Print this page
Saturday, 12 December 2015 11:25

በዕድሮች የዐይን ብሌን ልገሳ ቅስቀሳ ሊጀመር ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)


             የዐይን ባንኩ እስከአሁን ለ1227 ሰዎች ንቅለ ተከላ አከናውኗል
             ከ10ሺ በላይ ሰዎች የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡
                   
      ከ7 ሺ በላይ የሚሆኑት የአዲስ አበባ ከተማ ዕድሮች አባላት የዐይን ብሌን ልገሳ እንዲያደርጉ ቅስቀሳ ሊጀመር ነው፡፡ በከተማዋ የሚገኙት ዕድሮች የጋራ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮችም በአርአያነት የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ የሚያስችላቸውን የቃልኪዳን ሰነድ ፈርመዋል፡፡
በዐይን ባንኩ ዋና መስሪያ ቤት የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በተገኙበት ከትናንት በስቲያ በተካሄደ ስነ-ሥርዓት ላይ የምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ አባላትና ከፍተኛ የሥራ አመራሮች በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ፈርመዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ታምራት ገ/ማርያም፤ የዕድር አባላቶቹ ከህልፈት በኋላ የዐይን ብሌናቸውን ለዐይን ባንኩ ለመለገስ የሚያስችል ቅስቀሳ ለማድረግ ቃል በመግባት ከአይን ባንኩ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር መነን አያሌው ጋር በጋራ ስምምነት ሰነዱ ላይ ተፈራርመዋል፡፡
ከሀያ ዓመታት የዐይነ-ስውርነት ህይወት በኋላ ማንነቱን ከማያውቀው ለጋሽ ባገኘው የዐይን ብሌን ሳቢያ ብርሃን ለማግኘት የቻለውና በአሁኑ ወቅት በአንድ ት/ቤት በርዕሰ መምህርነት በመስራት ላይ የሚገኙ አቶ ደጀኔ ሚደቅሳ በዚህ ወቅት እንደተናገረው፤ የዐይን ብሌን ልገሳው እንደሱ ያሉ በአይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ለዐይነ- ስውርነት የተዳረጉ ወገኖችን ማዳን እንደሚችል ገልፆ ለዚህም ሁሉም ሰው እንዲተባበር ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ለዐይን ባንኩ ከህልፈት በኋላ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተው ፈርመዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ከ10 ሺ በላይ ሰዎች በቃል ኪዳን መዝገቡ ላይ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተው እንደፈረሙም ታውቋል፡፡ የዐይን ባንኩ ከተቋቋመበት 1995 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለ1,227 ሰዎች የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ በማድረግ ብርሀናቸውን እንዲያገኙ አድርጓል፡፡    

Read 3956 times