Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 February 2012 10:49

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንደኛ ክፍል ገብተን ትምህርት ስንጀምር የአንደኛ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃን አጠናቀን፣ ዩኒቨርስቲ ገብተን እያልን እየተመኘንና እያለምን ነው የምንማረው፡፡ የእያንዳንዳችንን ህይወት በደንብ ብንመረምር በህይወታቸው የመጀመሪያ ፈተና ወድቀው ወደ ሁለተኛው የህይወት ምዕራፍ መሻገር ያቃታቸው ጓደኞቻችን ይኖራሉ፡፡ እያንዳንዳችን የብዙ ሰዎችን ታሪክ እናውቃለን፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በጋራ አጠናቀን ከፊሎቻችን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ስንሸጋገር ሌሎች ታች የቀሩ ናቸው፡፡ ሁላችንም ግን አንደኛ ክፍል ስንገባ በጋራ ከሩቅ እናልመው የነበረው ዩኒቨርስቲ ድረስ ለመማር ነበር፡፡ ከአንደኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርስቲ እስኪገባ ያለው ሂደት ብዙ ውጣ ውረድ፣ መውደቅ መነሳት፣ በየጊዜው ያላሰብናቸው በጣም ጠንካራ ተወዳዳሪ ተማሪዎች ያጋጥሙናል፡፡

ሰዎች ነንና ማህበራዊ ኑሮው፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሌሎችም የተለያዩ መሰናክሎች ያጋጥሙናል፡፡ አሸናፊዎች ምክንያት አይደረድሩም እንጂ እንደማነኛውም ሰው በችግር ነው የሚያልፉት፡፡ ነገሮች የቱንም ያህል ተሟልቶላቸዋል ቢባል እንኳን ጊዜ ሊያጥራቸው ይችላል፡፡ ሁኔታዎች አይመቻቹም፡፡ በሰዎች ህይወት በ365ቱ ቀናትና በየዓመቱ የሚታዩ አዳዲስ ክስተቶች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ቀን አዲስ ነው፡

ገበሬው ብዙ ዝናብ እንዲዘንብለት ቢፈልግም እንኳን 365ቱም ቀናት የዝናብ ወቅት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ወራቶች እንኳን የክረምት፣ የፀደይ፣ የበጋና የበልግ ወቅት በሚል ተለክተው የተቀመጡ ናቸው፡፡ እነዚህን ወቅቶች በወቅቱ ለሚያስፈልገው ሥራ በትጋትና በተደጋጋሚ ጥረቶች ካልተጠቀምንባቸው በአግባቡ እየተጠቀሙባቸው ካሉት ሰዎች እየራቅን እንሄዳለን፡፡ ከነሱ ለመድረስ ደግሞ መክፈል ከሚገባን ዋጋ ከእጥፍ በላይ እንከፍላለን፡፡ እርስዎም ያሉበትን ደረጃ መለስ ብለው ይዩት፡፡ የት ነዎ? ከእድሜዎ ጋር የሚመጣጠን የህይወት ደረጃ ላይ ነዎ?

ወደሚቀጥለው ክፍል በሄድን ቁጥር የሚቀረን እያነሰ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ አትሌቶች ሩጫ ሲጀምሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በጋራ ሳይራራቁ ነው የሚሮጡት፡፡ ፅኑዎቹ መጨረሻ ላይ ጥቂት ሆነው ነው ሲሮጡ የምናገኛቸው፡፡ በቢዝነስ አሸናፊነት መምራት ነው፡፡ መምራት ሲባል ደግሞ በውድድር ሌሎችን መብለጥ ነው፡፡

ሌሎችን በውድድር በልጦ ሚሊዬነር፣ ቢሊዬነት ሊሆንና ገንዘብ ለመቁጠር ብቻ ሳይሆን ለሀገርና ለህብረተሰብ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ያለ የመጨረሻ ቁርጠኝነት ነው ፅኑነት የሚባለው፡፡ ከዚህ አንፃር እስኪ ራስዎን ይመዝኑ፡፡ ያለፈው ማንነትዎን ከዛሬው ጋር ያወዳድሩት፡፡ በተለይ በቢዝነስ ውስጥ ከሆኑ ከእርስዎ ጋር የጀመሩ ሰዎች የት ደርሰዋል? እርስዎስ የት ነዎት? የበለጧቸውም የበለጡዎትም አሉ፡፡ ለምን? ዋናው መመዘኛ ደግሞ የትላንት እርስዎን ተወዳድሮ አሸናፊ መሆን ነው፡፡

ምናልባት ቸልተኝነቱ፣ ታካችነቱ በዝቶ ይሆን በሌሎች የተበለጡት? እስኪ ያለፉበትን መለስ ብለው ይፈትሹት፡፡ ፅኑነት የተሟላ ዓለም ስለሆነ በአብዛኛው እርስዎ ፅኑ ነዎ ወይስ ፅኑ የሚሏቸው ሌሎችን ነው? በቂ ፅኑነት ካለዎ ከማንም በባሰ ሁኔታ እርስዎ አይፈተኑምና ከሌሎች ጋር እኩል መንገዱን እየሄዱ ከሆነ አሸናፊ የማይሆኑበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

(በዶ/ር ወሮታው በዛብህ ከተዘጋጀው “በኢንተርፕረነርሽፕ መበልፀግ” መፅሃፍ የተቀነጨበ)

 

 

Read 4565 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:51