Saturday, 12 December 2015 11:15

‘እንዳካሄድ ቁርጠኝነት’…‘ማስቀጠል ሂደቱ’….

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሦስቷ ወር ‘ፉት’ አለች አይደል! ዕድሜም ‘ፉት’ አለ፣ ኑሮም ‘ፉት’ አለ፣ ዓለምም ‘ፉት’ አለ…ቦታችንን ላለማስደፈር ነቅነቅ ያላልነው የሆነ ዓለም አቀፍ ሽልማት ያስፈልገናል፡፡ እኔ የምለው…‘ባለንበት መርገጡ ሰለቸን’ የሚል ሮማንቲክ ኮሜዲ ፊልም ይሠራልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ይሄ የስም አወጣጣችን ነገር ሀዲዱን ስቶላችኋል፡፡ ልክ እኮ… አለ አይደል… ስም የምናወጣው በህልማችን ይመስላል፡፡ ፊልም ማየት አበዛን መሰለኝ!
ለምሳሌ ‘ጆኒ’ ምናምን ድሮ ማቆላመጫ ነበር፡፡ ጆኒ ለመባል ደግሞ ‘ኦሪጂናል’ ስማችን የግድ ዮሀንስ መሆን የለበትም፡፡ አሁን ግን እነ ጆኒ እንደ መደበኛ ስም እየወጡ ነው አሉ፡፡
ኮሚክ እኮ ነው…ሁልጊዜም ከራሳችን ለማምለጥ እየሮጥን በየባዕድ አገሩ ደግሞ የእኛ ሰዎች አይደላችሁም እየተባልን…ይሄ ‘የመገዛት አስተሳሰብ’ መቼ እንደሚላቀቀን ለመገመት እንኳን አስቸጋሪ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በ‘አብዮቱ’ ሁለት ልጆቻቸውን ሆቺ ሚን፣ ቼ ጉቬራ ብለው የሰየሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ መአት ቤተሰቦችም ልጆቻቻውን አብዮት ‘ብለዋል፡፡’ ከዛ በፊት ደግሞ እንዲሁ ነበር፡፡
እኔ የምለው…ሀሳብም ጥያቄም አለን… ዘንድሮ ‘የቦተሊካው ነፋስ የነካቸው’ ስሞች በብዛት የማይወጡሳ!  እናማ…የጊዜውን ሁኔታ ያገናዘቡ ስሞች ለመስጠት ለሚያስቡ እንደ መነሻ ሀሳብ ሊሆን ከቻሉ ቀጥለው ባሉት ‘ዕጩ ስሞች’ የ‘ኮፒራይት’ ጥያቄ ላለማንሳት ይህ ‘አምደኚስት’ በመሠረተ ሀሳቡ ተስማምቷል፡፡ ቂ…ቂ...ቂ…
‘እንዳካሄድ ቁርጠኝነት’
‘ማስቀጠል ሂደቱ’
‘መተካካት ዘለቄታ’
‘አቅጣጫ ተደራሽ’
‘አጠናክሮ ትራንስፎርሜሽን’
ምናምን ማለት ነው፡፡ አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ…እንዲህ፣ እንዲህ አድርገን ካላስቀመጥነው በኋላስ ታሪክ ይህን ዘመን እንዴት ብሎ ሊያስታውሰው ነው! ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ የሚለው እንደሁ ገና ከአሁኑ ተረስቷል!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ለጓደኛው እያወራለት ነው፡፡ “የሰው ነገር ይገርምሀል፡፡ ባቡር ላይ ተሳፍሬ ጋዜጣዬን ወንበሩ ላይ አነጠፍኩና ላዩ ላይ ተቀመጥኩበት፡፡ አንዱ ይመጣና… ‘ወንድም እሱን ጋዜጣ እያነበብከው ነው?’ ይለኛል፡፡”
“አንተ ምን አልከው?” ሲል ጓደኛው ይጠይቀዋል፡፡
“ብድግ ብዬ የጋዜጣውን ገጽ ገለጥኩና እንደገና አንጥፌ ላዩ ላይ ተቀምጥኩና… “አዎ እያነበብኩ ነው፣’ አልኩታ!”
የምር ግን ዘንድሮ አንዳንድ ሰዎች የሚጠይቋችሁ ነገር… ግራ ይገባችኋል፡፡
እናማ… የስም መስጠት ነገርን ካነሳን አይቀር… ይኸው የአፍሪካ አገሮች ሁሉ ‘አደባባዮች’ አላቸው አይደል! …እናማ…ሀምሳ ምናምኑ ቦታ ከተወሰደ ለእኛ ምን ተረፈን አያሰኝም!
ታዲያላችሁ…እኛንስ “መሰባሰቢያ ከተማችን ነች፣ ማስታወሻ እናቁምላት...” ምናምን ብለው አገራቸው ላይ ‘አዲስ አበባ አደባባይ’ አይነት ነገር ያላቸው አገሮች ስንት ናቸው! አደባባይ እንኳን ቢቀር ‘አዲስ አበባ ፉል ቤት’ የሚል አላቸው!
ይኸው ፑሽኪን እንኳን ምን የመሰለ አደባባይ አለው አይደል!…እንኳንም ኖረው፡፡ አንድ ጊዜ እኮ ፑሽኪን የእኛ ነው፣ የእኛ አይደለም በሚል ክርክር ቢጤ ነበር ልበል፡፡ አራትና አምስት መቶ ዓመታት ወደኋላ ተንሸራቶ በአባቱ በኩል አበሻ ነው ምናምን ከማለት “ለኢትዮዽያ ምን ሠራላት?” ምናምን ማለት ይሻል ነበር፡፡ አሁን የፑሽኪን ዝርያዎች ቢጠየቁ “እውነት ነው፣ ፑሽኪን የሀበሻ ደም ስላለው እንኮራበታለን’ ይላሉ?
ግን እንደው የፑሽኪንን ያህል በስማቸው የሆኑ ነገሮች ሊሰየሙላቸው የሚገቡ ሰዎች ጠፍተው ነው! የምር እኮ ኮሚክ ነው…ያው ‘እንደለመደብን’ እርስ በእርስ ከመወዳደስና ከመከባበር ይልቅ ‘ፈረንጅ ይግድለኝ አይነት አስተሳሰብ ሊለቀን ስላልቻለ ቢመስል አይገርምም፡፡ (አሁንማ ኦፊሴላዊ መጠሪያዎች ሁሉ ‘የፈረንጅ ብርጉድ፣’ ‘የፈረንጅ ብርጉድ’ አይነት መሽተት ጀምረዋል። ‘ትራንስፎርሜሽን’ ‘ዳይሬክቶሬት፣’ ‘ክለስተር፣’ ‘ፖሊስ ስቴሽን’ አይነት ቃላትን ፍቺ የሚተነትን የአማርኛ መዝገበ ቃላት እየጠበቅን ነው፡፡)
አንዳንዴ ሳስበው የእኛው በሆኑ ስሞች ከሚጠሩ አደባባዮችና መንገዶች ይልቅ በውጪ ስሞች የሚጠሩት የሚበልጡ ይመስለኛል፡፡
‘ፈረንጆቹ’ እነ ‘ኮልስን፣’ ‘ዌዘረል፣’ ‘ካኒንግሀም’ ምናምን ሁሉ መንገድ አላቸው፡፡ ደጎልም አደባባይ አላቸው፡፡ እኔ የምለው… እኛን ለሚያክሉ ቀውላላ ሰውዬ ያቺን የምታክል አደባባይ ‘ፌይር’ ነው!
ዳያስፖራዎችም አደባባይ አላቸው፡፡ (‘ዳያስፖራ’ ኦፊሴላዊ ባልሆነ መንገድ ‘የአማርኛ ቃል’ ሆኗል ብዬ ነው በአገሪኛ ያበዛሁት፡፡) ለነገሩማ ከእኛ ከ‘ኢንዲጂነሶቹ’ ይልቅ ‘ለፈረንጅ የቀረቡት’ እነሱ አይደሉ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…የዓለም ዋና ከተሞች ሁሉ ካፌና ሬስቱራንት አላቸው፡፡ እግረ መንገዴን…ሀሳብ አለን…ለምንድነው የአውሮፓ ህብረት አባል ያልሆነው? ልክ ነዋ! ይሄ ሁሉ የአውሮፓ ከተማ ሁሉ ካፌና የሬስቱራንት መጠሪያ ሆኖ የለም እንዴ!
ስሙኝማ…የሌኒንን ሀውልት ‘አነሱት’ እንጂ (‘አፈረሱት’ ነው እንዴ የሚባለው!) አፍሪካ ኤኮኖሚ ኮሚሽን ፊት ለፊት ሆኖ “አፍሪካ እኔ እሻልሻለሁ…” የሚል ይመስል ነበር፡፡
የግዳችንን ‘ፈረንጅ’ ‘ፈረንጅ’ እንድንል ሚዲያውም አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ከራሳችን በርካታ ብሔራዊ በዓላት ይልቅ እነ ታንክስ ጊቪንግና እነ ቫለንየታይንስ ዴይ የአየር ሰዓቱን በሚቆጣጠሩበት ዘመን ወደ ራስ ዘወር ብሎ ለማየት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
የሚዲያ ነገር ከጠቀስን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ… “ትምህርት ለአገር ዕድገት ወሳኝነት እንዳለው አቶ እንቶኔ ለስብሰባው አስገነዘቡ…” አይነት ነገር ‘መክፈቻ ዜና’ በሚሆንበት አገር…ኧረ እባካችሁ የሚል ሲጠፋ አስቸጋሪ ነው፡፡
“የእንትን ዳይሬክቶሬት ሀላፊ ጤናማ ህብረተሰብ የልማት አንቀሳቃሽ ሞተር ነው አሉ…” ያሉትና እነ ሲ.ኤን.ኤን. ሰምተው እንዳልስማ ያላስተላለፉት የሚቆጨን አለን፡፡ ልክ ነዋ…ይህን ብሩህ አእምሮ ብቻ ሊያስበው የሚችለውን ነገር ለዓለም አበርክተው እነክርስትያን አማንፑርና እነቤኪ አንደርስን ያላወሩት ያው ተፈረንጅ ‘ምቀኝነት’ ስለሆነ አይደል!
አሁን ለምሳሌ ይሄ ‘አምደኚስት’ ተብዬ… “በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ተበልቶ ለሳምንት ያህል ሰውነት ምግብ እንዳያስፈልገው የሚያስችል የስንዴ ዘር አገኘ…” ቢባልና አንዱ ቦስ ደግሞ “ንጽህናቸው ያልተጠበቁ አካባቢዎች ለበሽታ ይዳርጋሉ…” ቢሉ ‘ሰበር ዜና’ የትኛው መሰላችሁ…የቦሱ ‘ግኝት፡፡
እናላችሁ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይሄ ሰውንም ሆነ የተለያዩ ስፍራዎቻችን የምንሰይምበት ‘ድንበር ሰባሪ’ አስተሳሰብ መጀመሪያ በአገር ውስጥ ዜማ ቢቃኝ አሪፍ ነው፡፡ (ኧረ ስነ ጽሁፍ!)
እናማ…ቢሆንም ባይሆንም የስም አወጣጣችንን ከጊዜው ጋር ለማስኬድ ከፍ ብለን የጠቀስናቸውን ስሞች ለመድገም ያህል…
‘እንዳካሄድ ቁርጠኝነት’
‘ማስቀጠል ሂደቱ’
‘መተካካት ዘለቄታ’
‘አቅጣጫ ተደራሽ’
ይሄን ሁሉ ‘ከጣፍን’ በኋላ የመጡልን አንድ፣ ሁለት ስሞች እንጨምርማ… (በሁለተኛ መደብ ብዙ ቁጥር መጠቀሱ ያዘለው ‘ምስጢር’ እንደሌለው ልብ ይባልልንማ…ልጄ፣ ዘንድሮ ፈጠን ብሎ በብሎኬት እንኳን ባይቻል በሰንሰል ቢጤ ነገር ግጥም አድርጎ ‘ማጠር’ ነው!)
ዘመንን የሚያስታውሱን ነገሮች ይቀመጡልንማ!
‘አጣዳፊ ስትራቴጂ’
‘አጠናክሮ ትራንስፎርሜሽን’
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4499 times