም ነው፡፡
ጥያቄና ጠያቂ በበዛበትና ተጠያቂና መልስ ሰጪ ማን እንደሆነ ግራ በገባበት ዘመን ውስጥ ነና!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የቦታ ነገር ሲነሳ የሆነ ነገር ትዝ አለኝ…
ቢሮው በር ላይ ቆመን… “የአየር መንገድ ቢሮ የት ነው?” “እንትን ባንክ የት ነው…” የምንል ሰዎች በዝተናል፡ በዛ ሰሞን አንድ ሽልል ያለች እንትና ‘መሀሙድ ሙዚቃ ቤት’ አካባቢ ሰዎችን… “ፒያሳ በየት በኩል ነው?” ብላ ስትጠይቅ እንደነበር ሰማን፡፡
ሀሳብ አለን…የመንገድ ስሞች አንዳንድ ቦታ እየተተከሉ እንዳለው ሁሉ በትላልቁ የእንትን መንገድ፣ የእንትን መንገድ እየተባለ የሌላው አገር ስም እንደሚለጠፍ ሁሉ… ‘ፒያሳ’ ‘መርካቶ’ ‘ኮሪያ ሰፈር’ ምናምን እየተባለ ይለጠፍልን፡፡ ‘ካዛንችስ’ ተብሎ ይለጠፍ እንዳንል ካዛንቺስ እንኳን ለእኛ ለቀያሾቹም ልትጠፋ ምንም አልቀራትም፡፡) ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…በብዙ ነገር ውስጥ “ጨርቅ ነው…” ብለን በገባንበት መንገድ ላይ ‘ማን ቆፈረው የማይሉት ጉድጓድ’ እየገጠመን ተቸግረናል፡፡ ነገሮች ሁሉ የማይሳኩት…አለ አይደል…ግማሾቹ አይደለም ሊጋመሱ… በበቂ እንኳን ሳይጀመሩ የሚከሽፉት ‘ማን ቆፈረው የማይሉት ጉድጓድ’ እየተደነቀረብን ነው፡፡ ጉድጓዶች ሁሉ የሚደፈኑበትን ዘመን ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!
Saturday, 19 December 2015 10:15
‘ማን ቆፈረው የማይሉት ጉድጓድ…’
Written by ኤፍሬም እንዳለ
Published in
ባህል