Saturday, 12 December 2015 11:59

አንጌላ መርኬል የ2015 የታይም መጽሄት ተጽዕኖ ፈጣሪ ተባሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የአይሲሱ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል
    በአለማችን በየአመቱ ስማቸው በክፉም ሆነ በደግ በስፋት የተነሳና አነጋጋሪ የሆኑ ግለሰቦችን እየመረጠ ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ታይም መጽሄት፣ የጀርመን መራሄ መንግስት አንጌላ መርኬልን የ2015 የታይም መጽሄት የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ በማለት መምረጡን አስታወቀ፡፡
ታይም መጽሄት ረቡዕ ዕለት በድረ-ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀው፣ ለዘንድሮው የታይም መጽሄት የአመቱ ምርጥ ሰው ምርጫ የመጨረሻ ዙር ከደረሱት ስምንት ዕጩዎች መካከል የመጽሄቱን አዘጋጆች አብላጫ ድጋፍ ያገኙት አንጌላ መርኬል አሸናፊ በመሆን ተመርጠዋል፡፡
ባለፉት 29 አመታት የታይም መጽሄት የአመቱ ምርጥ ለመባል የበቁት ብቸኛዋ ሴት የሆኑት አንጌላ መርኬል በዘንድሮው አመት በዩሮዞን ከተከሰተው የኢኮኖሚና የስደተኞች ቀውስ ጋር በተያያዘ ሰፊ የመገኛኛ ብዙሃን ሽፋን ያገኙ መሪ ሆነው መዝለቃቸው ለመመረጥ እንዳበቃቸው ተነግሯል፡፡
በዕጩነት ከቀረቡት ግለሰቦች መካከል አለማችንን በሽብር ተግባሩ እያመሳት የሚገኘው የአሸባሪው ቡድን አይሲስ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ ሁለተኛውን ደረጃ ሲይዙ፣ አነጋጋሪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል ተብሏል፡፡
የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ፣ እንዲሁም አይሲስ የተባለውን የሽብር ቡድን አጠፋለሁ ብለው ጦራቸውን ያዘመቱት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በእጩነት ቀርበው ነበር፡፡
ባለፈው አመት የታይም መጽሄት ምርጥ ተብለው የተመረጡት በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተከሰተውን የኢቦላ ቫይረስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ባለሙያዎች እንደነበሩ ያስታወሰው መጽሄቱ፣ በ2013 ደግሞ የሮማው ሊቃነ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ተመርጠው እንደነበር አክሎ ገልጧል፡፡
ታይም መጽሄት የአመቱ ምርጦቹን መምረጥ የጀመረው እ.ኤ.አ በ1927 ሲሆን በወቅቱ የተመረጡትም ቻርለስ ሊንድበርግ የተባሉ አውሮፕላን አብራሪ እንደነበሩ መጽሄቱ አስታውሷል።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፣ ማህታማ ጋንዲ፣ አዶልፍ ሂትለርና ኦባማን የመሳሰሉ የአገር መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች ከዚህ ቀደም የታይም መጽሄት የአመቱ ምርጦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

Read 2165 times