Saturday, 11 February 2012 10:57

ደርባ ግሩፕና የኢንቨስትመንት እቅዱ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ቤተ - ሠሪ እፎይ አለ

የሰሜኑን አቅጣጫ ይዘን ነው የምንጓዘው፡፡ የሱሉልታን ጋራና ከተማ አልፈን 30 ኪ.ሜ እንደተጓዝን ጫንጮ ከተማ እንደርሳለን፡፡ አሁን በስተግራ ታጥፈን፣ ወደ ሙገር በሚወስደው መንገድ ጥቂት እንደሄድን በግንባታ ላይ ያለውን ኢትዮ ሲሚንቶ ፋብሪካ እናያለን፡፡ ከዚያ ብዙም ሳንርቅ ደግሞ ምርት የጀመረውን አቢሲኒያ ሲሚንቶ ፋብሪካ እናገኛለን፡፡ ጉዟችንን ቀጥለን ወደ መዳረሻችን ስንቃረብ፣ የሆላንዶችን የአበባ እርሻ እያየን አልፈን 38 ኪሜ ያህል እንደተጓዝን ደርባ ከተማ እንደርሳለን፡፡ ከተማዋን አቋርጠን ወደ ቀኝ ታጥፈን 2 ኪ.ሜ ያህልና በአጠቃላይ 70 ኪ.ሜ እንደተጓዝን ከሙገር ሸለቆ አናት ላይ በ123 ሄክታር መሬት ላይ ተገማሽሮ የቆመውን ግዙፉን ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ እናገኛለን፡፡

ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ በዓመት 25 ሚሊዮን ኩንታል የሚያመርት ግዙፍና ዘመናዊ ፋብሪካ ሲሆን፣ በግንባታው 5ሺ ኢትዮጵያውያንና 1,500 ቻይናውያን ተሳትፈው፣ በ38 ወራት ተጠናቋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሚንቶ በምረትና በማሰራጨት ለ20ሺ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

የፋብሪካው ሥራ ሲጠናቀቅ የፕሮጀክት ወጪው 351 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን የተገመተ ሲሆን፣ ከሲሚንቶ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ 600 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚሆን አቶ ኃይሌ አሰግዴ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ለመሥራትና ለማስጀመር 25 ኪ.ሜ መንገድ፣ 6 ኪ.ሜ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ተሠርቷል፡፡ ከእንጭኒ ከተማ የተጠለፈ ከፍተኛ የመብራት ኃይል ተሸካሚ ትራንስፎርመር መስመር ሦስት ወረዳዎችን አቋርጦና 49 ኪ.ሜ ተጉዞ ባለ 132 ሜጋ ዋት ሰብስቴሽን ተተክሏል፡፡ ኃይል ተሸካሚው ባለፈበት መስመር ግራና ቀኝ ከቦታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮች ካሣ ተከፍሏል፡፡ አንድ ባለ 140 ሜትር ረዥም ድልድይና 10 አነስተኛ ድልድዮች ተገንብተዋል፡፡ በሰከንድ 10 ሊትር የሚሰጡ 6 የውሃ ጉድጓዶች 17 ኪ.ሜ ከፍተኛ የውሃ መስመር ተሠርቷል፡፡

አቶ ኃይሌ፣ ወደ ገበያ በምንገባበት ቀን የአገሪቷ የሲሚንቶ ፍላጐት ከመሟላቱም በላይ ከ3 እስከ 5 ባሉት ቀጣይ ዓመታት፣ ሲሚንቶን በተመለከተ እጥረት አልባ ኢትዮጵያን እናያለን ሲሉ፣ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ እንግዶች ስሜታቸውን በከፍተኛ እልልታና ጭብጨባ ገልጸዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት ሼክ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲ ኢንቨስትመንትን በአገሪቷ ለማስፋፋት ለተጫወቱት ተጨባጭ ሚና ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የመጀመሪያው የሚሊኒየም ልዩ የወርቅ ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ላይም ሼክ መሐመድ እስካሁን በአገሪቷ ባደረጉት ኢንቨስትመንት በፍፁም ያለመርካታቸውን ገልፀው፣ ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባላቸውና አጠቃላዩን ማኅበራዊ ሲስተም በሚያሳድጉ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር፡፡

በዚሁ መሠረት ከአራት ዓመት በፊት፣ በደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊነት፣ ዳሽን ሲሚንቶና ደርባ ላይምና ኬሚካል ፕሮጀክቶችን የሚመራ፣ በቀጣይም እሴታዊ ጠቀሜታቸውን እያየ የሚያስፋፋ፣ እንዲሁም ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ዘርፎች በማሰብና በማቀድ ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ያለው የደርባ ግሩፕ ተቋቋመ፡፡

በዓለም አቀፍ አሠራር የተረጋጋ ኢኮኖሚ የሲሚንቶ ፍላጐት ከጂዲፒ ዕድገት ጋር የተቆራኘ ሲሆን፣ በአንድ ፐርሰንት የጂዲፒ ዕድገት፣ የሲሚንቶ ፍላጐት በ1.2 ፐርሰንት ያህል ያድጋል ያሉት አቶ ኃይሌ፤ እስከ አንድ አመት የሲሚንቶ ፍላጐትና ዋጋ ይረጋጋል የሚል ግምት እንዳላቸው፣ በሚቀጥሉት ዓመታት የሲሚንቶ ዕድገት በአማካይ በ18 በመቶ እንደሚያድግም ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሲሚንቶ ፍላጐት ዕድገትን ተከትለው በአማራ ክልል ደጀን ወይም ሞጣ ላይ በቀን 40ሺ ኩንታል ሲሚንቶ የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ በሦስት ወር ውስጥ ለመጀመር ዕቅድ ተይዟል፡፡ በመቀጠልም፣ ደርባ ላይ በቀን 80ሺ ኩንታል የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ በ2006 ይጀመራል፡፡

ከሲሚንቶ ጋር ተያያዥነት ያለው ብረት ነው ያሉት አቶ ኃይሌ፤ በቅርቡ ኮምቦልቻ አካባቢ ጦሳ የብረት ፋብሪካ ግንባታ ለመጀመር ተቆጣጣሪ መሃንዲሶች የተቀጠሩ ሲሆን የግንባታ ፕሮፖዛል ተቀብለው እየገመገሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው፣ በዓመት የተለያየ መጠን ያላቸው 1.3 ሚሊዮን ቶንስ ብረት ሲያመርት ለ1000 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ሀዋሳ ላይ የኬብል ፋብሪካ ለመገንባት ጥናት ተጀምሯል፡፡

ሼክ መሐመድም በቀጣይ ሦስት ዓመታት ለመሥራት የታቀዱትን ፕሮጀክቶች ጠቅሰዋል፡፡ “ትግራይና የአማራ ክልሎችን የምንጨምርበት የጅንስ ፋብሪካ አለ፡፡ ጥጡ ከትግራይ ይመጣል፤ ፋብሪካው ደግም በወሎ ይተክላል፡፡ በእርሻ ተጀምሯል፡፡ ግን 446 ሚሊዮን ቶን ሩዝ እየበቀለ፣ አንዳንድ ምሁራን የተቅማጥ መድኃኒት ነው ሲሉ ያሳዝናል፡፡ ክቡር ጠ/ሚ/ር፣ ሳላጋንን፣ ዱባይ ውስጥ ያሉ ባለ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴሎች የሚጠቀሙት የኢትዮጵያን አትክልት ነው፡፡ የስኳር ፕሮጀክታችን ጥናት ‘ጠ/ሚኒስትር ቢሮ ሄዷል’ ብለውኛል፣ እንዴት እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡ ከኦቾሎኒ (ለውዝ) የሚሠራ ዘይት ለማምረት መሬቱን ተረክበናል፡፡ ኤክስፐርቶችን ለማምጣት ኢሮፕና ማሌዢያ ልከናል፡፡ እነሱ ሲመጡ የዘይት አቅርቦት በአጭር ጊዜ (በ18ወር) ውስጥ ተጠናቅቆ፣ የኢትዮጵያን የራሷን ዘይት እናቀርብላችኋለን፡፡” ብለዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል የተጀመረው እርሻ ዋነኛ ሰብል ሩዝ ቢሆንም ስኳር ድንች፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላና አኩሪ አተርም ይመረታሉ፡፡ ኩባንያው፣ ከክልሉ መንግሥት 10ሺ ሄክታር መሬት በሊዝ የገዛ ሲሆን፣ 290ሺ ሄክታር መሬት ለመግዛት በሂደት ላይ ነው፡፡ ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ 52 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሲሆን ከዚህ ውስጥ እስካሁን 3.45 ቢሊዮን ብር ለተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎች ግዥ፣ ለአማካሪዎችና ለኮንስትራክሽን አገልግሎቶች ወጥቷል፡፡ የፕሮጀክቱ ሥራ ሲጠናቀቅ፣ ለ350ሺ ዜጐች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ለውጭ ገበያ ከሚያቀርበው ሽያጭ በየዓመቱ 17.25 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡ አስሩ ሺ ሄክታር ለ15ሺ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ከሽያጩም 1.72 ቢሊዮን ብር ይጠበቃል፡፡

ደርባ ግሩፕ በሆቴሎችና ሪዞርቶችም ይሳተፋል፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ሆቴልና ሪዞርት ለመገንባት አቅዷል፡፡ ኮምቦልቻ፣ ላንጋኖ፣ አርባ ምንጭ፣ ጋምቤላ፣ ላሊበላ፣ ጐንደር፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክና ሻላ ሐይቅ ጥሩ የቱሪስት መስህብነት እንዳላቸው ተገንዝቧል፡፡

የኮንስትራክሽን ኩባንያም ያቋቁማል፡፡ በኢትዮጵያ በቂ የኮንስትራክሽን መሳሪያ፣ የመሥሪያ ካፒታል፣ የሠለጠነ የሰው ኃይልና የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የለም - እጥረት አለ፡፡ ዘርፉ በአገሪቷ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ሌላው ደግም በግሩፑ ውስጥ ላሉ ፕሮጀክቶች የግድብ፣ የመስኖና የመንገድ ሥራ የሚያገለግሉ የተለያዩ መሳሪያዎች ተገዝተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ያቋቁማል፡፡

የጉድጓድ ቁፋሮ ኩባንያም ማቋቋም ከግሩፑ ዕቅዶች አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎችና ባለሙያዎች የሚደራጅ ሲሆን እስከ 1000 ሜትሮች መቆፈር የሚችሉ መሳሪያዎች ግዢ ተፈፅሞ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ ሳራ ሲቲ እና መንትዮቹ ሕንፃዎች ግሩፑ፣ በሪል እስቴት የሚሳተፍባቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ሳራ ሲቲ ዘመናዊ አፓርትመንቶችን ከገበያ ማዕከላት (Shopping malls) ጋር የያዘ በመዲናዋ እንብርት የሚሠራ ቁጥር አንድ የገበያ ሕንፃ ነው፡፡ ይህ ምኞታዊ የከተማ ልማት እውን የሚሆነው በዘርፈ ብዙ የአርክተክቸራል ዲዛይንና በኢንጂነሪንግ አማካሪነት በመካከለኛው ምሥራቅ ቀዳሚ በሆነው “INNOVATORS” ኩባንያ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የላቀ የጥራት ደረጃ ያላቸው 192 ባለ 5 ፎቅ ቅንጡ የአፓርታማ ሕንፃዎችን ይኖሩታል፡፡

ባለ 38 ፎቆቹ መንትያ ሕንፃዎት በሜክሲኮ አደባባይ ለቢሮ አገልግሎት የሚሠሩ ናቸው፡፡ ግሩፑ የሪል እስቴት ፕሮጀክት በአቃቂ አካባቢ ሲኖረው፣ የራሱን ዋና መ/ቤት በሾላ አካባቢ ይገነባል፡፡

ማያ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 38 ኪ.ሜ ላይ ጫንጮ ከተማ ሳይደርስ የተሠራ ፋብሪካ ነው፡፡ ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ 25 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በዓመት 80 ሚሊዮን ፒፒ ከረጢት ያመርታል፡፡ 50 ሚሊዮኑ ከረጢት ለደርባ ሲሚንቶ አገልግሎት ሲውል 30 ሚሊዮኑ ከረጢት ለሽያጭ ያቀርባል፡፡ የፋብሪካው መሳሪያዎች ዘመኑ ያፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሲሆኑ በዚህ ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ምርት ይጀምራል፡፡ ፋብሪካው ለ300 ዜጐች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን ከመቶ ዘጠናዎቹ ሴቶች ናቸው፡፡

አምና የተቋቋመው ደርባ ትራንስፖርት 1000 ቮልቮ የጭነት መኪናዎች፣ ለሲሚንቶ ፈላጊው ትራንስፖርትን ያካተተ አገልግሎት መስጠት ያስችላሉ፡፡ ለመኪናዎቹ ግዥ 162 ዩሮ ወይም 211 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሆኗል፡፡

ለደርባ ትራንስፖርት መኪናዎች የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጥም ደርባ ወርክሾፕ ይቋቋማል፡፡ “ደርባ ላይም ኤንድ ኬሚካልስ” ኩባንያ በ288 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንትና በ250 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ፋብሪካ ነው፡፡ በአገሪቷ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ በአርአያነት የሚጠቀስ ዘመናዊ የግብይት ሲስተም ደርባ ትሬዲንግ ሃውስ ይቋቋማል፡፡

በዘመናዊ ቢዝነስ፣ ኮርፖሬት ኩባንያዎች ከሚያገኙት ትርፍ የተወሰነ ያህል ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲዉል ይመድባሉ፡፡ ደርባ ግሩፕም ከዚሁ ዓላማ ጋር የሚመሳሰል የሼክ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲ ፋውንዴሽን አቋቁሟል፡፡ የፋውንዴሽኑ ዓላማ በድህነት ቅነሳና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ምርምር የሚያደርጉትን ለመደገፍና ለማበረታትት ፈንድ ይመድባል፡፡ ለድህነት ቅነሳ አስተዋጽኦ ላደረጉ ወይም ምርጥ ተመክሮ ላሳዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሽልማት ይሰጣል፡፡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የኮሌጅ ትምህርታቸውን መቀጠል ላልቻሉ ጎበዝ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ይሰጣል፡፡ ሴት ተማሪዎች ለስኮላርሺፕ እንዲያመለክቱ ይበረታታሉ፡፡

ዘመናዊው የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከአባካቢ ብክለት የፀዳ ለመሆኑ ዓለም አቀፍ እውቀና አግኝቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተራቆተውን አካባቢ አረንጓዴ ለማልበስ አንድ ሚሊዮን ዛፎች እንደሚተክል አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የጤና ማዕከል፣ ሁለት የጐልማሶች ማሠልጠኛ ማዕከልና ድልድይ የሠራ ሲሆን ለተዘዋዋሪ ብድር የሚሆን 2.5 ሚሊዮን ብር ሰጥቷል፡፡ የክልሉ መንግሥት መሬት ሲሰጣቸው ሁለት ት/ቤቶች ለመሥራት ቃል ገብቷል፡፡

በደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ አካባቢ 500 የመኖሪያ አፓርትመንቶች፣ (ባንክ፣ ፀጉር ማስተካከያ፣ የውበት ሳሎን፣ የኢንተርኔት ማዕከል፣ የተለያዩ ሱቆች፣ ጂም፣ …) ያለው የገበያ ማዕከል፣ 500 ሰዎች መያዝ የሚችል አዳራሽ፣ መመገቢያ ስፍራ፣ መዋኛ፣ የቅርጫትና የመረብ ኳስ፣ የሜዳ ቴኒስ ሜዳ፣ አነስተኛ ስታዲየም፣ 1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አነስተኛ ሆስፒታልና ሌሎችንም የያዘ የሠራተኛ መኖሪያ መንደር በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

 

 

Read 17694 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 12:31