Print this page
Saturday, 12 December 2015 11:54

የሩስያው ኮሙኒስት ፓርቲ ስታሊንን ሊዘክር አቅዷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ፔኔዛ በተባለችው የሩስያ ከተማ የሚንቀሳቀሰው ኮሙኒስት ፓርቲ፤ አምባገነኑን የቀድሞው የሩስያ መሪ ጆሴፍ ስታሊንን ለመዘከርና ብዙዎች እንደሚሉት ሰውዬው አምባገነን መሪ አለመሆናቸውን የሚያሳዩ ጥናቶች የሚሰሩበት የጥናት ማዕከል በስማቸው ለመክፈት ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ፓርቲው 2016ን የስታሊን አመት በሚል ለማክበር ማቀዱን እንዳስታወቀ የዘገበው ቢቢሲ፣ አመቱን ሙሉ የሚከናወኑ የተለያዩ ስታሊንን የሚዘክሩ ዝግጅቶችን ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና በስታሊን ስም ሊቋቋም የታሰበው የጥናት ማዕከልም ሰውዬውን በአምባገነንነት በመወንጀል ያለ አግባብ ስማቸውን የሚያጠፉ አካላትን ፕሮፓጋንዳ የሚያከሽፉ ፊልሞች እንደሚታዩበት የፓርቲው ሃላፊ ጂኦርጂ ካሜኔቭ መናገራቸውን ገልጧል፡፡
የስታሊን አመት ክብረ በዓል ከሁለት ሳምንታት በፊት በሚከፈት የፎቶ ግራፍ ኢግዚቢሽንና የስታሊን የልደት በዓል ስነስርአት የሚጀመር እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ በመጋቢት ወር መጀመሪያም ስታሊን የሞተበት ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቋል፡፡
መጪው የፈረንጆች አዲስ አመት የስታሊን ህገ መንግስት በመባል የሚታወቀው የሩስያ ህገ መንግስት የጸደቀበት 80ኛ አመት መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኮሙኒስት ፓርቲውም በስታሊን ታላቅነት ዙሪያ ምርምር ለሚያደርጉ ወጣት ተመራማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዱን አመልክቷል፡፡

Read 1967 times
Administrator

Latest from Administrator